በህገመንግስቱ ላይ ህዝብን ለአመጽ በማነሳሳት፣ የህዝብን ሃሳብ በማናወጥ እና “ጨፍጫፊ” በማለት የመንግስትን መልካም ስሙን በማጥፋት የተከሰሰው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ በመከላከያ ማስረጃነት ያቀረበው የቢቢሲ ዶክመንተሪ ፊልም፣ የቢቢሲ ስለመሆኑ ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ሲል ፍ/ቤቱ ጉዳዩን ለውሣኔ ቀጥሯል፡፡
ተከሳሹ ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ቢቢሲ ያዘጋጀው ነው በሚል በመከላከያ ማስረጃነት የቀረበው የድምጽ ምስል ዶክመንተሪ ፊልም በእርግጥም የቢቢሲ ስለመሆኑ ጥያቄ በማስነሳቱ ከጣቢያው ሃላፊዎች ማረጋገጫ እንዲያቀርብ ቀደም ባለው ቀጠሮ ፍ/ቤቱ ትዕዛዝ የሰጠው፡፡ ከትናንት በስቲያ በዋለው ችሎት የተከሳሽ ጠበቃ ለፍ/ቤት እንዳስረዱት፤ ማረጋገጫውን ለማግኘት ከቢቢሲ ሃላፊዎች ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸውን ጠቁመው ለዚህኛው ቀጠሮ ሊደርስላቸው ባለመቻሉ ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሠጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን ቀደም ሲል በአቃቤ ህግ የቀረበበትን ማስረጃ ይከላከሉልኛል ያላቸውን የሰው ምስክሮች ለፍ/ቤቱ ከማሰማቱም በተጨማሪ የሰነድ ማስረጃዎችን አቅርቦ መከራከሩ ይታወሳል፡፡
ለፍ/ቤቱ ካቀረባቸው የመከላከያ የሰነድ ማስረጃዎች መካከልም 4 ገጽ ያለው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ጉባኤ (ኢሠመጉ) ሪፖርት፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ “ኢትዮጵያን አመጽ አያሰጋትም” ሲሉ የሠጡት ቃለ ምልልስ፣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ሪፖርት እንዲሁም ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ ቢቢሲ በፎከስ ኦን አፍሪካ ያሠራጨውና ፍ/ቤቱ ማረጋገጫ የጠየቀበት ዘገባ ይገኙበታል፡፡ ተከሣሹ ባቀረባቸው የመከላከያ ማስረጃዎች ላይ አስተያየቱን የሰጠውን አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ የቀረቡት ማስረጃዎች ከክሱ ፍሬ ሃሳብ ጋር ግንኙት የላቸውም ብሎ የተከራከረ ቢሆንም ፍ/ቤቱ ሣይቀበለው ቀርቷል፡፡ አቃቤ ህግ በቀረቡት የሰነድ ማስረጃዎች ላይ ያለውን አጠቃላይ አስተያየት በቀጣዩ ቀጠሮ ለማቅረብ ፍ/ቤቱን ጠይቆ ተፈቅዶለታል፡፡ ፍ/ቤቱም የተከሳሽን የቢቢሲ ዘገባ ማረጋገጫ ለመቀበልና የአቃቤ ህግን አጠቃላይ የማስረጃ አስተያየት ሠምቶ ውሣኔ ለመስጠት ለየካቲት 5 ቀን 2006 ዓ.ም ቀጥሯል፡፡
በሌላ በኩል ሐዋሣ በሚገኘው የሲዳማ ዞን ከፍተኛ ፍ/ቤት፤ የሃዋሣ ዩኒቨርሲቲ የ300ሺህ ብር የፍትሃ ብሔር ክስ ያቀረበባቸው የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ አሳታሚና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሚሊዮን ደግነው እንዲሁም ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ ባለፈው ረቡዕ ፍ/ቤት ቀርበው የቃል ክርክር ካደረጉ በኋላ፣ የፍ/ቤቱን ውሣኔ ለመስማት ለጥር 20 ቀን 2006 ተቀጥረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፍ/ቤቱን ሂደት ለመከታተልና ስለዘገባው ማብራሪያ ለመስጠት ወደ ሃዋሣ በሄደበት ወቅት የትራፊክ አደጋ የደረሰበት ጋዜጠኛ ኤፍሬም በየነ ስለ አደጋው ፖሊስ አዲስ አበባ ድረስ መጥቶ ቃሉን የተቀበለ ሲሆን፤ እስካሁን ግን ክስ እንዳልተመሠረተ የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
አዲስ አድማስ
No comments:
Post a Comment