Wednesday, December 11, 2013

የሶማሊ ክልል ለመከላከያ አዛዦች የመክበሪያ ቦታ መሆኗን ምንጮች አስታወቁ በጅጅጋ ከፍተኛ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የህወሀት ከፍተኛ የመከላከያ አዛዦች ወደ ሶማሊ ክልል ሲመደቡ ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ሀብት አጋብሰው እንደሚመለሱ ተናግረዋል።

በጅጅጋ ከፍተኛ መስሪያ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ የኢሳት ምንጮች እንደገለጹት የህወሀት  ከፍተኛ የመከላከያ አዛዦች ወደ ሶማሊ ክልል ሲመ  ከክልሉ መንግስት ጋር በመተባበር ከፍተኛ ሀብት አጋብሰው እንደሚመለሱ ተናግረዋል። 
በአሁኑ ጊዜ ተቀማጭነታቸው ጅጅጋ የሆኑት እና በክልሉ ቁጥር አንድ ሀብታም የሚባሉት /ወ/ት ሀዋ የሌተናንት ጄኔራል ዮሀንስ ገ/መስቀል ሁለተኛ ሚስትና የልጅ እናት ሲሆኑ፣ ግለሰቧ ከተራ ጫት ነጋዴነት በአንድ ጊዜ በብዙ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት ለማጋበስ የቻሉት በፍቅር ጓደናቸው አማካኝነት መሆኑን ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ ሰራተኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
ጄኔራል ዮሐንስ ከወ/ት ሀዋ ጋር የተዋወቁት በኮሎኔልነት ማእረግ የምእራብ ጎዴ አዛዥ በነበሩበት ወቅት ሲሆን፣ በወቅቱ ክልሉ ያወጣውን የምእራብ ጎዴን የካናል ጠረጋ የመከላከያ ሰራዊት እንዲያሸንፍ በማስደረግና የሰራዊቱ አዛዥም ስራውን ወ/ት ሀዋ ኩባንያ አቋቁመው በሰብ ኮንትራትነት እንዲሰጣቸው በማድረግ በአንድ ጊዜ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ እንዲያገኙ አድርገዋቸዋል።
በጄኔራል ዮሀንስና በወ/ት ሀዋ መካከል ያለው የፍቅር ግንኙነት እየደራ ሲሄድ፣ ወ/ት ሀዋ ከፍተኛ ሀይል እየተሰማቸው ከታክስ ጋር በተያያዘ ጥያቄ የሚያቀርቡባቸውን የክልል ሰራተኞችን ሳይቀር የመከላከያን መኪኖች ይዞ በመሄድ በማስፈራራት ከግብር ራሳቸውን ነጻ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ምንጮች ይናገራሉ።
ወ/ት ሀዋ ከፍቅር ጓደኛቸው ከጄ/ል ዮሐንስ ጋር በመሆን ባቋቋሙት ኩባንያ በጅጅጋ ሁለት ታላላቅ ፎቆችን የገነቡ ሲሆን፣ ከዚህም በተጨማሪ ያለምንም ጫረታ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ሀብት የፈሰሰባቸውን ፕሮጀክቶች እንዲሰሩ ተፈቅዶላቸዋል።
ከፕሮጅቶች መካከል የቀብሪ ደሀር የውሀ አቅርቦት፣ የደገሀቡር የውሀ አቅርቦት፣ ጅጅጋ መምህራን ማሰልጠኛ ማስፋፊያ፣ የክልል የትምህርት ቢሮ ፕሮጀክት፣ ጅጅጋ አየር ማረፊያ አካባቢ የሚገኘው ዘመናዊ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ግንባታና ሌሎችንም ውድ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል። ምንም እንኳ /ወ/ት ሀዋ ግንባር ቀደም ሆነው ሀብቱን ቢቆጣጠሩትም ከጀርባ ሆነው የክልሉን ፕሮጀክቶች የሚያሰሩት ጄኔራል ዮሐንስ መሆናቸውን ምንጮች ይናገራሉ።
ጄ/ል ዮሐንስ በአዲስ አበባ ቦሌ መድሀኒያለም አካባቢ እጅግ ዘመናዊ ፎቅ አሰርተዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በክልሉ ውስጥ አሁን በመከላከያ አዛዥነት የሚንቀሳቀሱ አንድ የህወሀት የመከላከያ ኮሎኔል የክልሉ ፕሬዚዳንት የትውልድ ቦታ ላይ አንድ የውሀ ፕሮጀክት እንዲሰሩ የ120 ሚሊዮን ብር ተፈራርመው ስራውን ከጀመሩ በሁዋላና አስፈላጊው ክፍያ ከተፈጸመ በሁዋላ ፐሮጀክቱ አለመሳካቱን ምንጮች ገልጸዋል። ባለፈው ወር ለእኝሁ ኮሎኔል 22 ሚሊዮን ብር ከክልል መስተዳደር ወጪ ተደርጎ እንደተከፈላቸውም ምንጮች ገልጸዋል።
ሰሞኑን በተከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ዝግጀቶችን ከማዘጋጀት ጀምሮ የሽያጭ እቃዎችን እስከማቅርብ የሚደረሱ ስራዎችን ከህወሀት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች በኮንትራት ወስደው ከፍተኛ ትርፍ እንዳገኙበት እነዚሁ የመስተዳድሩ የአስተዳደር ሰራተኞች ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን ጽሬዚዳንት ለማነጋገር ወደ ጽህፈት ቤታቸውው ስልክ ብንደውልም አልተሳካልንም።
 ኢሳት ዜና

No comments:

Post a Comment