Friday, December 20, 2013

ደቡብ ሱዳን ከየት ወዴት? (ጥንቅር) ደረጀ ሀብተወልድ፦ኢሳት በደቡብ ሱዳን ባለፈው እሁድ የተነሳው ግጭት ወደ ጦርነት ተሸጋግሮ አመጽ ያስነሱት ሀይሎች "ቦር"የተሰኘችውን ቁልፍ የሆነች ከተማ መቆጣጠራቸውን ዓለማቀፍ መገናኛ ብሀን ዘግበዋል።

በደቡብ ሱዳን ባለፈው እሁድ የተነሳው ግጭት ወደ ጦርነት ተሸጋግሮ አመጽ ያስነሱት ሀይሎች "ቦር"የተሰኘችውን ቁልፍ የሆነች ከተማ መቆጣጠራቸውን ዓለማቀፍ መገናኛ ብሀን ዘግበዋል።
ቅድመ-ታሪክ
በአሁኑ ወቅት ሱዳን የሚባለው አካባቢ በጥንት ጊዜ የኑቢያ መንግስት ወይም አገዛዝ ተብሎ ይጠራ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያመለክታሉ።አካባቢው ከክርስቶስ ልደት ከ2600 ዓመት በፊት ጀምሮ ይተዳደር የነበረውም፤ በግብፆች ነበር።የግብፃውያን እና የኑብያውያን የጋራ አስተዳደርና ስልጣኔም እስከ 350 ዓመተ ምህረት ድረስ የኩሽ ሥልጣኔ ተብሎ ሲጠራ ቆይቷል። ግብጽ እና ሱዳን ከጥንት ጀምሮ የዚህ ዓይነት ግንኙነት የነበራቸው አገሮች ነበሩ።
እንደገና ከዘመናት በሁዋላ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1874 ግብፆች ወደ ሱዳን በመግባት የራሳቸውን ክልል መሰረቱ።የግብፅ የእስላማዊ ማሀዲስት አብዮተኞች በ1885 ሱዳንን ወረሩ።ይሁንና ከ1882 ጀምሮ ግብፅን በቅኝ ግዛት ስር አድርጎ የቆየው የታላቋ ብሪታኒያ ጦር ከአምስት ዓመት በሁዋላ ማለትም በ1898 ዓ.ም ወደ ሱዳን በመዝለቅና የማሀዲስቶችን ወረራ በመቀልበስ ሱዳንንም የራሱ አደረገ።ከዚያም"የአንግሎ ኢጂፕሺያን ሱዳን" አስተዳደር ተመሰረተ።
በ20ኛው ክፍለ ዘመን መግቢያ ክርስቲያን ሚሺነሪዎች ወደ ሱዳን ደቡባዊ ክፍል በመግባት ህዝቡን ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ጀምሮ ስለ እምነትና የተለያዩ ነገሮች በማስተማር ለወጡት። የሚሺነሪዎቹን የትምህርት ውጤት ተከትሎ በሙስሊሙ የሰሜኑ ክፍል እና በክርስቲያኑ የደበብ ሱዳን ህዝብ መካከል በግልጽ የሚታይ ልዩነት ተፈጠረ።
"አንግሎ ኢጅፕሺያን ሱዳን" -የተሰኘው አስተዳደር፤ ሱዳን ራሷን የቻለች አገር እንድትሆን እስከወሰነበት እስከ 1953 ዓመተ ምህረት ድረስ እንግሊዝና ግብጽ በጋራ በመሆን ሱዳንን አስተዳድረዋል።
ሱዳን ራሷን ማስተዳደር በጀመረች በሦስተኛው ዓመት ማለትም እ.አ.አ በ1955 የዱብቡ ሱዳን ተወላጅ የሆኑ የጦር መኮንኖች በሱዳን መንግስት ላይ አመፁ።ያንን ተከትሎ በሰሜን እና በደቡብ ሱዳን መካከል ግጭት ተቀሰቀሰ።
የጦር መኮንኖቹ ያመፁት፤ መሰረቱ ከሰሜናዊ ክፍል የሆነው የሱዳን መንግስት እስልምናን እና የአረብን ባህል በሀይል ወደ ደቡቡ ክፍል እያስፋፋ ነው በሚል ምክንያት ነው።ከዚህም በተጨማሪ መንግስት በፌዴራል አወቃቀር ሥርዓቱ መሰረት የደቡብ ሱዳን ህዝብ የራሱን መሪዎች መርጦ እንደሚተዳደር የገባልውን ቃል ኪዳን አላከበረም የሚል ክስም አቅርበዋል።እናም እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ጃንዋሪ 1 ፣1956 ዓመተ ምህረት ከቅኝ ግዛት ነፃ መውጣቷን በአዋጅ ይፋ ያደረገችው ሱዳን- በ1972 ዓመተ ምህረት እስከተፈረመው የ አዲስ አበባው ስምምነት ድረስ በሁለት ጎራ ሆና በእርስ በርስ ግጭት ስትታመስ ኖራለች።
ረዥም ዓመታት ባስቆጠረው የሁለቱ ሱዳኖች የ እርስበርስ ጦርነት ወደ 500 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል።ከዚህ ሁሉ እልቂት በሁዋላ በተደረገው ስምምነት ደቡብ ሱዳኖች -በሱዳን መንግስት ስር ሆነው የራሳቸውን ክልል እንዲመሰርቱ ተደረገ።
• * * * *
…ይሁንና በስምምነቱ የተገኘው አንፃራዊ መረጋጋት ብዙም ሳይቆይ እ.አ.አ በ1983 ዓመተ ምህረት የወቅቱ የሱዳን ፕሬዚዳንት ጃፋር መሀምድ አል ኒሜሪ ስምምነቱን በማፍረስ ሱዳን በሸሪያ ህግ የምትተዳደር እስላማዊ አገር ሆና እንደምትቀጥል በግልጽ አወጁ።ይህ የኒሜሪ አዋጅ ደቡቦችን ክፉኛ አስቆጣ። ወዲያውኑም የደቡብ ሱዳን የነፃነት ንቅናቄ(ኤስ ፒ ኤል ኤ) ተመሰረተ።ጦርነት በሱዳን አገረሸ።ወንድማማቾቹ ከሁለት አስርት፤ማለትም ከሀያ አመታት በላይ ተዋጉ፤በጠመንጃ ተገዳደሉ፣በሳንጃ ተሞሻለቁ..የሱዳን ምድር በደም ታጠበ።በነዚህ የጦርነት ዓመታት በተለይ በአማፅያኑ ድርጊት የተቆጡ የመንግስት ወታደሮች በሰላማውያን የደቡብ ሱዳን ነዋሪዎችና መንደሮቻቸው ላይ በተደጋጋሚ አሰቃቂ ጭፍጨፋ ፈፀሙ።ህዝባዊ ጥያቄና አመጽ የሚነሳባቸው መንግስታት አንዱ ዘዴያቸው"ከልዩነት ማትረፍ" እንደመሆኑ መጠን ፤የሱዳን መንግስትም በጭፍጨፋው ሳያቆም በተለያዩ ብሔረሰቦችና ጎሳዎች መካከል ግጭት እንዲፈጠር ተግቶ ሢሰራ መቆየቱንም መረጃዎች ያመለክታሉ።
በ2002 ዓ.ም የሱዳን መንግስት እና ኤስ.ፒ.ኤል ኤ ግጭታቸውን በድርድር ለመፍታት ተስማሙ።በሰላም ንግግሩ የሱዳን መንግስት- ለተከታታይ ስድስት ዓመታት ከደቡብ ሱዳን ጋር ፍትሀዊ የስልጣን ክፍፍል እንደሚያደርግ እና ከዚያም ለደቡብ ሱዳን ህዝብ ሪፈረንደም እንደሚያዘጋጅ ስምምነቱን ገለፀ።ይሁንና የሰላም ድርድሩ እየተካሄደ ባለበት በዚህ ወቅትም ሁለቱም ወገኖች ጦርነቱን አላቆሙም ነበር።
ድርድሩ በተጀመረ በሶስተኛው ዓመት ማለትም ጃንዋሪ 9 ቀን 2005 ዓመተ ምህረት የ አፍሪካካ ረዥሙ ጦርነት ተብሎ የተጠራውን የሁለቱን ሱዳኖች ግጭት ያስቆማል የተባለው ስምምነት በሱዳን ፕሬዚዳንት በኦማር ሀሰን አልበሽር እና በአማጽያኑ መሪ በጆን ጋራንግ መካከል ተፈረመ።በድርድሩ ከሱዳን አጠቃላይ የነዳጅ ሀብት ግማሹ ለደቡብ ሱዳን እንዲውል ፣ፍትሀዊ የስልጣን ክፍፍል እንዲኖርና እና ከስድስት ዓመታት በሁዋላ ሪፈረንደም እንዲካሄድ ተስማምተው ነው ፊርማቸውን ያኖሩት።
እናም...ከድርድሩ ከሁለት ሳምንት በሁዋላ የአማጽያኑ መሪ ጆን ጋራንግ የሱዳን ምከትል ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ።
ለመታገል እንጂ ለሹመት ያልተፈጠሩት ጆን ጋራንግ ብዙም ሳይቆይ በሄሊኮፕተር አደጋ ህይወታቸው ማለፉ ተነገረ። የ አደጋው መንስዔ መጥፎ አየር እንደሆነ በሱዳን መንግስታዊ ብዙሀን መገናኛዎች በስፋት ቢነገርም፤ አደጋው የተቀነባበረ ሴራ ሊሆን እንደሚችል የፃፉና የተናገሩም በርካታ ናቸው። የ አደጋው ዜና በሰላሙ ድርድር ተስፋ አድርገው የነበሩትን በተለይም ደቡብ ሱዳኖችን አስቆጣ።በዜናው በተቆጡ ወገኖች በካርቱም ግጭት ተቀስቅሶ መቶ ሰዎች ተገደሉ። በደቡብ ሱዳኖች ዘንድ ፦"በድርድር ስም ድላችንን እየቀለበሰ ነው" የሚል ክስ መሰማቱ ያስደነገጠው የሱዳን መንግስትም ወዲያውኑ የጆን ጋራንግ ምክትል የነበሩትን ሲልቫ ኪርን በምክትል ፕሬዚዳንትነት ሾመ።ያን ተከትሎ ሁኔታዎች እየተረጋጉ እና የሰላም ስምምነቱ ውሃ የሚይዝ እየመሰለ መጣ።
ጃንዋሪ 9፣2011 በተካሄደው የደቡብ ሱዳን ሪፈረንደም 98 .8 በመቶ የሚሆኑት ድምጽ ሰጭዎች ከሰሜን ሱዳን ተለይተው የራሳቸውን መንግስት መመስረት እንደሚፈልጉ አስታወቁ። አዲሲቷን አገር ዱባን የፈጠረው የደቡብ ሱዳን ሪፈረንደም "ታሪካዊ" ተብሎ ተወደሰ።ዓለማቀፍ ትኩረትን ሳበ። መንግስታት ለደቡብ ሱዳናውያኑ ፦"የ እንኳን ደስ ያላችሁ!"መልእክቶቻቸውን አጎረፉ።
የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽርም ያለምንም ማንገራገር ውጤቱን እንደሚቀበሉ አስታወቁ። አክለውም የአሁኑ የስልጣን ዘመናቸው በ2015 ሲጠናቀቅ እንደገና ለምርጫ እንደማይቀርቡ አስታወቁ።
አልበሽር በሪፈረንደሙ ሂደት እና ውጤት የተለሳለሰ አቋም ያሳዩት-ባስተዳደር ጊዜያቸው በዳርፉር እና በሌሎች የሱዳን አካባቢው ለተፈጠሩ እልቂቶች በ ዓለማቀፉ ፍርድ ቤት ተጠያቂ ስለሆኑ እና ዓለማቀፋዊ ጫናና ውጥረቱ ስለበረታባቸው እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ።
ህዝበ ውሳኔውን ተከትሎ በሱዳን አየር ላይ አንፃራዊ ሰላም የሰፈነ ቢመስልም በድርድሩ ጊዜ ጥርት ብለው ባልተቋጩ እና ወደፊት በሂደት እንደሚፈቱ ስምምነት ላይ ተደርሶባቸው በነበሩ ጉዳዮች ዙሪያ አዲስ ውጥረት መፈጠሩ አልቀረም።በተለይ በነዳጅ ሀብቷ በምትታወቀው በአብዬ ግዛት ሁለቱ ሱዳኖች የፈጠሩት ውዝግብና ግጭት በዋነኝበት የሚጠቀስ ነው። እናም ትናንት በሪፈረንደም ሰላም መሰረቱ የተባሉ አገሮች በማግስቱ የፈጠሩትን ውጥረት፤ በመነጋገር ሊፈቱ ባለመቻላቸውና ውጥረቱ ወደ ግጭት ተሸጋግሮ -ለገላጋይ በማስቸገራቸው- አህጉራዊና ዓለማቀፍ የሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲላክ ተደረገ።
ሁለቱ ሱዳኖች-ከአብዬ በተጨማሪ በሌሎች በርካታ የድንበር አካባቢዎችም ያነሷቸው የይገባኛል ጥያቄዎች አልተቋጩም፣እልባት ሊያገኙ አልቻሉም። እናም ጊዜያቸውን ጠብቀው የሚፈነዱ ፈንጆች ሆነው እንደተዳፈኑ እየጋሙይገኛሉ።

የሁለቱ ሱዳኖች ግንኙነት በዚህ አሣሳቢ ደረጃ ላይ ባለበት ሁኔታ ነው ከሰሞኑ ከአዲሲቷ ነፃ አገር ማለትም ከወደ ደቡብ ሱዳን አስገራሚ ዜና የተሰማው።
ህዝባቸውን ከጨቋኝ እና ከአምባገነን መዳፍ ስር ለማውጣትና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ተቋዳሽ ለማድረግ ለዓመታት ጠመንጃ አንግበው ሲታገሉ መቆየታቸውን ሲናገሩ የሚደመጡት ደቡብ ሱዳናውያን እነሆ እርስበርስ መዋጋት ጀምረዋል።
ደቡብ ሱዳን ካለፉት ሳምንታት ወዲህ በተኩስ እየተናጠች ነው።በ አልበሽር ወታደሮች ሳይሆን በራሷ ልጆች ጥይት።
ከቀናት በፊት ጁባ በተኩስ መናወጧን ተከትሎ የአዲሲቷ አገር መሪ የሆኑት ሳልቫኪር የቀድሞው ምክትል ፕሬዚዳንት ሪክ ማቻር ታማኝ ወታደሮች መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሌሊቱን ተኩስ መጀመራቸውን እና ችግሩ በቁጥጥር ስር መዋሉን ነበር የተናገሩት።
ፕሬዚዳንቱ አክለውም እንዲህ አይነቱን ድርጊት እንደማይታገሱትና ሙከራውን ባደረጉት ላይ ሁሉ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ። ማስጠንቂያቸውን ተከትሎ የአገሪቱ ቴሌቪዥን ከጠፋ ከሰአታት በሁዋላ እንደገና ስራ ጀመረ።
የተፈጠረው ግጭትም ሊበርድ አልቻለም።
ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ተሞክሮ የነበረው መፈንቅለ መንግስት መክሸፉን በተናገሩ ማግስት ግጭት ማገርሸቱን ነው ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሀን የዘገቡት። አልፎ አልፎ በትንሹ ይሰማ የነበረው ተኩስ በተከታታይ እየጋመ መጣ።
ቀን ውሎ ሲያድር የተነሳው ግጭት ወደ ጦርነት ተሸጋግሮ አመጽ ያስነሱት ሀይሎች "ቦር"የተሰኘችውን ቁልፍ የሆነች ከተማ እንደተቆጣጠሩ ነው ቢቢሲ ሀሙስ ማለዳ የዘገበው።
የመንግስት ወታደራዊ ቃል አቀባይ ፊሊፕ አገር፦"ወታደሮቻችን ቦር ከተማን ለቅቀዋል።ከተማዋ በሬክ ማቻር ወታደሮች ቁጥጥር ስር ወድቃለች"በማለት ተናግረዋል።
ባለፈው እሁድ በጁባ በተቀሰቀሰው እና እያደር እየተቀጣጠለ በመጣው በዚህ ግጭት እስካሁን 500 ሰዎች መሞታቸውን የዜና አውታሩ አመልክቷል። በደቡብ ሱዳን ዳግም መቋጫ የማይገኝለት የእርስበርስ ግጭት እንዳይከሰት ከፍተኛ ስጋት ተፈጥሯል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ባንኪ ሙንን ጨምሮ ሌሎች መንግስታትም፤ ተቀናቃኝ ወገኖች ነፍጣቸውን በማስቀመጥ አለመግባባታቸውን በድርድር እንዲፈቱ የተማጽኖ ጥሪ እያቀረቡ ነው።


ፕሬዚዳንቱ መንስኤው"የመፈንቅ መንግስት ሙከራ ነው"ቢሉም፤በዲንቃና ንዌር ጎሳዎች መካከል ያለው የቆየ ፉክክር ለአሁኑ ግጭት መነሳት ምክንያተ እንደሆነ ይነገራል። ፕሬዚዳንቱ ከዲንቃ ሲሆኑ፣ ምክትላቸው የነበሩት ደግሞ ንዌር ናቸው። ፕ/ት ሳልቫኪር የራሳቸውን ጎሳ አባላት ወደ ስልጣን በማምጣት ሀይላቸውን እያጠናከሩ ነው የሚል ትችት በተቃዋሚዎቻቸው ይቀርብባቸዋል።

የዘርና የጎሳ ፖለቲካ ማቆሚያ የለውም። ትናንት አስተዳደራዊ በደል ፈፅሞብናል ያሉትን የሰሜኑን የሱዳን መንግስትን ለመታገል በአንድነት የታገሉ አንድ ህዝቦች እነሆ ነፃ ሀገር በመሰረቱ ማግስት እርስበርስ መፋጀት ጀምረዋል። የጁባ አየር ዛሬም ከሪፈረንደም በሁዋላ በጥይት ጭስ ተበክሏል። ዓለማቀፉ ህብረተሰብም ትናንት፦"እንኳን ደስ አላችሁ!" እያለ ያወደሳቸውን ወንድማማቾች "አረ የገላጋይ ያለህ" እያለ እየተማፀነ ይገኛል።"ውጥረቱና ግጭቱ ወዴት ያመራ ይሆን?"የሚለውም እንዲሁ ዓለማፉን ህብረተሰብ እያነጋገረ ያለ አጀንዳ ሆኗል።

No comments:

Post a Comment