ፈጽመዋል በተባሉት የተለያዩ ወንጀሎች ክስ ተመሥርቶባቸው በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ፣ ከፍተኛና ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸውንና የፀናባቸውን ‹‹ፍርደኞች ከ25 ሺሕ ብር እስከ 350 ሺሕ ብር፣ በድምሩ ከ1.8 ሚሊዮን ብር በላይ ጉቦ በመቀበል ከእስር ፈትተዋል በሚል የተጠረጠሩ ሦስት የአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት አስተዳደር የተለያዩ ማዕረግተኞችና ከእስር ተፈተዋል የተባሉ አሥራ ሦስት ግለሰቦች ላይ ክስ ተመሠረተ፡፡
የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ፣ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ወንጀል ችሎት ታኅሣሥ 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ተጽፎ ያቀረበው ጥር 1 ቀን 2006 ዓ.ም. የተነበበው ክስ እንደሚያብራራው፣ የማረሚያ ቤቱ የእስረኛ አስተዳደር ኃላፊ ዋርደን ኢብራሂም መሐመድ፣ የፍችና ሪከርድ ቡድን መሪ ኦፊሰር ገብረ መድኅን አልጋና የማረሚያ ቤቱ ከፍተኛ ጥበቃ አስተዳደር፣ ሰለሞን ገለታና ሚስባህ ከድር ከተባሉ ግለሰቦች ጋር ሕገወጥ የጥቅም ትስስር በመፍጠር 11 ፍርደኞችን ጉቦ እየተቀበሉ ከእስር እንዲፈቱ ማድረጋቸውን ክሱ ያብራራል፡፡
ሰለሞን ገለታ የተባለው ተከሳሽ መስፍን አዲላና ቴዎድሮስ ግደይ ከተባሉት ተከሳሾች ጋር በመመሳጠር፣ ዶ/ር በድሪ ጅብሪል፣ ሰለሞን በየነ፣ መሐመድ ሁሴን (ያልተያዘ)፣ አማን ወርቁ፣ ሸምሱ ወርቁ፣ አማን ጀማል፣ ጌታቸው አቃኔ፣ ሐጐስ ኪዳኔና ቃሲም ከማል የተባሉ በተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች ተፈርዶባቸው ሳሉ፣ የእስራት ጊዜያቸው ሳይጠናቀቅ ጉቦ ከፍለው እንዲፈቱ ማድረጋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡
እስረኞቹ እንዲፈቱ የተደረገው በስማቸው ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያልደረሰባቸውን የመዝገብ ቁጥሮች በመጠቀም፣ ሐሰተኛ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤትና የሰበር ሰሚ ውሳኔ የመስጠት የሥራ ሒደት፣ ‹‹ከእስር በዋስ ይፈቱ›› የሚል የመፍቻ ትዕዛዝ፣ ሐሰተኛ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ሬጅስትራር ፊርማ ያለበት ሸኚ ደብዳቤ በማዘጋጀትና ሐሰተኛ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ደረሰኝ በመጠቀም መሆኑን ክሱ ይዘረዝራል፡፡
በመሆኑም ሁሉም ተጠርጣሪዎች በዋና ወንጀል አድራጊነትና በሚሰጠው ውጤት ሙሉ ተካፋይ በመሆን፣ በሥልጣን ያላግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል መከሰሳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
No comments:
Post a Comment