Saturday, November 23, 2013

[የሳዑዲ ጉዳይ]፦ የዮሴፍን ውለታ የማያውቅ ሌላ ፈርኦን ተነሳ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ። አሜን። ቅዱሱ መጽሐፍ የሃይማኖት ብቻ መጽሐፍ ሳይሆን የታሪክም ምስክር ነው። ዮሴፍ በተሰደደበት በምድረ ግብጽ ኑሮውን ብቻ እያሸነፈ የኖረ አልነበረም። የግብጽ አስተዳደር በመልካምና ፍትሃዊ በሆነ የገንዘብ አከፋፈልና በንብረት አጠባበቅ ያገለገለ ለግብጽ ህዝብና መንግስት ባለውለታ ነበር። ህዝበ እስራኤል በችግር ምክንያት ተሰደው በመልካም ጸባይ ኑሯቸውን እያሸነፉ ምድረ ግብጽን እያለሙ፤ እግዚአብሔርን እያመለኩ፤ ሀገራቸውንም እያሰቡ፤ የሚመለሱበትንም ቀን በተስፋ እየጠበቁ ይኖሩ ነበር።

 ከመልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ገብረሚካኤል

(በሚኒሶታ የቅዱስ ዑራኤል ቤ/ክ አስተዳዳሪ)
aba
ስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ። አሜን።
ቅዱሱ መጽሐፍ የሃይማኖት ብቻ መጽሐፍ ሳይሆን የታሪክም ምስክር ነው። ዮሴፍ በተሰደደበት በምድረ ግብጽ ኑሮውን ብቻ እያሸነፈ የኖረ አልነበረም። የግብጽ አስተዳደር በመልካምና ፍትሃዊ በሆነ የገንዘብ አከፋፈልና በንብረት አጠባበቅ ያገለገለ ለግብጽ ህዝብና መንግስት ባለውለታ ነበር። ህዝበ እስራኤል በችግር ምክንያት ተሰደው በመልካም ጸባይ ኑሯቸውን እያሸነፉ ምድረ ግብጽን እያለሙ፤ እግዚአብሔርን እያመለኩ፤ ሀገራቸውንም እያሰቡ፤ የሚመለሱበትንም ቀን በተስፋ እየጠበቁ ይኖሩ ነበር። በሁዋላ ግን የዮሴፍን ውለታ የማያውቅ ሌላ ፈርኦን ተነሳ። በህዝበ እስራኤል ላይ ግፍና መከራ ፤ ሰቆቃና ሞት አጸናባቸው። እግዚአብርሔርም ካህኑን አሮንንና መስፍኑን ሙሴን አስነሳ፤ ህዝቡንም ይዘው ወጡ ይላይ ቅዱሱ መጽሐፍ። ቅድስቲቷ ሀገር ኢትዮጵያ ለዜጎቿና ለሌላው ዓለም ባለውለታ ናት። 
ይህን ውለታዋን የማያውቁ ሌላ ፈርኦኖች ተነሱ። ኢትዮጵያ ባለብዙ ታሪክ በልጆቿ ተከብራ፤ በእግዚአብሔር ተጠብቃ የቆየች ምስረታዋ ከጻድቁ ከኖህ ልጅ ጀምሮ የተመሰረተች የሰው ልጅም መገኛ፤ በስነ መንግስት አመሰራረትም ከ 3000 ዓመት ታሪክ በላይ ያላት፤ በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔርን አምና ሥርዓተ አምልኮ የፈቸመች፤ በሐዲስ ኪዳን ልደተ ክርስቶስን ቀድማ ያመነች፤ ወንጌልን የተቀበለች፤ ጥምቀተ ክርስትናን በ 34 ዓ/ም የተጠመቀች ራሷን ችላ የኖረች ነጻ ሀገር ናት። በሀይማኖት ምክንያት ነጻነት ያጡትን ምዕራባውያን መነኮሳትን (9ኙን ቅዱሳን) የተቀበለች በክርስትና የማያምኑትንም እምነታቸውን አክብራ፤ ነጻነታቸውን ጠብቃ ያስተናገደች ቅድስት ሀገር ኢትዮጲያ። ዳር ድንበሯ ተጠብቆ የቆየ አሁን ግን በመንፈሳዊውም ይሁን በስጋዊ መልካም መሪ ያጣች፤ ድንበሯ የተጣሰ፤ ባህር በሯን የተወረሰች፤ መሬቷ የተሸጠ ሆነችና አረፈች። አንድ ሀገር እንደ ሀገር ለመቀጠል ከፈለገ ሊንከባከባቸው የሚገባው ዘላቂ እና ቋሚ ጥቅሞች ሊኖሩት ያስፈልጋል። ከእነዚህ አይነተኛው ማንነቱንና ቋሚ ሉዓላዊነቱን የሚያረጋግጥበት ዳር ድንበር ነው። ይህ ዳር ድንበርና በእርሱ ውስጥ የተካለሉት ሀብቶች የአንድ ትውልድ ወይንም በአንድ ወቅት የወጣ የአመራር ቡድን ንብረት አይደሉም።
በዚህም ላይ ለመወሰን ማንም ቡድን መብትም ሆነ ስልጣን የለውም። እነዚህን ዘላቂ ጥቅሞች በደረስንበት ጊዜ የመጠቀም እንጂ አሳልፈን የመሸጥም ሆነ የመስጠት መብት የለንም። ከወንጀሉ ሁሉ የከፋው ወንጀል የራሱን ዘመን ብቻ ሳይሆን የሚመጣውን ትውልድ እድል ማበላሸት ነው። ስለዚህም ዛሬ ባለንበት ሰዓት ባልጠግብ ባይ ኢግብረገባውያን ባለስልጣናት ክፉ አስተዳደር ምክንያት በየአህጉሩ እየተሰደደ የሚገኘው ወገናችን በብዙ መከራና ስቃይ ውስጥ ይገኛል። አንዳንዶቹ በተሻለ ዓለም ደህና ሲኖሩ እንደ ፈርኦን በመሰሉ በሚመራ ሀገር ያሉ ደግሞ ግፍ መከራ ጸንቶባቸው ሲሰቃዩ ሲሞቱ እያየ እየሰማ ዝም የሚል መሪ ከቶውንም ታይቶ አይታወቅም። ምንም እንኳን በሦስተኛው ዓለም የሚኖር ማንኛውም ሰው የስደተኛ ኑሮ ነው የሚኖሮው ምክንያቱም ከላይ እስከታች ከአንደኛው ዓለም ምጽዋት ጠባቂ ስለሆነ። ስለዚህ ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ሆይ መለያየትን አስወግደን ከመራራቅ መቀራረብ፤ ከመናናቅ መከባበር ያስፈልጋልና በአንድነት ሆነን የተናቀውን ማንነታችንን ወደ ቀደመ ክብራችን እንመልስ። እግዚአብሔር አምላካችን የሞቱትን ነፍሳቸውን ይማርልን፤ የቆሰሉትን ይፈውስልን፣ የተጨነቁትን ያጽናናልን፣ የተሰደዱትን ሁሉ በክብር ወደ ሀገራቸው ይመልስልን። የኢትዮጵያን ውለታ የማያውቅ ሌላ ፈርኦን ተነሳ ከመባል እግዚአብሔር ይጠብቀን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፤ አሜሪካንን ይጠብቅ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር

No comments:

Post a Comment