ጥቅምት ፰(ስምንት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢህአዴግ ከሙስና መንሰራፋት ጋር በተያያዘ የገጠመውን ፈተና በድል ለመወጣት ሕዝቡን ማሳተፍ እንዳለበትና ያለሕዝቡ ተሳትፎ የሚደረጉ ነገሮች ሁሉ የማይመለስ ጥፋትን ያስከትላሉ ሲሉ አቶ ስብሃት ነጋ ለኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮችን ምክር ለግሰዋል።
የጸረ ሙስና ኮምሽን በሸራተን ሆቴል ያዘጋጀውና በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ሙክታር ከድር እና የፓርላማው አፈጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ በመሩትና ዛሬ በተጠናቀቀው ስብሰባ ላይ የተገኙት የቀድሞ የህወሃት ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ስብሃት ነጋ ፣ በጸረ ሙስና ትግሉ ሕዝብ እንዲካፈል መጀመሪያ መታወቅ አለበት ካሉ በኃላ ” እኛ ህዝቡን አሳውቀነዋል ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
አንድ መ/ቤት 200 ሰራተኞች ቢኖሩት እነዚህ ሰራተኞች በመ/ቤታቸው ጉዳይ የመጨረሻ አዋቂ መሆናቸውን በምሳሌነት የጠቀሱት አቶ ሰብሃት፣ ይህ አዋቂ ሕዝብ እንዳይታዘበን፣ የማይቀበለውን ቃል ተናግረን እንዳናጭበረብረው መጠንቀቅ አለብን ብለዋል፡፡
ኢህአዴግ ይህን አዋቂ ሕዝብ ካልያዘ የሚገጥመው ችግር ለመመለስም የማይቻል ነው ሲሉም አስጠንቅቀዋል፡፡
ሙስና በአሁኑ ወቅት የሌለበት አንድም መንደር የለም የሚሉት አቶ ስብሃት ፣ “ለመሆኑ የሙስናን መንስኤ ታውቁታላችሁ ወይ፣ መንስኤው ፓርቲው ነው፣ ነጋዴው ነው፣ የውጪ ኃይሎች ናቸው?’ ለመሆኑ መጠኑስ ስንት ነው፣ በመቶኛ ስሌት ስንት ነው፣ ስንት ሚሊየን ብር ጠፋ?” ሲሉ እነአቶ ሙክታርን በጥያቄ አፋጠዋል፡፡
መንስኤው ካልታወቀ ቀጣዩ ምንድነው ያሉት አቶ ስብሃት፣ በማታውቀው ነገር ልትታገል፣ ለውጥም ልታመጣ አትችልም በማለት የሙስና ሁኔታ በተጨባጭ ጥናት እንዲደገፍ ጠይቀዋል፡፡
የደረንስንበት የሙስና ሁኔታ ቀላል ስላልሆነ ይህን ጠርገን ንጹህ መሬት መቼ እናገኛለን ሲሉ ጥያቄ አዘል አስተያየታቸውን አክለዋል።
አቶ ሙክታር ከድር የተነሱትን ሃሳቦች በገንቢነቱ እንቀበላለን ካሉ በኃላ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም በመባል የሚታወቀው ፕሮግራም የታሰበውን ያህል ለውጥ አለማምጣቱን በመጥቀስ ይህ ችግር ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነትን ለመዋጋት አዳጋች ሁኔታ መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ስብሰባ ስለሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት አሳሳቢነት ትምህርት ሲሰጡ ከዋሉት ባለስልጣናት መካከል አቶ አባዱላ ገመዳ በአንድ ወቅት በሙስናና ብልሹ አሰራር በፓርቲያቸው ሰብሰባ ላይ ተገምግመው በትርፍነት የያዙትን መኖሪያ ቤት ለኦህዴድ እንደሚያስረክቡ ቃል በመግባታቸው በሕግ ሳይጠየቁ የታለፉ ሲሆን ቤቱን ግን በገቡት ቃል መሰረት ለፓርቲው አለማስረከባቸው ታውቆአል፡፡
እንዲህ ዓይነት በሙስና የተጨማለቁ ባለስልጣናት ስለሙስና አስተማሪና መድረክ መሪ ሆነው መታየታቸው ኢህአዴግ አሁንም ከባድ ችግር ውስጥ ስለመኖሩ ጠቋሚ ነው በማለት አንዳንዶች ለዘጋቢው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ግሎባል ፋይናንሻል ኢንተግሪቲ የተባለው ተቋም በኢትዮጵያ እስከ 3 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ በእየአመቱ ወደ ውጭ ተዘርፎ እንደሚወጣ ከአመት በፊት ባወጣው ሪፖርት መጥቀሱ ይታወቃል።
አቶ ስብሀት ነጋ በአንድ ወቅት ይመሩት የነበረው ኢፈርት የተባለው ግዙፉ የህወሀት ኩባንያ እንዲሁም የህወሀት ባለስልጣኖች እና የመከላከያ ሰራዊት መኮንኖች በአገሪቱ ውስጥ በተንሰራፋው ሙስና ዋነኞቹ ተዋናዮች መሆናቸው በተደጋጋሚ ይዘገባል።
No comments:
Post a Comment