Wednesday, October 2, 2013

የጋምቤላን መሬት የተቀራመተው የህንዱ ካራቱሪ የንግድ ባንክን 62 ሚሊዮን ብር ዕዳን መክፈል ተስኖታል(zehabesha)

 ኩባንያው የሠራተኞች ግብር፣ ጡረታ እንዲሁም 
 የክልሉን የመሬት ግብር አልከፈለም
 ከቀረጥ ነጻ ያስገባቸውን ማሽነሪዎች በማከራየትና በመሸጥ እየተከሰሰ ነው
 ከተረከበው 300 ሺ ሔክታር ያለማው 800 ሔክታር ብቻ ነው
በፋኑኤል ክንፉ

መሠረቱን በጋምቤላ ክልል ያደረገው የህንድ ካራቱሪ አግሮ ፕሮዳክት ኀ/የተ/የግ/ማህበር በተሰጠው መሬት ላይ የልማት ሥራ ማከናወን አለመቻሉን እንዲሁም የባንክ ብድርና የግብር ግዴታዎቹን እየተወጣ አለመሆኑ ተገለፀ።
አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተጠባባቂ የቢዝነስ ዴቭሎፕመንት የስራ ሒደት ባለቤት ስለጉዳዩ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንዳስረዱት “ካራቱሪ ከባንኩ እ.ኤ.አ በዲሴምበር 2011 ወደ 62 ሚሊየን ብር ብድር መውሰድን አስታውሰው ነገር ግን መክፈል በሚገባው ጊዜ ሊከፍል አለመቻሉን፣ ብድሩንም ለማስታመም የተደረጉ ተጨማሪ ጥረቶች ባለመሳካታቸው ጉዳዩ ወደህግ ክፍል መመራቱን አስታውቀዋል። ባንኩ በአሁኑ ወቅት ይህ ብድር የተበላሸ ወይንም መመለስ የማይችል ነው በሚል ጉዳዩን ይዞት ለማስመለስ ወደ ሕጋዊ እርምጃ መግባቱን” ተናግረዋል።
በተያያዘም በግብርናው ዘርፍ ለመሰማራት ከአራት ዓመት በፊት በጋምቤላ ክልል 300ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ተዋውሎ የገባው የህንዱ ኩባንያ ካራቱሪ ባለው ደካማ ማኔጅመንት ምክንያት ሥራውን ማከናወን ባለመቻሉ በአሁኑ ወቅት ትልቅ አደጋ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል። 
አቶ አለምሰገድ አያሌው የኩባንያው የምርት መሳሪዎች ዋና ክፍል ኃላፊና የሠራተኞች ተወካይ ለሰንደቅ ጋዜጣ በስልክ እንደገለጹት ኩባንያው 300ሺ ሄክታር ለማልማት ከግብርና ሚኒስቴር መሬት ተረክቦ የነበረ ቢሆንም ባለፉት አምስት አመታት ከ800 ሄክታር በላይ ለማልማት አልቻለም። 
ግብርና ሚኒስቴር ይህንኑ ደካማ አፈጻጸም በማየት ከአንድ ዓመት በፊት 200ሺ ሄክታር መሬት የነጠቃቸው መሆኑን አቶ አለምሰገድ አስታውሰው ይህንንም ማልማት ባለመቻላቸው በአሁኑ ወቅት በእጃቸው የሚገኘው መሬት 10ሺ ሄክታር ብቻ ነው ብለዋል። ይህም ሆኖ በአሁኑ ወቅት በበቆሎ ሰብል የተሸፈነው 800 ሄክታር ገደማ ብቻ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
ድርጅቱ 150 ያህል ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች እንዳሉት ያስታወሱት አቶ አለምሰገድ የሰራተኞች ደመወዝ ክፍያ እስከ45 ቀናት እንደሚዘገይ፣ ለጡረታና ለግብር ከሰራተኛው የሚሰበሰበው ክፍያ በአግባቡ ለሚመለከተው አካል እንደማይገባ ማረጋገጣቸውን ጠቅሰዋል።
የኩባንያው አመራሮች በውጪ ምንዛሪ የሚያስገቡዋቸውን ዘርና ማዳበሪያ በአገር ውስጥ እንደሚሸጡ፣ ከቀረጥ ነጻ ያስገቡዋቸውን ማሽነሪዎች በማከራየትና ለሶስተኛ ወገን በመሸጥ ያልተገባ ጥቅም እንደሚያጋብሱ ተናግረዋል።
ይህንኑ አቤቱታቸውን ለጋምቤላ ክልል የሚመለከታቸው መ/ቤቶች በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።
የጋምቤላ ክልል ኢንቨስትመንት ቢሮ ዳይሬክተር አቶ ጆን ሾል ስለጉዳዩ ከሰንደቅ ጋዜጣ ተጠይቀው የካራቱሪ የስራ አፈጻጸም እጅግ ደካማ መሆኑን አረጋግጠዋል። ኩባንያው በተጨማሪም ለወረዳ መክፈል ያለበትን የመሬት ግብር ጭምር እንዳልከፈለ የጠቆሙት አቶ ጆን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የተበደረውን ባለመክፈሉ ባንኩ በመያዥነት የያዛቸውን ንብረቶች ወደማስከበር ስራ ፊቱን ማዞሩን ጠቁመዋል።
በቅርቡ ከፌዴራል መንግስት ባለሙያዎች ወደቦታው መጥተው ችግሩን አጥንተው መመለሳቸውን ጠቁመው በቅርቡ ኩባንያውን በተመለከተ የመጨረሻ መፍትሔ ሊገኝ እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የካራቱሪ አግሮ ፕሮዳክት ኃ.የተ.የግ.ማኅበር (ጋምቤላ ኤሊያ አካባቢ) የሥራ ኃላፊዎችን በስልክ አግኝተን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።¾

የዜና ርዕስ ከዘሐበሻ – የዜና ዝርዝር ሰንደቅ ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment