Friday, November 8, 2013

በመንግስት ቸልተኝነት በስደት ላይ ባሉ ዜጎች እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ በአስቸኳይ ይቁም!!!






























በመንግስት ቸልተኝነት በስደት ላይ ባሉ ዜጎች እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ በአስቸኳይ ይቁም!!! በሃገራችን በኢህአዴግ አገዛዝ ዘመን ዜጎች በሚደርስባቸው ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች ምክንያት በህጋዊና ህጋዊ ባልሆኑ መንገዶች ከሃገራቸው በብዛት ተሰደዋል፡፡ ከእነዚህ ከሚሰደዱ ዜጎች መካካልም ብዙውን ቁጥር የሚይዙት ወገኖች በመንገዳቸው ብዙ አሰቃቂና እስከ ሞት የሚደርስ አደጋ የሚገጥማቸው ሲሆን ይህንን አደጋ ተቋቁመው ካሰቡበት ቦታ የደረሱትም ቢሆኑ በባእድ ሃገር ዜጎችና መንግስታት በሚደርስባቸው በደል የኢህአዴግ መንግስት ከዜጎቹ ጎን በመቆም ስቃያቸውና በደላቸው እንዲቆም ከመጠየቅና አጋር ከመሆን ይልቅ በሃገር ውስጥ ባሉ ሚዲያዎች አማካኝነት ‹ሃገሪቱ በልማት እያደገች ባለችበትና ስራ አጥነት እየተቀረፈ ባለበት ወቅት› ሃገር ጥለው መሰደዳቸው ስህተት መሆኑን እየጠቀሰ በዜጎች ስቃይና ሞት እየቀለደ ይገኛል፡፡ ፓርቲያችን ሰማያዊ እነዚህ ዜጎች ከሃገር የሚሰደዱት በሃገሪቷ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፍትህ ባለመኖሩና የመልካም አስተዳደር ችግር አስከፊ ደረጃ ላይ በመድረሱ እንደሆነ ያምናል፡፡በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫና ምክንያትም በየበረሃው በኮንቴይነር ታሽገው የሚሞቱ፣በባእዳን ዜጎች ኩላሊታቸው እየተሸጠ የሚገኙ፣በባህር ለማቋረጥ ሲሞክሩ በመንገድ ላይ የቀሩና በተለይም ሰሞኑን ከተለያዩ ምንጮች እንደሚሰማው በሳኡዲ አረቢያ ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰባቸው የሚገኙ ሴት እህቶቻችን ጉዳይ እንደሚያሳስበው በአፅንኦት ይገልፃል፡፡በመሆኑም 1.በአሁኑ ወቅት በሳኡዲ አረቢያ ስቃይ እየደረሰባቸው ያሉ ዜጎቻችንን ህይወት ለመታደግ መንግስት ከሳኡዲ አረቢያ መንግስት ጋር በመወያየት አስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጥ 2.የሳኡዲ ዐረቢያ መንግስትም በዜጎቻችን ላይ እየደረሰ ያለው በደል የሰብአዊ መብት ጥሰት መሆኑን በመረዳት ግፍና ስቃዩ በአስቸኳይ እንዲቆም እንዲያደርግ 3.እነዚህን ዜጎች ለስደትና ለስቃይ የሚዳርጉና የችግሩ መንስኤ የሆኑ ድርጅቶችና ግለሰቦች ለፍርድ እንዲቀርቡና ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድባቸው 4.ዜጎች የሚሰደዱበትን ምክንያት በጥልቅ በመመርመርና በማጥናት አስከፊውን ስደት ለማቆም መንግስት የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲያደርግ 5.መንግስት ዜጎች የሚሰደዱበትን ምክንያትና የሚደርስባቸውን ስቃይ ከተራ ፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በዘለለ ለህዝቡ ትክክለኛ መረጃ እንዲሰጥና በዜጎች ስቃይ ላይ መሳለቁንና ማቃለሉን እንዲያቆም ይጠይቃል፡፡ ፓርቲያችን ሰማያዊ በቀጣይነት መረጃዎችንና ጥናቶችን በማሰባሰብ ችግሩን በዘላቂነት የሚፈታ የመፍትሄ ሀሳብ ለማምጣት ጥረት የሚያደርግና ምንጊዜም ከግፉአን ወገኖቻችን ጎን የሚቆም መሆኑን እየገለጸ ዜጎቻችንን ከስቃይ ለማዳን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ሲቪክ ተቋማት፣የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች፣ፖለቲካ ፓርቲዎችና አለም አቀፍ ማህበረሰቡ ከጎናችን እንዲቆሙ በአፅንኦት ይጠይቃል፡፡ ጥቅምት29 2006ዓ/ም

No comments:

Post a Comment