Tuesday, November 19, 2013

በዜጎች ሰቆቃ ፕሮፓጋንዳ ለምን? በፕሮፓጋንዳ የተለከፈ ፓርቲና መንግስት በኢትዮጵያ ሀገራችን ፓርቲና መንግሰት መለያየት አሰቸጋሪ እንደሆነ ከተረዳን ውለን አድረናል፡፡ ለዚህም ነው መንግሰት የሚባለው አካል ሁል ጊዜ ግዴታውን በሚወጣበት ጊዜ አብሮ ፕሮፓጋዳ የሚጨምርበት፡፡

ግርማ ሠይፉ ማሩ 
በኢትዮጵያ ሀገራችን ፓርቲና መንግሰት መለያየት አሰቸጋሪ እንደሆነ ከተረዳን ውለን አድረናል፡፡ ለዚህም ነው
መንግሰት የሚባለው አካል ሁል ጊዜ ግዴታውን በሚወጣበት ጊዜ አብሮ ፕሮፓጋዳ የሚጨምርበት፡፡ ሰሞኑን ግን
ቅጥ ያጣ የፕሮፓጋዳ ርዕስ ሆኖ ያገኙሁት ደግሞ በሳውዲ ሀረቢያ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ላይ በደረሰው ግፍ፣
ሰቃይ፣ መከራና ሞት ጎን ለጎን የኢትዮጵያ መንግሰት ችግሩን ለመፍታት ከሚያደርገው ጥረት የገዘፈ የፕሮፓጋንዳ
ዘመቻና ነውረኝነት የተሞላበት ዘገባ ነው፡፡ 
ማፈሪያው የኢትዮጵያ ቴሌቪዝን እና ፕሮግራም ሰሪዎቹ (አሁን ደግሞ ዜና አንባቢዎቹ ጭምር ድምፀታቸው ሲሰማ የድል ብስራት የሚነግሩ ነው የሚመስሉት) በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ተገኝተው የሚያስተላልፉት ዘገባ ተጎጂዎቹ ህገ ወጥ ስለመሆናቸው እና በመንግሰት በጎ አድረጊነት ወደ ሀገራቸው መመለሳቸውን የሚያብስሩ ናቸው፡፡ ይህን ፅሁፍ ሳዘጋጅ በስቃይ ላይ ከሚገኙት ኢትዮጵያዊያን አሰር ከመቶ እንኳን የሚሆኑት ወደ ሀገራቸው መግባት ባልቻሉበት ሁኔታ ዕድል አግኝተው መመለስ የቻሉት ዜጎች የመንግሰትን ሰኬታማ እንቅስቃሴና ችሮታ እንዲያወድሱ እየተደረገ ነው የሚገኘው፡፡ የሚያሳዝነው ከሳምንት በላይ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው በስቃይ ላይ የሚገኙ ዜጎችን እሮሮ እየሰማን ባለንበት ወቅት በኤምባሲው ጥረት በአንድ ቀን ያለ ምንም ችግር መግባቱን የሚገልፅ ተጎጂ ማቅረብ ችግሩን ለማቅለልም ሆነ የኢትዮጵያ ኤምባሲን ትጋት ለማሳየት አይረዳም፡፡ ይልቁንም ይህ ተፈናቃይ የተሰራው ፍሪዝ ፀጉሩ ሳይበላሽ በአንድ ቀን ሊመለስ ከቻለ በእድል ወይም ከሹሞች የአንዱ ዘመድ ሆኖ መሆን ይኖርበታል፡፡ በጣም የሚያስገርመው ይህ ሚዲያ የኢትዮጵያ መሆኑን የሚያጠራጥር ነው፡፡ ይህ ፕሮግራም የሚቀርበው በአማርኛ ባይሆን ዝግጅቱ ባለቤት የሳውዲ የኮሚኒኬሽን ሚኒስትር መስሪያ ቤት ነው የሚመስለው፡፡ ዜናው ሲጀምር “በህገወጥ መንገድ ሳውዲ ገብተው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ….” ብሎ ይጀምራል፤ አነዚህን ዜጎች ወደ ህገወጥ ስደት የደራጋቸው መቼም ደርግ ወይም ንጉሡ አይደለም፡፡ ለእነዚህ ወጣቶች በማንኛውም ሁኔታ ሀገራቸውን ለቀው እንዲሄዱ በቀጥታም በተዘዋዋሪም የሚገፋው ሀገሪቱን በመምራት ላይ ያለው መንግሰት እና መንግሰት የሚከተለውን ፖሊሲ የቀረፀው ፓርቲ ነው፡፡ ደርሶ ግፍ የደረሰባቸውን ዜጎች ጥፋተኛ ለማድረግ የሚደረግ ጥረት በታሪክ ፊት ተጠያቂ ያደርጋል እንጂ አንድም ውሃ የሚቋጥር ውጤት አያመጣም፡፡ ሌላው አስገራሚ ነገር መንግሰት ዜጎች ሰሜታቸውን በሰላማዊ መንገድ ሊገልፁ የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት ሲገባው፤ ይህ ለማድረግ በሌሎች አነሳሽነት ጥያቄ ሲቀርብለት ሰበብ ፈጥሮ ማገዱን ብሎም ህገወጥ እርምጃ መውሰዱ አሳፋሪ ነው፡፡ መንግሰት የህዝብን ድምፅ እንዲሰማ ማድረግ ለዲፕሎማሲው ስራ የሚያግዘው ጠቃሚ ግብዓት አድርጎ ከመውሰድ ይልቅ፣ ችግር የለም የኔን ህዝብ በእኔው መንገድ (በሳውዲው መንገድም ጭምር) ጭጭ አደርገዋለሁ በሚል ትዕቢት እየሄደ ይመስላል፡፡ የህዝብን ሰሜት ለማፈን መንግሰት ምክንያቱ ምን ይሆን? እንቆቅልሽ ነው የሆነብኝም፡፡ የሚያውቅ ካለ ይህን እንቆቅልሽ ይፈታልኝ ዘንድ በማክበር እጠይቃለሁ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶክትር ቴዎድሮስ አድሃኖም በሁኔታው ብስጭትም ንዴትም እንደገባቸው በአንድ ምረቃ ስነስርዓት ገልፀዋል፤ ሌሎች ዜጎች ይህን የተሰማቸውን ብስጭት፣ የኢትዮጵያዊያን ክብር መደፈር የሚገልፁበትን መንገድ መዝጋት ይፋዊ የሆነ የአንባገነንት ተግባር ካልሆነ ምንም ሊሆን አይችልም፡፡ የኛ ይበቃል እናንተ ምን ቤት ናችሁ ነው ነገሩ? በዚህ አጋጣሚ አንድ አሰገራሚ ነገር ላካፍላችሁ አንድ ጎምቱ ሊባሉ የሚችሉ የህወሃት አባል፣ የሳውዲ ህዝብ ሳይሆን የፖሊስ ኃይሉ ነው እንዲህ የሚያደርገው፣ ይህ ሃይል ደግሞ ሰብዓዊ መብት በማክበር ብዙ አይታወቅም ብለው ትንተና ሰጡኝ፣ የሚገርመው በዚሁ ዕለት በሀገራችን ያለው የፖሊስ ሀይል ይህን ለማውገዝ የወጡ ዜጎችን ሲደበድብ ነበር የዋለው፡፡ ሌላው ጎምቱ የብአዴን አባል ደግሞ ችግሩ ከተፈጠረበት ምክንያት አንዱ በሳውዲ ሀረብያ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ክልክል ነው፡፡ ስለዚህ ችግሩ የኛው ዜጎች ስላማዊ ሰልፍ ለማድግ በመሞከራቸው የመጣ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ህገወጦች በህገወጥ መንገድ ሰው ሀገር መግባታቸው ሳያንስ ሰልፍ ለማድረግ መሞከራቸውጥፋት ነው የሚል እንደምታ ያለው ማብራሪያ ቸረውኛል፡፡ ሌሎቹን አስተያየቶች ለጊዜው እንተዋቸው እና ባጠቃላይ በኢህአዴግ መንደር ያለው መግባባት አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ህዝቡን ስለ ህገወጥ ሰደት ለማሰተማር ጥሩ አጋጣሚ ተደርጎ መወሰድ እንዳለበት ነው፡፡ በዜጎች ላይ የደረሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ እንግልት፣ ስቃይና ሞት እንደ መልካም አጋጣሚ የተወሰደ ይመስላል፡፡ ጎበዝ መሪዎቻችን የነዚህ ሰዎቸ ድምር መሆኑን መረዳት ስፈልጋል፡፡ ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ በፋክት መፅሔት ላይ “አመል ካልሆነ በቀር … “ ብሎ ያስነበበን መጣጥፍ ትዝ አለኝ ኢህአዴግ አመል ካልሆነ በስተቀር በዚህ ችግር፣ ሰቆቃና ሞት ፕሮፓጋንዳ ከመስራት ይልቅ በውጭም በሀገር ውሰጥም የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያኖችን ሊያስተባብረበት እና ዜጎቹን ሊታደግ የሚችልበትን መንገድ መጠቀም ለምን ይሳነዋል፡፡ ክፉ አመል ነው፡፡ በእኔ እምነት አሁንም መንግሰት ዜጎችን ለስደት የሚዳርገውን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታ ለማሻሻል የሚያስችል አቅምም ብቃትም የሌለው ከመሆኑ በላይ ችግሩን በቅጡ የተረዳው አይመስልም፡፡ በሀገር ውስጥ ላሉት ሰራ መፍጠር ተቸግሮ የሚባዝን መንግሰት አሁን ደግሞ ዶላር ልክው ኮኖዶሚኒየም እየገዙ ይደጉሙኛል የሚላቸው ምስኪን ዜጎች ባልተጠበቀ ሁኔታ ለረጅም ዓመት የደከሙበትን ጥሪት ጥለው በሃያና ሰላሣ ሺ አዲስ ሰራ ፈላጊዎች እየመጡ መሆኑን ነው፡፡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ መሆኑ ነው፡፡ የሳውዲ መንግሰት ህጋዊ ፎርማሊቲ እንዲያሟሉ በሰጠው ጊዜ ገደብ አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ ይህን ለማድረግ ዳተኛ የነበረው የኤምባሲ ሃላፊዎችና መንግሰት ተጠያቂነታችሁ ተመዝግቦ እንደሚቀመጥ መዝንጋት የለባችሁም፡፡ አሁንም ቢሆን መንግሰት ከፕሮፓጋንዳው ዘመቻ ረገብ በማለት የአካል ጉዳት ለደረሰባቸው፣ ህይወታቸው ላለፉ ዜጎች ተገቢው ካሳ ሊገኝ የሚችልበትን መንገድ አጥብቆ መያዝ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ዜጎችን ህገ ወጥ እያሉ ስቃይና ሞት የጥፋታችሁ ዋጋ ነው የሚለው ዜና መቆምይኖርበታል፡፡ ሃምሳ ሚሊዮን ለሃያ ሺ ተጎጂ ለማቋቋሚያ ቀርቶ ሀገር ውስጥ ለማምጣት አይበቃም፡፡ ይህም የማሳሳቻ ፕሮፓጋንዳው አካል ነው፡፡
ክብር ለኢትዮጵያ እና ለዜጎቿ!!!!
ethiomedia

No comments:

Post a Comment