JANUARY 14, 2014
መንግስት መጪውን ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የማግባባት መጠነ ሰፊ ዘመቻ ሊጀምር እንደሆነ ተደረሰበት። የመጀመሪያው ሙከራም በደሴ እንደሚጀመር ተረጋግጧል። በመንግስት ሚዲያዎች አማካኝነት ተቃዋሚዎችን ጥላሸት የመቀባት ዘመቻም በእቅዱ አብሮ ተካቷል። ከረቡእ ታህሳስ 17 እስከ አርብ ታህሳስ 19\2006 ድረስ ለከፍተኛ የአዲስ አበባና የክልል ስራ ሃላዎች በተካሄደ ዝግ ስብሰባ ላይ ሙስሊሙን አስመልክቶ ሰፊ የዘመቻ እቅድ ነው ይፋ የሆነው ፡፡ መንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በከፍተኛ ባጀት ጭምር በመታገዝ አዲሱን እቅድ ለመጀመር የተገደደው ምርጫው ላይ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ከፍተኛ የሆነ ሽንፈት ይደርስብኛል በሚል ስጋት እንደሆነ ገለፃ ተደርጎበታል።
ይህ እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን ከፍተኛ የሀገሪቱ ባለስልጣናትና የታወቁ አምባሳደሮች ጭምር እቅዱን በማዘጋጀት ደረጃ እንደሚሳተፉ የተገለፀ ሲሆን ለእቅዱ የሚሆን መሪ ሃሳቦችም በባለስልጣናቱ ይፋ ተደርጓል። በአሁኑ ወቅት በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሙስሊሞች በግልፅ በሚታይ መልኩ በመንግስት ላየ ከፍተኛ ጥላቻ እንዳላቸው ለስራ ሃላፊዎቹ የተገለፀላቸው ሲሆን ምርጫውን ለማሸነፍ ሲባል ውስብስብ የሆኑ ዘመቻዎችን ተግባራዊ በማድረግ ህዝቡ ወዶ ሳይሆን ተገዶም ጭምር እንዲመርጥ የማድረግ ስትራቴጂ መንደፍ እንዳለባቸው ከስምምነት ላይ ደርሰዋል ፡፡ ምንም እንኳ ሁሉም ሙስሊም ሊባል በሚችል መልኩ መንግስት ላይ ጥላቻ እንዳለባቸው ቢረጋገጥም ቀላል ቁጥር የሌላቸው ሙስሊም ያልሆኑ ዜጎችም የኢህአዴግ መንግስት ላይ ጥላቻ እንዳላቸው መረጋገጡን ባለስልጣናቱ በስብሰባው ላይ ስጋታቸውን አስቀምጠዋል። በዚህም መሰረት የእነዚህን ህብረተሰብ ክፍሎች ድምፅ ለማግኘት ይህ እቅድ በዘመቻ መልክ መሰራቱ ወሳኝ መሆኑ የማያጠራጥር እንደሆነ የገለፁት ባለስልጣናቱ እቅዱን በሶስት እርከን ከፍሎ ለመስራት አቅደዋል ፡፡
ይሄውም እጅግ በጣም ደሃ የሚባሉትን የህብረተሰብ ክፍሎች ኖረም አልኖረ በአነስተኛ ጥቃቅን በማታለልና በመያዝ ኢህአዴግን በውድም ሆነ በግድ እንዲመርጡ ማድረግ የመጀመሪያው እርከን ሲሆን በሁለተኛው እርከን የሚገኙት ደግሞ ሃብታም የሚባሉ ክፍሎች እንደሀኑ ተገልፇል። እነዚህን ክፍሎች ኢህአዴግን እንዲመርጡ ለማድረግ ቀላል እንደሆነ የገለፁት የስብሰባው ተሳታፊዎች በሀብታቸው ላይ በመምጣት ከነሙሉ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው ጭምር ኢህአዴግን እንዲመርጡ በማድረግ ተፈላጊውን ድምፅ ማግኘት እንደሚቻል ተገልፇል። ለኢህሃዴግ ሃላፊዎች ፈታኝ ሊሆኑ የሚችሉት በሶስተኛው እርከን ላይ የተገለፁት ክፍሎች ሲሆኑ እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች መካከለኛ ገቢ እንዳላቸው የታመነባቸውና ተማሪዎች እንደሆኑ ተገልፇል። ኢህአዴግ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች በውድም ሆነ በግድ እንዲመርጡት ለማድረግ እንደሚቸገር ገልፀው በነዚህ ክፍሎች ላይ ዘመቻው ከፍተኛ የሆነ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግባቸው ይፋ ሆኗል።
ዘመቻውን በሚፈለገው ደረጃ ተፈፃሚ ለማድረግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ትልቅ ፈተና ሊሆኑ እንደሚችሉ እንደ ስጋት የተቀመጠ ሲሆን ይህን ለመከላከል በቀጣይ ጊዚያቶች የመንግስት ሚዲያዎች በተቃዋሚዎች ላይ ሰፊ የማጥላላት አመቻ እንዲከፍቱ እንደሚደረግ ታውቋል። ይህ እቅድ እንዲጎለብትና ወደ ስራ በአፋጣኝ ለመግባት እንዲቻል ከፍተኛ የመንግስት ኤክስፐርቶችና አምባሳደሮች ጭምር የሚከታተሉት ኮሚቴ ተቋቁሞ እቅዱ እየተሰራ ሲሆን በሁለት ሳምንት ጊዜውስጥ የመጀመሪያው ዘመቻ ለኢህአዴግ ከፍተኛ ጥላቻ እንዳላቸው በሚታመኑት በደሴ ከተማ ነዋሪዎች እንደሚጀመር የመንግስት ባለስልጣናቱ ይፋ ማደረጋቸውን የፍትህ የውስጥ ምንጮች አጋልጠዋል።
No comments:
Post a Comment