
ትናንት በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ የደረሰው የፈንጂ ፍንዳታ በሁለት ሶማሊያውያን አሸባሪዎች የተፈፀመ መሆኑን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል አሰፋ አብዩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስረዱት ፥ በክፍለ ከተማው ወረዳ 01 ቀበሌ 01 በተለምዶ ሩዋንዳ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ በአንድ የመኖሪያ ቤት ውስጥ ነው ፍንዳታው የደረሰው ።
ፖሊስ ፍንዳታው ፈንጂ መሆኑንና ፥ በጥቅም ላይ የዋለው ቲ ኤም ቲ የተባለ የፈንጂ ዓይነት መሆኑን እንደደረሰበት ገልፀዋል ።
ፍንዳታውንም ሁለት ሶማሊያውያን ማቀነባበራቸውን ፖሊስ እንዳረጋገጠና ግለሰቦቹ የአሸባሪ ቡድኑ አልሸባብ አባል መሆናቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እንዳሉም ነው ጀነራል አሰፋ አብዩ ያስረዱት ።
ከሁለቱ አሸባሪዎች መካከል አንደኛው ወገቡ ላይ የታጠቀና ለአጥፍቶ ጠፊ ተግባር የተዘጋጀ መሆኑን የሚያሳይ ነው ።
ሌላኛው አሸባሪ በሻንጣ ፈንጂ የያዘ ሲሆን ፥ የፈነዳውም ፈንጂ በሻንጣው ውስጥ የነበረ መሆኑን ነው ጀነራል አሰፋ ያስረዱት ።
ለአጥፍቶ ጠፊ ተግባር ሲዘጋጅ የነበረው ግለሰብ የታጠቀው ፈንጂ ግን እንዳልፈነዳ አመልክተዋል ።
አሸባሪዎቹ በአጠቃላይ ሶስት ፈንጂዎችንም ይዘው ነበር ።
አሸባሪዎቹ ህዝብ ባለበት ስፍራ አደጋ ለማድረስ ተከራይተው በነበሩበት ቤት ውስጥ ሲዘጋጁ ፍንዳታው ደርሷል ብሎ ፖሊስ እንደሚጠረጥር ነው የጠቆሙት ።
ከአሸባሪዎቹ ጋር ፖሊስ የእጅ ቦምቦችንና ሽጉጥ ከነጥይቱ አግኝቷል ።
ከዚህ የምንማረው
ጀነራል አሰፋ አብዩ እንደሚሉት ሶማሊያውያን አሸባሪዎቹ ቤቱን ከተከራዩ ከ22 እስከ 23 ቀን ይሆናቸዋል ።
እስከ ስድስት የሚደርሱ ቤቶችን በከተማዋ የሚያከራዩት የቤቱ ባለቤቶች ስለነዚህ ግለሰቦች ስምን ጨምሮ ማንነታቸውን እንደማያውቁ ነው የተደረሰበት ።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ቤቱንም ሆነ መኪናውን ሲያከራይ ስለተከራዩ ማንነት በቂ እውቀት ይዞ ፥ መታወቂያና ፓስፖርት ተመልክቶ መሆን እንዳለበት ነው ያሳሰቡት ።
የሚያገኛቸውን መረጃዎች በአቅራቢያው ለሚገኝ የፖሊስ ተቋም መስጠት ግዴታው መሆኑን በመረዳትም ፥ ሽብርተኝነተን ከፖሊስ ጎን ሆኖ እንዲከላከል ጥሪ አቀርበዋል ።
No comments:
Post a Comment