(ኢ.ኤም.ኤፍ) በቱርክ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የኢትዮጵያ አዲሱ ፕሬዘዳንት በመሆን በዛሬው እለት ተሹመዋል። ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በትውልድ የወለጋ ሰው ሲሆኑ ቤተሰቦቻቸው የኦነግ ደጋፊ ናችሁ በሚል ከአፄው ዘመን ጀምሮ እስከ አሁን ከፍተኛ ግፍ ያስተናገዱ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የኦህዴድ/ኢህ አዴግ አባል ብቻ ሳይሆን ስራ አስፈጻሚ ሆነው በማገልግል ላይ ይገኛሉ። የሳቸው የወንድም ወይም የእህታቸው ልጅ ወይም በሌሎች ዘመዶቻቸው ላይ ይህ አስተዳደር ያደረሰባቸው መከራ ብዙ ቢሆንም፤ እሳቸው ግን የዚህን መንግስት አስተዳደር ሲደግፉ ቆይተዋል። ከቅርብ ዘመዶቻቸው መካከል አንደኛው ልጅ በ 97 ምርጫ ቢሾፍቱ ላይ ለክልል ምክር ቤት ኦፌዴንን ወክሎ ተወዳድሮ ካሸነፈ በኋላ፤ በዚህ መንግስት የደረሰበትን ግፍ መናገር ይቀፋል!
ጋዜጠኛ ወሰንሰገድ ገብረኪዳን ስለአዲሱ ፕሬዘዳንት ምርጫ ሂደት፤ ከአዲስ አበባ የላከው አጭር ሪፖርት ከዚህ በታች ቀርቧል።
8፡35 የሁለቱ ምክርቤት ስብሰባ ተጀመረ፡፡
8፡ 42 ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የስንብት ንግግር ማድረግ ጀመሩ፡፡ ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመን ሀገራችንን ወደዕድገት ማምራት ችለናል፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት አስፍናል፡፡ ፍትሃዊ የዳኝነት ሥርዓትን ገንብተናል፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊን አዲሲቷን ሥርዓት መገንባት የቻሉ ናቸው ሲሉ አወድሰዋቸዋል፡፡ ከእሳቸው ጋር መሥራት በመቻሌ እኔ ራሴ እድለኛ አድርጌ እቆጥረዋለሁም ብለዋል፡፡
የአደራ መልዕክቶች ሃገራችን በዕድገት ግስጋሴ ላይ የተገኘችው የግል የቡድን መብቶችና ዲሞክራሲ ነፃነቶች ሰጥታ በመንቀሳቀሷ ነው፡፡ ሙስናን መታገል አለባችሁ፡፡ ብዝሃነት የእርስ በርስ መናቆሪያ ሳይሆን የአንድነታችን መሰረት ነው፡፡ የመከባበርና የመቻቻል ባህልን አፍርሰን እንጠቀማለን የሚሉ የውጪ ኃይሎች መኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህ አክራሪነትን መታገል አለባችሁ፡፡ መሠረታዊ ጉዳዮቻችን ላይ የጋራ አመለካከት በመያዝ የታማኝ ተቃዋሚ እንቅስቃሴ በማድረግ የራሳችሁን አስተዋፅኦ እንድታደርጉ እጠይቃለሁ፡፡ 9፡05 ላይ ንግግራቸውን አጠናቀዋል፡፡
9፡07 አፈጉባዔ አባዱላ ገመዳ ዕጩ ፕሬዝዳንት ጠቆሙ፡፡
ዕጩው ፕሬዝዳንት አምባሳደር ሙላቱ ተሾመ ዊርቱ ናቸው፡፡ ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ናቸው፡፡ ካለምንም ተቃውሞ በፕሬዝዳንትነት ተመርጠዋል፡፡ የጠ/ፍ/ቤት ዳኛ አቶ ጌታነህ ተገኔ ቃለመሃላ አስፈፅመዋቸዋል፡፡
9፡20 ተመራጩ ፐሬዝዳንት አምባሳደር ተሾመ ከተሰናባቹ ፕ/ት ሥልጣናቸውን ተረክበዋል፡፡ የሁለቱን ም/ቤት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ጋዜጠኛ ሃብታሙ አሰፋ፤ የዛሬው ፕሬዝዳንትና ትዝታውን እንዲህ በማለት ያጫውተናል።
የዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ፕሬዝዳንት ሆኖ መመረጥ አስራ ሁለት ዓመት ወደ ሁዋላ መለሰኝ። የዛሬ አስራ ሁለት ዓመት በወቅቱ በተሰናባቹ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ምትክ ኢህአዴግ ያው ለሽወዳ የኦሮሞ ብሄር አባል የሆነ ሰው ይሾማል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር። በሁዋላ በስተመጨረሻ በመጣ ግምት የዛሬው ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ በዶ/ር ነጋሶ እንደሚተኩ ከኢህአዴግ ሰፈር በስፋት ተወራ። በጊዜው እሰራበት በነበረው ሩሕ ጋዜጣ የዶ/ር ሙላቱን ፎቶ አስደግፈን ዜና ይዘን ወጣን።እኛ ብቻ ሳይሆን አስቀድሞ ውስጥ ውስጡን ዶ/ር ሙላቱን ለመሾም መታሰቡ የተነገራቸው የስርዓቱን ምስጢር እናቃለን የሚሉት ሳይቀሩ ማንም ያላሰባቸው አቶ ግርማ በቅጽበታዊ ውሳኔ ፕሬዝዳንት እንደሆኑ ግልጽ ነበር። ዘንድሮ ፕሬዝዳንት ይሆናሉ ብሎ ግምት ከተሰጣቸው ብዙዎቹ የሉበትም ።ህወሃት ግን እስከ መቼ ነው ፕሬዝዳንቱን ከኦሮሞ አደረኩ እያለ መቀለዱን የሚያቆመው። ወሬ ወጣብኝ ብሎ ድንገት የዛሬ አስራ ሁለት ዓመት ሀሳቡን የለወጠው ህወሃት (የሚሾምም የሚሽርም ነውና) ዛሬም በይስሙላ ፓርላማ የሌለ ስልጣን ሽግግር መባሉ ትንሽ ፈገግ ያሰኛል። ለሁሉም ዶ/ር ሙላቱ ለታጩበት ፕሬዝዳንትነት ከኢህአዴግ ጋር ተጣብቀው በአስራ ሁለት ዓመታቸው ሲሾሙ ቢያንስ ምን ይሰማቸው ይሆን?
የሆነው ሆኖ ዶ/ር ሙላቱ ኦህዴድ ናቸው።የህወሃት ታዛዥና ዶ/ር ነጋሶ አቶ መለስን መንግስቱን መሰልከኝ ብለው እቅጩን ተናግረው በወጡበት ስብሰባም ከተገኙ የኦህዴድ ባለስላጣናት አንዱ ነበሩ። የራሳቸው ሀሳብ የሌላቸው እና ፍጹም የህወሃት ታዛዥ በጨዋ ቋንቋ <<አጎብዳጅ>> የራሳቸው ወጥ አቋም የሌላቸው ሲባሉ ግን እሰማ ነበር። ለሁሉም ዶ/ር ሙላቱ ዛሬ የተሰጣቸውን የውሸት ዲሪቶ በማንበብ ስራቸውን ጀምረዋል።ቀሪውን የምናየው ቢሆንም ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ እንደ ዶር ነጋሶ ግን መንፈሰ ጠንካራ እንዳልሆኑ በተደጋጋሚ ሲወራ ይሰማል።
ethiomedia
No comments:
Post a Comment