DECEMBER 29, 2013
ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ከተለያዩ የሣውዲ አካባቢዎች በመሠባሠብ መጠለያ ጣቢያ የገቡ ስደተኞች፤ የኢትዮጵያ ቆንስላ ከፍተኛ እንግልት እንዳደረሰባቸው በመግለጽ ባሰሙት ተቃውሞ ከሳውዲ ፖሊስ ጋር ተጋጩ፡፡ እጃቸውን ለፖሊስ እንደሰጡና በ10 አውቶቡሶች ተጭነው ሹማሲ ወደተሠኘው የመጠለያ ጣቢያ እንደገቡ የገለፁት ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ከገቡበት ቀን ጀምሮ ለአምስት ቀናት በኢትዮጵያ ቆንፅላ ዳተኝነት የጉዞ ሰነድ በጊዜ ሣይዘጋጅልን ለእንግልት ተዳርገናል ብለዋል፡፡ ያለ ጉዞ ሰነድ መንገላታታቸውን በመወቃም እሁድ እለት በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ ለ3 ሰዓታት ያህል ብሶታቸውን እንዳሰሙ ስደተኞቹ ተናግረዋል፡፡ የሃገሪቱ ፖሊስ አመፅ አስነስተዋል ያላቸውን ስደተኞች ለመደብደብ ሌሊት ወደ ጣቢያው እንደገባ ስደተኞቹ ጠቅሰው፤ በርካታ ኢትዮጵያውያን ላይ የአካል ጉዳት እንደደረሠባቸውና በፖሊስ ጥይት የተመቱ እንዳሉም ገልፀዋል፡፡ ኤምባሲው ወደ ሃገር ቤት ትመለሣላችሁ ብሎ ባቀረበው ጥሪ ወደ መጠለያ ጣቢያው እንደገቡ የተናገረች አንዲት ስደተኛ ለኤምባሲው ሰራተኞች ብንደውልም ድብደደባው ካለቀ በኋላ ነው የደረሱት ብላለች፡፡
በድብደባው እንደተጎዳ የተናገረ ሌላው ስደተኛ በበኩሉ፤ የኤምባሲው ሰራተኞች ዘግይተው ከመድረሳቸውም በተጨማሪ እንደቆሠልን እያዩ፣ ወደ ህክምና ቦታ ለመውሠድም ሆነ እርዳታ ለማድረግ አልሞከሩም ሲል አማሯል፡፡ ከተቃውሞና ከግጭቱ በኋላ፤ ለሴቶችና ለህፃናት ቅድሚያ በመስጠት የመመለሻ ሰነድ ተዘጋጅቶ እየተሰጣቸው መሆኑን የተናገሩት ስደተኞች፤ በድብደባ የተጐዱትን ጨምሮ በርካታ ወንዶች አሁንም በመጠለያ ጣቢያው እየተንገላቱ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሣደር ዲና ሙፍቲን አነጋግረን በጉዳዩ ላይ በሠጡን ምላሽ፤ በወቅቱ በሚዲያዎች የተነገረውን ያህል ባይሆንም፣ “ወደ አውቶቢስ ግቡ አንገባም” የሚል ችግር ተፈጥሮ እንደነበር ጠቅሰው፤ አንዲት ሴት ከመጐዳቷ ውጪ በሌሎች ላይ የደረሠ ጉዳት እንደሌለ ሣውዲ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንፅላ ፅ/ቤት ጠይቀው መረዳታቸውን ገልፀዋል፡፡ ከ145ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሃገር ቤት መመለሳቸውን ያስታወሱት አምባሣደር ዲና፤ አሁንም በመደበኛ በረራዎች በአማካይ እስከ 300 ሠው እየተመለሠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሌላ በኩል በደቡብ ሱዳን ያለውን ውዝግብ ተከትሎ በሃገሪቱ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ጉዳት እንዳይደርስ መንግስት ከሌሎች የኢጋድ አባል አገራት ጋር በመሆን የ24 ሠአት ክትትል እያደረገ መሆኑን ቃል አቀባዩ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡
No comments:
Post a Comment