Wednesday, December 11, 2013

የመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የመንግሥት ተቋማት የኢንተርኔት መረጃዎችን ሚስጥራዊ ሊያደርግ ነው

ተቋማቱ በኤጀንሲው የተሠራውን ‹‹ዳጉ ሜይል›› መጠቀም ይገደዳሉ
የመረጃ ደኅንነት ኤጀንሲ በቅርቡ በፀደቀው አዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ መረጃዎችና ኢንተርኔትን መሠረት ያደረጉ የመረጃ ልውውጦች ከኢንተርኔት ‹‹ሃከሮች›› (በርባሪዎች) ለመከላከል የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይፋ ሊያደርግ ነው፡፡
ቁልፍ የሚባሉ የመንግሥት ተቋማት እንደ ጂ-ሜይል (Gmail) ያሉ የኢንተርኔት መልዕክት ማስተላለፊያዎችን እንዳይጠቀሙ ሊገደዱ ነው፡፡
ኤጀንሲው በቅርቡ ተግባራዊ ለማድረግ እያበለፀገ የሚገኘው ቴክኖሎጂ ቁልፍ የሚባሉ የመንግሥት ተቋማት የኤሌክትሮኒክስ የመረጃ ልውውጥንና የመረጃ ማኅደርን ሚስጥራዊ የሚያደርግ መሆኑን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በእንግሊዝኛ ስያሜው ‹‹ፐብሊክ ኪይ ኢንፍራስትራክቸር›› በሚል የሚታወቀውና በርካታ የዓለም አገሮችና ግዙፍ የሚባሉ ተቋማት በአሁኑ ወቅት የሚጠቀሙበት ውድ የቴክኖሎጂ ውጤት ሲሆን፣ ኤጀንሲው ይህንን ቴክኖሎጂ በራሱ የሰው ኃይል እንዳበለፀገው ለመረዳት ተችሏል፡፡
የቴክኖሎጂ ውጤቱ በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ ሲገመት፣ ተግባራዊ በሚሆንበት ወቅትም ቁልፍ የሆኑ የመንግሥት ተቋማት የመረጃ ልውውጣቸውን በዚህ ቴክኖሎጂ ለማድረግ ይገደዳሉ፡፡
ቴክኖሎጂው በኢንፎርሜሽን ደኅንነት መስክ ‹‹ክሪፕቶግራፊ›› በሚል የሚታወቀውን የመረጃ ደኅንነት አገልግሎት በተቋማቱ ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ የሚያስችል ነው፡፡ ‹‹ክሪፕቶግራፊ›› ማለት በኢንተርኔት ወይም በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የሚተላለፍ ወይም የተቀመጡ መረጃዎችን መረጃው ከሚላክለት ተቀባይ በስተቀር ማንኛውም አካል ወይም የቴክኖሎጂ ውጤት መረጃውን እንዳያነበው ወይም እንዳይቀይረው የሚያስችል የመረጃ ምስጠራ ሳይንስ ነው፡፡
ኤጀንሲውን በድጋሚ እንዲቋቋም ያደረገው በቅርቡ የፀደቀው አዋጅ ለኤጀንሲው ከሰጣቸው ኃላፊነቶች መካከል ይህ የ‹‹ክሪፕቶግራፊ›› ወይም የመረጃ ምስጠራ ተግባር አንዱ ነው፡፡
ይህ ኃላፊነት ለኤጀንሲው የተሰጠበትን ምክንያት ለማብራራት በደጋፊ ማስረጃነት ከአዋጁ ጋር የተያያዘው ማብራሪያ የተሻለ ደኅንነት አላቸው የሚባሉ አገሮች በራሳቸው ቴክኖሎጂ ላይ ብቻ ጥገኛ መሆናቸውን ያስረዳል፡፡ ኢትዮጵያ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝና የቴክኖሎጂውን እውቀት ያካበቱ ዜጎችም በጣም ውስን መሆናቸውን ያብራራል፡፡
በዚህ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ በእጅጉ ኋላ የቀረች መሆኗንና በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በስፋት አገልግሎት ላይ የዋሉ የኢንተርኔት መረጃ መለዋወጫ መንገዶች (ቴክኖሎጂዎች) አሜሪካ በሚገኙ ኩባንያዎች መበልፀጋቸውን ይገልጻል፡፡ እነዚህም የጐግል፣ የያሁና የቢንግ ሰርች ኢንጂኖች እንዲሁም የፌስቡክ ማኅበራዊ ድረ ገጽ በአጠቃላይ የሁሉም ሰርቨሮች የሚገኘው በአሜሪካ መሆኑን ያትታል፡፡
ከላይ በተጠቀሱ የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ሰርቨሮች በአሜሪካ የሚገኙ ናቸው ማለት አሜሪካ በሰርቨሮቹ የሚገኙ መረጃዎችን እንደልቧ ማግኘት የምትችል መሆኑን የአዋጁ አባሪ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ ሌላው የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን ለአደጋ ተጋላጭ የሚያደርገው የቴክኖሎጂው መገልገያ መሣሪያዎች (እንደ ኮምፒውተርና ተዛማጅ መሣሪያዎች) በአምራቾች በሚፈበረኩበት ወቅት የተጋላጭነት ቀዳዳ (Back Doors) እንዲኖራቸው የሚደረግ እንደሆነና ይህም አምራቾች በፈለጉበት ወቅት በፈጠሩት ቀዳዳ ሠርገው በመግባት መረጃዎችን ከባለቤቱ ዕውቅና ውጭ እንደፈለጉ ማድረግ የሚያስችላቸው ነው፡፡
ኤጀንሲው በማገባደድ ላይ የሚገኘው የ‹‹ክሪፕቶግራፊ›› ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረገው አገር አቀፍ የ‹‹ፐብሊክ ኢንፍራክትራክቸር›› ቢያንስ ቢያንስ ቁልፍ የሆኑ የመንግሥት ተቋማት መረጃዎችን ሚስጥራዊነት ወይም የመረጃው ባለቤትና ተቀባይ ባልሆኑ አካላት መነበብ ወይም መለወጥ እንዳይቻል ማድረግን በመሠረታዊነት ያካተተ ነው፡፡
በዚህ መሠረተ ልማት ከሚካተቱ የመንግሥት ተቋማት መካከል ፍርድ ቤቶች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ኮምፒዩተራይዝድ የሆኑ ሥርዓቶችን የሚከተሉ ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት መሆናቸውን ባለፈው ሳምንት ካካሄደው ዓውደ ርዕይ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ኤጀንሲው በራሱ የሰው ኃይል ያበለፀገው ‹‹ዳጉ ኢሜይል›› የሚል መጠሪያ የተሰጠው እንደ ‹‹ያሁ›› እና ‹‹ጂሜይል›› የኢንተርኔት መልዕክት መለዋወጫ ቴክኖሎጂ ማበልፀጉን ለመረዳት ተችሏል፡፡ ‹‹ዳጉ ኢሜይል›› ከአፋር ብሔረሰብ የመረጃ መለዋወጫ ‹‹ዳጉ›› የተባለ ባህላዊ ሥርዓት መጠሪያ ስያሜውን እንዳገኘ በዓውደ ርዕዩ የተገለጸ ሲሆን፣ የሙከራ ትግበራው ተጠናቆ በኤጀንሲው ግቢ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
በቅርብ ጊዜ ውስጥ ‹‹ዳጉ ኢሜይል›› ወደ ተግባር የሚገባ መሆኑንና ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት በዚህ ቴክኖሎጂ ብቻ የመጠቀም ግዴታ እንደሚጣልባቸው ለመረዳት ተችሏል፡፡
በቅርቡ ተግባራዊ ይደረጋሉ ተብለው የሚጠበቁት እነዚህ ቴክኖሎጂዎች ኤጀንሲው ሰሞኑን አካሂዶ በነበረው ዓውደ ርዕይ ላይ ይፋ ሆነዋል፡፡ ኤጀንሲው የቴሌኮም ማጭበርበርን የመከላከል ኃላፊነት በአዋጅ ካገኛቸው ሥልጣኖች አንዱ ሲሆን፣ በዚህ የደኅነነት አገልግሎት ላይ በስፋት መሥራት በጀመረ በጥቂት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 1.75 ቢሊዮን ብር ኪሳራ መታደጉን አስረድቷል፡፡
ከኢትዮ ቴሌኮም ኔትወርክ ውጭ የስልክ ግንኙነት ከሌላው ዓለም ጋር በመፍጠር የተሰማሩ ወንጀለኞች መኖራቸውን የሚያስረዳው ኤጀንሲው የወንጀለኞቹ መረብ ከሕገወጥ ንግድ፣ ከአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርና ከሽብር ጋር የተገናኘ መሆኑን አሳውቋል፡፡ በመሆኑም በዚህ የቴሌኮም ማጭበርበር አገሪቱ 2.7 ቢሊዮን ብር ማጣቷን፣ ኤጀንሲው በስፋት ከተንቀሳቀሰ በኋላ ግን 1.75 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉንና 125 ሰዎችም በሕግ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጿል፡፡
በመረጃ ደኅንነት ዘርፍ በኢትዮጵያ ውስን እውቀት መኖሩ በገሃድ ያለ እውነት በመሆኑ፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍም የመረጃ ደኅንነት ትምህርት በትምህርት ቤቶችና በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠት እንዳለበትና በዚህ ዙሪያም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመወያየት ላይ እንደሚገኝ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
riporter

No comments:

Post a Comment