የሚዲያ ነፃነት ይረጋገጥ፤ የታሰሩ ጋዜጠኞችም በአስቸኳይ ይፈቱ!!! – ከአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
የሚዲያ ነፃነት ይረጋገጥ፤ የታሰሩ ጋዜጠኞችም በአስቸኳይ ይፈቱ!!! – ከአንድነት ለዴሞክራሲና ፍትህ ፓርቲ
(አንድነት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY (UDJ)
ከጥቅምት 27 ቀን 2006 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 29 ቀን 2006 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስድስተኛው የአፍሪካ ሚዲያ መሪዎች ፎረም እየተካሄደ ነው። ፓርቲያችንም ይህንን ጉባዔ በአንክሮ እየተከታተለው ሲሆን በርካታ የአፍሪካ ሚዲያ ባለሙያዎች የፕሬስ ነፃነት ባልተረጋገጠበት፣ የግል ጋዜጦችና መፅሄቶች ተልካሻ ሰበብ እየተፈለገ በሚዘጉበት፣ ጋዜጠኞች ሀገር ጥለው እንዲሰዱ በሚደረግበት፣ በሀገር ውስጥ አንድም የግል ቴሌቪዥን ጣቢያ ባልተቋቋመበት፣ ስርዓቱን የሚተቹ ጋዜጠኞች ወደ እስር የሚወረወሩበትና የሚታሰሩበት ገዥ ስርዓት ወዳላት ሀገራችን መጥተዋልና አቋማችንን ማሳወቅ ተገቢ ሆኖ አግኝተነዋል። ጉባኤው በሀገራችን መካሄዱ ላይ ምንም ተቃውሞ ባይኖረንም በገዥዎች የሚጨቆነው የአፍሪካ ሚዲያ ላይ ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ ግን የለንም። ምክንያቱም ለሚዲያዎች ነፃና ገለልተኛ አለመሆን አምባገነን ገዥዎችና ስርዓታቸው ቀን ከሌሊት ነፃ ሚዲያና ነፃ አስተሳሰብ እንዳይኖር ስለሚሰሩ ነው።
ስለዚህ ሚዲያውን የሚጨቁኑትና የሀሳብ ልዕልና እንዳይኖረው የሚያደርጉት ኢትዮጵያን ጨምሮ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት አምባገነን መሪዎች መሆናቸውን በስብሰባው ላይ የታደሙ የአፍሪካ መሪዎች ልብ እንዲሉ እንፈልጋለን። ፓርቲያችን አንድነት አጥብቆ እንደሚያምነው የአፍሪካ የሚዲያ ባለሙያዎች የሚዲያ ነፃነት የሚረጋገጠው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ሲረጋገጥ መሆኑን አምነው በቅድሚያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይገነባ አንቀው በመያዝ የህዝቡንና የሚዲያውን ነፃነት ጨፍላቂ የሆኑትን አምባገነን ስርዓቶች መታገል እንደሚገባ፤ ለዚህም ሚዲያው አበክሮ እንዲሰራ ጥሪ እናቀርባለን። በአምባገነናዊ ስርዓት ውስጥም ነፃ ሚዲያ መመስረት የማይታሰብ መሆኑን ፓርቲያችን ይገነዘባል። ወደ ሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ስንመጣም ስርዓቱ ለነፃ ሚዲያ ማበብ ቁርጠኝነት ያነሰው በመሆኑ ከማስመሰል ባለፈና ለስርዓቱ አጨብጫቢ የሆኑ ሚዲያዎችን ከመቀፍቀፍ በዘለለ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓቱ መጎልበት አስተዋፅኦ የሚያደርጉ ተች ሚዲያዎችን ሊፈጥር አልቻለም።
ይልቁንም በተቃራኒው በግል ተነሳሽነት ለመንቀሳቀስ የሚሞክሩትን ከማጥፋትና ጋዜጠኞችን ከማሰር ቦዝኖ አያውቅም። በተለይም ነፃው ፕሬስ በመንግስት የተቀነባበረና ከፍተኛ ጥቃት ሰለባ ነው። ስለዚህ በሀገራችን የተገኙ የአፍሪካ የሚዲያ ባለቤቶች የኢትዮጵያ መንግስት ለሚዲያ ነፃነት መረጋገጥ እንዲሰራ ተጨባጩን የሀገራችንን የሚዲያ እድገት እንዲመረምሩ ጥሪ
እናስተላልፋለን። በመጨረሻም በኢትዮጵያችን ያለው አምባገነን
ስርዓት በርካታ ጋዜጠኞችን እስር ቤት አጉሯል። ጠንካራ የግል ጋዜጦችንም ዘግቷል። ለክቡራን የአፍሪካ ሚዲያ ባለቤቶችና አዘጋጅ ለሆነው አካል ጥያቄ እናቀርባለን።
በሀገራችን ሃሳባቸውን በነፃነት ስለገለፁ ብቻ ለእስር የተዳረጉት
እንዲፈቱና የሚዲያ ባለሙያዎችም ይህንን በአካል ቃሊቲ በመሄድ ከእስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ የሱፍ ጌታቸውና ዝዋይ የሚገኘውን ውብሸት ታየን በማነጋገር እንዲያረጋግጡ ጥሪ እናቀርባለን። እግረ መንገዳችሁንም በኢህአዴግ ስርዓት ውስጥ ነፃ ፕሬስ ምን ማለት እንደሆነ ትረዳላችሁ፤ ስንቶቹ ሀገራቸውን ጥለው እንደተሰደዱ ታውቃላችሁ።
ክብርና ነፃነት ለነፃ ሚዲያና ጋዜጠኞች!!!
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ
ጥቅምት 29 ቀን 2006 ዓ.ም
አዲስ አባባ
No comments:
Post a Comment