Friday, January 10, 2014

አቶ ያረጋል አይሸሹምን ጨምሮ 6 ግለሰቦች ከ6 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራተ ተቀጡ

አዲስ አበባ ፣ ጥር 2 ፣ 2006 (ኤፍ.ቢ.ሲ.) በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በጨረታ ሂደት የሙስና  ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው 6 ግለሰቦች ዛሬ ከ6 እስከ 15 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራተ ተቀጡ።
ተከሳሾቹ አቶ ያረጋል አይሸሹም የቀድሞ የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የፌደራል ህብረት ስራ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ፣ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ሃላፊና የክልሉ ምክር ቤቱ አፈጉባኤ የነበሩት አቶ ሀብታሙ ሂካ ፣ የጌድዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት ባለቤትና ስራ አስኪያጅ አቶ ጌድዮን ደመቀ፣ አቶ አሰፋ ገበየሁ የአቶ ጌድዮን አማካሪ ፣ አቶ ገዛኧኝ አድገ እና አቶ መክብብ ሞገስ በስራ ተቋራጭነት የሚሰሩ ናቸው።
በ1997 ዓ.ም ከክልሉና ከፌደራል መንግስት በተገኘ የ79 ሚሊዮን ብር በጀት የአሶሳ ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና ኮሌጅ ፣ የግልገል በለስ ማሰልጠኛ ኮሌጅና የጣና በለስ ሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት የማስፋፊያ ግንባታ ፕሮጀክት እንዲከናወን አቶ ያረጋል አይሸሹም የሚመሩት የክልሉ ካቢኔ ይወስናል።
በግልፅ ጨረታ ወጥቶ ተጫራቾች ተወዳድረው ግንባታው መከናወን ሲገባው ፥ ባልተገባ መንገድ 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሽ በፈጠሩት የጥቅም ትስስር ፤ የጌድዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት እንዲያሸንፍ ይደረጋል።
የክልሉ መንግስት የግዥ ስርዓት መመሪያ ከ300 ሺህ ብር በላይ የሆነ ግዥ ሲፈፀም የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ማፅደቅ አለበት የሚል ቢሆንም ፥ ከተከሳሾቹ አቶ  ያረጋል አይሸሹምና አቶ ሀብታሙ ሂካ ከባለሃበቶቹ ጋር በመመሳጠር ጌድዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት ያለግልፅ ጨረታ እንዲያሸንፍና ሶስቱንም ፕሮጀክቶች እንዲሰራ ያደርጋሉ።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከ 5 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ክፍያ ተጫራቹ እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን ፥ በ13 ወራት ይጠናቀቃል ተብለው ውል የተገባባቸው ፕሮጀክቶች ከ5 ዓመት በላይ አስቆጥረዋል ፤ ጨረታውን አሸነፈ የተባለው ድርጀትም በህገወጥ መንገድ እንዲያሸንፍ ከመደረጉም በላይ ደረጃው ፕሮጀክቶቹን ለመገንባት የሚያስችል አለመሆኑም በክስ መዝገቡ ተጠቅሷል።
የፌደራል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አቃቤ ህግ አቶ ያረጋል አይሸሹምና አቶ ሀብታሙ ሂካን ስልጣንን ያለአግባብ በመጠቀም የሙስና ወንጀል ሌሎች ባለሀብቶችን ደግሞ  በመመሳጠር በዚህ ወንጀል በመሳተፋቸው ከሷቸዋል።
እንዲከሰሱ ካስቻሏቸው ነጥቦች መካከል በ13 ወራት ይጠናቀቃል ተብለው ውል የተገባባቸው ፕሮጀክቶች ከ5 ዓመት በላይ መጓተታቸው ፣ በተጨማሪ 7 ሚሊየን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ለተቋራጩ መከፈሉ ፣ እነዚህ ባለሀብቶች በተለያየ ጊዜያት ለአቶ ያረጋል አይሸሹምና ለአቶ ሀብታሙ ሂካ ጉቦ መስጠታቸው ፣ የጨረታ መመሪያ ደንብ መጣስና ሌሎች ተያያዥ ጭብጦች ናቸው።
መዝገቡን ሲመረምር የቆየው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት ባለፈው ህዳር 11 2006 አቶ ያረጋል አይሸሹም ፣ አቶ ገዛኧኝ አድገና  አቶ መክብብ ሞገስን በአቃቤህግ ከተመሰረተባቸው ክሶች በአንድ ብቻ ጥፋተኛ ናቸው ሲል ፥ አቶ ሀብታሙ ሂካ ፣ ጌድዮን ደመቀና አቶ አሰፋ ገበየሁን በ3 ክሶች ነበር ጥፋተኛ ያላቸው።
በዚህ መሰረት ዛሬ ከሰዓት ችሎቱ የተከሳሾችን የቅጣት ማቅለያ ከግምት በማስገባት አቶ ያረጋል አይሸሹምን በ7 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ20 ሺህ ብር ፣ አቶ ሀብታሙ ሂካን በ15 ዓመት ፅኑ እስራት እና  በ45 ሺህ ብር ፣አቶ አሰፋ ገበየሁን በ15 ዓመት ፅኑ እስራትና 60 ሺህ ብር ፣ አቶ ጌድዮን ደመቀን በ14 ዓመት ፅኑ እስራት እና 60 ሺህ ብር ፣ አቶ ገዛኧኝ አድገ እና አቶ መክብብ ሞገስን እያንዳንዳቸው በ 6 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ25 ሺህ ብር እንዲቀጡ ወስኗል።
በመዝገቡ በ7ኛ ተራ ቁጥር ተጠቅሶ የነበረው የአቶ ሀብታሙ ሂካ ወንድም አቶ ሀብተገብርኤል ሂካ ህዳር 11 ፣ 2006 ዓ.ም በዋለው ችሎት በብይን በነፃ መለቀቁ ይታወሳል።

No comments:

Post a Comment