-በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ኮምፒዩተሮች ላይ ምርመራ ያካሂዳል-ብሔራዊ የኮምፒዩተር አደጋ ምላሽ መስጫ ማዕከል ይኖረዋልባለፉት በርካታ ዓመታት በሥራ ላይ የሚገኘውን የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ከፍተኛ ኃላፊነትና ጉልበት የሚሰጥና በድጋሚ እንዲቋቋም የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ፡፡በፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች ተጨማሪ ውይይት እየተደረገበት የሚገኘው ይህ ረቂቅ አዋጅ፣ በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ከፀደቀ በኋላ ኤጀንሲው በድጋሚ የሚዋቀር ሲሆን የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማትን፣ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ ኃይል መረብን፣ በግንባታ ላይ የሚገኘውን አገራዊ የባቡር ትራንስፖርት መረብን፣ ወታደራዊ የኮምፒዩተር ሥርዓትንና ሌሎች ኮምፒዩተራይዝድ የሆኑ መሠረተ ልማቶችን በኮምፒዩተር አማካይነት ከሚቃጡ ጥቃቶች የመጠበቅ ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡የረቂቅ አዋጁ አባሪ ሰነድ ሆኖ የቀረበው ማብራሪያ እንደሚያስረዳው፣ በአገሪቱ በሚታየው የኢኮኖሚ ዕድገት ሳቢያ በርካታ የአገሪቱ እንቅስቃሴዎችና አገልግሎቶች የኮምፒዩተርና የኮምፒዩተር መረብ ጥገኛ መሆናቸው፣ እንዲሁም የዓለም ነባራዊ ሁኔታ አዋጁ እንዲዘጋጅና ኤጀንሲውን በድጋሚ እንዲቋቋም ለማድረግ ምክንያቶች ናቸው፡፡ የአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የባቡር፣ የአቪዬሽን፣ የውኃ አቅርቦትና ሌሎች ኮምፒዩተራይዝድ በሆኑ ሥርዓቶች እየተመሩ መሆኑን በአብነት ያነሳል፡፡ በምሳሌነትም የአገሪቱ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ማመንጫ፣ ማስፋፊያና ማሠራጫ ሥርዓቱ በኮምፒዩተራይዝድ ሥርዓት የሚመራ በመሆኑ፣ በዚህ ሥርዓት ላይ የሚደረግ የኮምፒዩተር ጥቃት የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት ከማቋረጡም በተጨማሪ፣ ኃይል አመንጪ ግድቦች ውስጥ የተጠራቀመ ውኃ ፍሰቱ እንዲዛባ በማድረግ መሠረተ ልማቱ ሙሉ በሙሉ እንዲወድም ሊያደርግ እንደሚችል ይገልጻል፡፡በተመሳሳይ በአገሪቱ እየተገነባ ያለው የባቡር ትራንስፖርት በኮምፒዩተር ሥርዓት ቁጥጥር የሚደረግበት በመሆኑ፣ በዚህ ሥርዓት ላይ ጥቃት በማድረስ ባቡሮች ከመስመራቸው ውጪ እንዲንቀሳቀሱና አደጋ እንዲደርስባቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል በማለት ያስረዳል፡፡በመሆኑም ኤጀንሲውን በድጋሚ በማዋቀር ሰፊ የደኅንነት ኃላፊነቶችን እንዲወጣ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ይህንን ኃላፊነት ኤጀንሲው እንዲወጣ በኤጀንሲው ሥር ብሔራዊ የኮምፒዩተር ድንገተኛ አደጋ ምላሽ መስጫ ማዕከል እንዲቋቋም የሚያስችል አንቀጽ በረቂቅ አዋጁ ተካቷል፡፡ ማዕከሉ ሊደርሱ የሚችሉ ጥቃቶችን ለመለየት፣ ጥቃቶችን ቀድሞ በመተንተን ለማወቅ፣ ጥቃት ሲከሰት በብቃት መግታት ወይም መጠነ ሰፊ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጠርና ሌሎችንም ተግባራት የሚያከናውን ይሆናል፡፡
ኤጀንሲው ይህንን ኃላፊነቱን በአግባቡ ለመወጣት እንዲያስችለው የደኅንነት ኦዲት ማድረግ የሚያስችል ሥልጣን በረቂቁ ተካቷል፡፡ የደኅንነት ኦዲት ማለት ኮምፒዩተርን መሠረት ባደረገ ቁልፍ መሠረተ ልማት ላይ ተጋላጭነትን ለማወቅ የዘልቆ ገብ ፍተሻ ተግባራትን ማከናወንና አገራዊ የኢንፎርሜሽን ፖሊሲና ስታንዳርድን መሠረት በማድረግ፣ የተቋማቱን የኢንፎርሜሽን ደኅንነት ሥርዓት በመገምገም የእርምት ዕርምጃ እንዲወስዱ ማድረግ የሚል ትርጓሜ በረቂቁ ተሰጥቶታል፡፡ኢንፎርሜሽን (መረጃን) መሠረት ባደረጉ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ወይም ሥርዓቶች ላይ እንዲሁም በዜጎች ሥነ ልቦና ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበርና የኤሌክትሮማግኔቲክ ጥቃቶችን ለመከላከል አስፈላጊ አፀፋዊ ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት ይኖረዋል፡፡ የሳይበርና የኤሌክትሮማግኔቲክ ጥቃቶች የሚባሉት የኢንተርኔት ሬዲዮ ወይም ቴሌቪዥን፣ የቴሌቪዥንና የሬዲዮ አገልግሎቶች፣ የማኅበራዊ ሚዲያዎች (ማለትም ፌስቡክን የመሳሰሉ)፣ ዌብሳይቶች፣ ብሎጐችንና የመሳሰሉትን በመጠቀም የሚተላለፍ መሆኑን የአዋጁ ማብራሪያ ያትታል፡፡
በእነዚህ የመገናኛ አውታሮች የሚተላለፉ መረጃዎች ለማኅበራዊ፣ ለፖለቲካዊና ለኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ያላቸው ፋይዳ ግዙፍ ቢሆንም በተቃራኒው ለጦርነት ቅስቀሳ፣ የአገርን ገጽታ ለማጉደፍ፣ ፀረ ልማት ፕሮፓጋንዳዎችንና ኢኮኖሚያዊ ትንበያ (ስፔኩሌሽን) ማሠራጨት መጠቀሚያ ሊሆኑ እንደሚችሉ ማብራሪያው ይገልጻል፡፡ በመሆኑም የአዋጁን መፅደቅ ተከትሎ የተጠቀሱትን ጉዳት ያላቸውን መረጃዎች ኤጀንሲው የማክሸፍ ሕጋዊ ሥልጣን አለው፡፡
ኢንፎርሜሽንና ኮምፒዩተርን መሠረት ያደረጉ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ደኅንነትን ለማረጋገጥ ሲባል ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማውጣት የጥቃት ሰለባ ወይም መነሻ ናቸው ተብለው በተጠረጠሩ ኮምፒዩተሮች ወይም መሠረተ ልማቶች ላይ አስፈላጊውን ምርመራ ማካሄድ፣ ሌላው በረቂቅ አዋጁ የተካተተ የኤጀንሲው የወደፊት ኃላፊነት ነው፡፡
No comments:
Post a Comment