ኒው ኤጅ የተሰኘው የእንግሊዝ ኩባንያ በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኦጋዴን ቤዚን፣ ኤልኩራን በተባለ ሥፍራ የነዳጅ ጉድጓድ ቁፋሮ ጀመረ፡፡ ኒው ኤጅ በኦጋዴን ብሎክ ሰባት፣ ስምንትና አዲጋላ በተባለ ድሬዳዋ አቅራቢያ በሚገኙ የነዳጅ ፍለጋ ቦታዎች አፍሪካ ኦይል ከተሰኘ የካናዳ ኩባንያ ጋር በነዳጅ ፍለጋ ሥራ የተሰማራ ኩባንያ ነው፡፡ ኩባንያው ኤልኩራን በተባለ በሶማሊያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ አካባቢ የነዳጅ ጉድጓ ቁፋሮ ጀምሯል፡፡
ታማኝ የዜና ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኩባንያው የመቆፈሪያ ማሽኑን ተክሎ የቁፋሮ ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ ሳለ የቁፋሮ ባለሙያዎች በማሽኑ ላይ የቴክኒክ ችግር በማግኘታቸው የቁፋሮ ሥራውን ሳይጀምሩ አዘግይተውታል፡፡ ባለሙያዎቹ በማሽኑ ላይ ያገኙትን የቴክኒክ ችግር አስወግደው የቁፋሮ ሥራውን ባለፈው ሳምንት መጀመራቸውን ምንጮች ተናግረዋል፡፡
የሚቆፈረው ጉድጓዱ ጥልቀት 2,800 ሜትር እንደሆነና የቁፋሮውን ሥራ ለማጠናቀቅ ሦስት ወራት ያህል እንደሚፈጅ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከሦስት ወራት በኋላ በጉድጓዱ ውስጥ ነዳጅ መኖርና አለመኖሩን የሚጠቁም የሙከራ ሥራ እንደሚሠራ ታውቋል፡፡
አፍሪካ ኦይል በቅርቡ በድረ ገጹ ይፋ ባደረገው ሪፖርት ከኒው ኤጅ ጋር በመተባበር በኦጋዴን ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ ገልጿል፡፡ አፍሪካ ኦይል በኤልኩራን የነዳጅ ክምችት እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ መገኘቱን ጠቅሶ፣ አሁን በሚቆፈረው ጉድጓድ በአካባቢው የሚገኘውን የነዳጅ ክምችት መጠን ለማወቅ እንደሚቻል አስታውቋል፡፡
‹‹በኤልኩራን ነዳጅ መኖሩ ይታወቃል፡፡ አሁን ዋናው ሥራ የሚሆነው በሚቆፈረው ጉድጉድ ውስጥ የነዳጅ ፍሰት እንዲከሰት በማድረግ በአካባቢው የሚገኘውን የነዳጅ ክምችት መጠን ማወቅ ነው፤›› ብለዋል ምንጮች፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የፔትሮሊየም ባለሙያዎች በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ቴኔኮ የተባለ የአሜሪካ ኩባንያ በኤልኩራን በቆፈረው የመጀመሪያ የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ የተፈጥሮ ዘይት ፍሰት ማግኘቱን አስታውሰው፣ በወቅቱ ኩባንያው ክምችቱ በቂ አይደለም በሚል ትቶት ሄዷል ብለዋል፡፡ አክለውም አሁን ባለው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅመው አፍሪካ ኦይልና ኒው ኤጅ በኤልኩራን ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ክምችት ሊያገኙ እንደሚችሉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡ ዜናው የሪፖርትር ነው።
ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ
No comments:
Post a Comment