Monday, January 20, 2014
“ነፃነታችንን መልሱልን!?”
ከተመስገን ደሳለኝ
የኢህአዴግ መራሹ መንግስት ‹መዝገበ ቃላት› ለነፃነት የሚሰጠው ትርጓሜ ‹አራምደዋለሁ› ከሚለው ግራ-ዘመሙ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ብያኔ አንፃር የሚተነተን በመሆኑ፣ የየትኛውም ተቋም ነፃ ሆኖ የመንቀሳቀስ መብት ላይ ረዣዥም እጆቹን ደጋግሞ እየጫነ ሲጨፈልቅና ሲያስጨፈልቅ ለመኖሩ በርካታ ማሳዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡ ይሁንና ከብዙዎቹ መሀል ለጊዜው የእምነት ተቋማት የነፃነት ወሰን እስከ ምን ድረስ ነው? የሚለውን ተጠየቅ በተለይም ከሁለቱ ታላላቅ ሃይማኖቶች (ክርስትና እና እስልምና) አንፃር ተራ በተራ ከፈተሽን በኋላ ተቋማቱን ከእንዲህ አይነቱ ወደ ቅርቃር ከሚገፋ ፈተና የሚታደጋቸውን ብቸኛ የመውጫ መንገድ ለማስታወስ እሞክራለሁ፡፡
‹‹እስልምናን መቆጣጠር››
ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ገዥው ፓርቲ እስልምናን ሙሉ ለሙሉ የመቆጣጠር እቅዱን ዳር ለማድረስ ያልፈነቀለው ድንጋይ፣ የአልማሰው ሥር እንዳልነበር ጥቂት የማይባሉ ምልክቶችን አይተናል፡፡ ለምሳሌነትም የቅርቡ በተለምዶ ‹‹የአወሊያ ንቅናቄ›› ተብሎ የሚጠቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ በቂ ይመስለኛል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ (ንቅናቄ) ለመጀመሪያ ጊዜ አደባባይ የወጣው፣ መንግስት የእምነት ተቋሙን በማያፈናፍን መልኩ ለመቆጣጠር በፌደራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ፊት-አውራሪነት ያለአንዳች ይሉኝታ (የብዙሃኑን የእምነቱ ተከታዮች ይሁንታ ሳያገኝ) ‹‹አህባሽ›› የተሰኘ አስተምህሮ በድፍረት ለመጫን ከሞከረባቸው ጊዜያት አንስቶ ባደረጋቸው ተከታታይ ጣልቃ-ገብነቶች ሳቢያ ነው ወደሚል ድምዳሜ ከሚያደርሱን ምክንያቶች ዋነኛው ሆኖ ይነሳል፡፡ ለመንደርደሪያነት ያህልም የተቃውሞውን ጅማሮ በአዲስ መስመር በጨረፍታ እንዳስሰው፡፡
…ለንቅናቄው መነሾ የሆነው በወቅቱ የመጅሊሱ የአመራር አባል የነበሩት ጀማል መሀመድ፣ ለእምነቱ ብቸኛ የሆነውን ሚሲዮናዊ አወሊያ ትምህርት ቤትን በተመለከተ ታሕሳስ 21 ቀን 2004 ዓ.ም ላይ የላኩት ደብዳቤ ነው፤ የደብዳቤው ጭብጥም በርካታ የመስጂድ ኢማሞች፣ መምህራን እና የአረብኛ ተማሪዎች መባረራቸውን የሚያረዳ እንደነበረ አይዘነጋም፡፡
የመጅሊስ አመራርን ‹ፖለቲካዊ ክንድ› ፈርጣማነት በሚያሳብቅ መልኩ የተሰናዳው ይህ ደብዳቤ የቀሰቀሰው ቁጣ፣ ሕዝበ-ሙስሊሙ ለዓመታት አምቆት የነበረውን ብሶት ሊያፈነዳና በርካታ የመብት ጥያቄዎቹን እንዲያነሳ መግፍኤ ይሆናል ብሎ አስቀድሞ የገመተ ያለ አይመስለኝም፤ የሆነው ግን ይህ ነበር፡፡ የእምነት ነፃነት እንዲከበር ሶስት መሰረታዊ ጭብጦችን የያዙት ጥያቄዎችም፡- ‹‹የመጅሊስ አመራሮች አይወክሉንምና ወርደው አዲስ ምርጫ ይካሄድ››፣ ‹‹አህባሽን በምእመኑ ጫንቃ ላይ በግዴታ ለመጫን የሚደረገው ሙኩራ ይቁም›› እና ‹‹አወሊያ ከመጅሊስ ወጥቶ በገለልተኛ ቦርድ ይተዳደር›› በሚል ስር የሚጠቃለሉ ናቸው፡፡ የኋላ ኋላም በአገዛዙ ‹‹እስላማዊ መንግስት በሽብር ተግባር ለመመስረት›› ወደሚል ተምኔታዊ ውንጀላ የተቀየሩት እነዚሁ ጥያቄዎች ነበሩ፡፡
በርግጥ ‹‹አህባሽ››ን ተከልሎ የመጣው መንግስታዊ ጫና ዋነኛ ዓላማው (ከአንዳንድ የምዕራብ ሀገራት ፍላጎት ባሻገር) አስተምህሮውን ተገን አድርጎ ምእመኑን እርስ በርስ በመከፋፈል፣ የተቋሙን ነፃነት በቀላሉ ለመጋፋት የሚያስችለውን መደላድል መፍጠር ነው፡፡ ይሁንና ስልቱ ምንም እንኳ ከሃሳቡ ተጋፊዎች አንጻር አነስተኛ ቢሆንም፣ መንገድ ጠራጊ ደጋፊዎች ሊያስገኝለት መቻሉን መካድ ግን መሬት ካለው እውነታ ጋር እንደ መላተም ይቆጠራል፤ ምክንያቱም የመጅሊሱ አመራር ሙሉ በሙሉ ከአገዛዙ ጎን በመቆም አጀንዳው ቅቡል እንደሆነ ለማስመሰል የማይናቅ አስተዋጽኦ አድርጓልና፡፡
ይህም ሆኖ አብዛኛው የእምነቱ ተከታይ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ተቃውሞ በተነሳበት እዛው አወሊያ ግቢ ተሰባስቦ፣ ከሰባት መቶ ሺህ በላይ የውክልና ፊርማ በማሰባሰብ፣ አስራ ሰባት አባላት ያሉት አንድ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አዋቅሮ ሲያበቃ ከላይ የተጠቀሰውን ሕገ-መንግስታዊ የመብት መከበር ጥያቄውን መልክ አስይዞ መታገሉ ብዙም አላዳገተውም፡፡ እነሆም በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች ሕዝበ-ሙስሊሙን ከጎኑ በማሰለፍ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ እስከተከበረው የዒድ አል-ፈጥር በዓል ድረስ በየመስጊዶቹ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለጥያቄዎቹ ሁነኛ መልስ ይሰጠው ዘንድ ከፍተኛ የተቃውሞ ትግል አድርጓል፤ በተጨማሪም የኮሚቴው አባላት ከተመረጡ ከስምንት ወራት በኋላ (ሐምሌ 10/2004 ዓ.ም) በግፍ መታሰራቸው ሳያንበረክከውና ሳይከፋፍለው፤ ይከተለው ከነበረው ሰላማዊ መንገድ ውልፍት ሳይል ለተራዘመ ጊዜያት መቀጠሉ በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ የታሪክ ገፅ ላይ አዲስ አሻራውን ለማሳረፈ ያስቻለው ይመስለኛል፡፡
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ
አህአዴግአዊ ‹ህቡዕ መዳፍ›…
አገዛዙ በግልፅ የሚታየውን መጅሊስ፣ በማይታይ ስውር ‹መዳፉ› ልጓም ጨብጦ እየጋለበ በኃይማኖታዊ ተቋሙ ላይ በስፋት ጣልቃ መግባቱን የምንረዳው ‹‹መፍትሄ አፈላላጊ›› ተብለው የተመረጡትን የኮሚቴውን አባላት አንድ በአንድ ለቅሞ ወህኒ ቤት ከወረወረ በኋላ፣ የከሰሰበትን የመወንጀያ ጭብጥ እና እንዲከላከሉ የወሰነበትን የማስረጃዎች ይዘት ስንመረምር ነው፡፡
በርግጥ ሁሉም የተከሰሱት በፀረ-ሽብር ሕጉ ሲሆን፣ ከውሳኔው በኋላም አንዳንድ አንቀጾች ከመሻሻላቸው በቀር ምንም የረባ ለውጥ አልታየም፡፡ ይሁንና መንግስት ገና ከመነሻው (ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ) በኮሚቴው አባላት ላይ የተለያዩ ‹ዶክመንተሪ ፊልሞች›ን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በማስተላለፍ የወንጀለኛነት ብያኔ እና የማጠልሸት ቅስቀሳ አድርጎባቸዋል፡፡ ከዚህ በኋላም (ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም) ‹‹ጥፋቶች›› ያላቸውን አራት ጭብጦች በመዘርዘር መደበኛ ክስ መስርቶባቸዋል፡፡ የክሱ ይዘትም ከሞላ ጎደል እንደሚከተለው ተጠቃሎ ሊቀርብ ይችላል፡-
‹‹…‹መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ› በሚል እርስ በእርስ ተመራርጠው ሲያበቁ ከጥር 5 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ሁሌ በየሳምንቱ አርብ ለፀሎት አወሊያ መስጊድ ለሚሰበሰበው ሕዝብ የሽብር ዓላማቸውን ለማራመድ በአዲስ አበባ እና በክልሎች ባዘጋጁት የሰደቃ እና የአንድነት ዝግጅቶች ለሚጠሩት ሕዝብ፣ በማሕበራዊ ድህረ-ገፆች፣ ለዚሁ ትግበራ በተቋቋሙት የተለያዩ ኃይማኖታዊ መገናኛ ብዙሀን፣ በመፃህፍት፣ በበራሪ ፅሁፎችና ዘጋቢ ፊልሞች አማካኝነት… የመጨረሻ ግባቸው የሆነውን እስላማዊ መንግስት ለመመስረት የሙስሊሙ ሕዝብ ቁጥር ከ80 በመቶ በላይ ነው በማለት ለሽብር ተግባር ቀስቅሰዋል፤ አነሳስተዋል፡፡››
ጉዳዩንም በዝግ ችሎት ሲመለከት የነበረው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከአንድ ወር በፊት (ታሕሳስ 3 ቀን 2006 ዓ.ም) የሰጠው ውሳኔ በሶስት የተከፈለ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ የመጀመሪያው አቡበከር መሀመድ፣ አህመዲ ጀበል፣ ያሲን ኑር እና ካሚል ሸምሱን ጨምሮ አስራ አራት ሰዎች ያሉበት ሲሆን፣ ከተከሰሱበት የወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 32(1)(ሀ)(ለ) እና 38(1) መካከል፣ በአንቀጽ 32(1)(ሀ) እንዲከላከሉ ተወስኗል፤ በተጨማሪም ‹‹በፀረ-ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3(1)(2)(4)(6) እና አንቀጽ 4 ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ›› ከሚለው ደግሞ አንቀጽ 3 ቀርቶ በአንቀጽ 4 ተመሳሳይ የተከላከሉ ብይን ተሰጥቶባቸዋል፡፡ ሁለተኛው ጋዜጠኛ የሱፍ ጌታቸውን ጨምሮ አራት ሰዎችን የሚመለከት ሲሆን፤ እነርሱም ከእነ አቡበክር ክስ ጋር የተጠቀሰባቸው የወንጀለኛ መቅጫ አንቀጾች ሁሉም ውድቅ ሆነው በፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ አንቀፅ 7(1) ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ ሶስተኛው የአቶ ጁነዲን ሳዶን ባለቤት ወ/ሮ ሀቢብ መሀመድ እና ሁለት የበጎ አድራጎት ድርጅትን ጨምሮ አስራ ሁለት ተከሳሾች ያሉበት ሲሆን፣ የተላለፈው ውሳኔም በነፃ መሰናበታቸውን የሚገልፅ ነው፡፡
‹‹ማስረጃ›› ፍለጋ…
ከክሱ ጀርባ ረጅሙ የመንግስት እጅ መኖሩን የሚያመላክተው ‹‹ጥፋተኛ›› በተባሉት ተከሳሾች ላይ የቀረበው ‹‹ማስረጃ›› ነው፡፡ እንዲያ ስርዓቱን በኃይል አፈራርሰውና ሌሎች ኃይማኖታዊ ተቋማትን ጨፍልቀው ‹‹እስላማዊ መንግስት›› ሊመሰርቱ ወጥነው ሲንቀሳቀሱ እጅ ከፈንጅ ለመያዛቸው በበቂ ሁኔታ ያስረዱልናል ብለው የጠቀሷቸው ‹‹ማስረጃዎች›› በጠቅላላ የሚከተሉት ናቸው፡- ‹ሁሉም ታሳሪዎች ለፖሊስ ሰጡ የተባለው የእምነት-ክህደት ቃል፣ ዓቃቢ-ሕግ ሰብስቦ ያቀረባቸው የሰው ምስክሮች፣ የሞባይል ቀፎዎች፣ ላፕቶፖች፣ ሲዲዎች፣ በራሪ ወረቀቶች፣ ጭልፋና የወጥ-ድስቶች…›፤ በቃ! በአናቱም ‹‹የሙስሊሙ ቁጥር ከሀገሪቱ ሕዝብ ሰማኒያ በመቶውን ይይዛል ብለዋል›› የሚለው ክስ ተራ አሉባልታ መሆኑን ለማስረገጥ፣ ራሳቸው የኮሚቴው አባላት መጋቢት 2004 ዓ.ም ለቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ከፃፉት ደብዳቤ ውስጥ የሚከተለውን አንቀጽ ብቻ መጥቀሱ በቂ ነው፡-
‹‹…እንደሚታወቀው የሃገሪቱን ሰላሳ ሶስት በመቶ የሚሆነውን የሕብረተሰብ ክፍል የሚወክለው የኢትዮጵያ እስልምና ጠቅላይ ም/ቤት (መጅሊስ) ተገቢው ሕጋዊ ሰውነት የለውም…››
እናሳ! ዓቃቢ-ሕግጋኑ 80 በመቶን ከየት አምጥተው ይሆን? …በርግጥ አቶ መለስ ዜናዊ ‹‹መረጃ እንጂ ማስረጃ የለንም›› እንዲል ገዥው ፓርቲ በእነዚህ የ‹‹ሽብር›› ማስፈፀሚያ ቁሳቁሶች ነው መንበረ-መንግስቱን ከመገልበጥም ሆነ ሀገሪቱን ከኃይማኖታዊ ስርዓት ለጥቂት ታድጌያታለሁና ወንዶች በጭብጨባ፣ ሴቶች በእልልታ አመስግኑኝ የሚለው፡፡
የክሱን ልብ-ወለድነት በአመክንዮ ለማስረዳት ከ‹‹ማስረጃዎቹ›› ውስጥ ሁለት ጉዳዮችን ብቻ መምዘዙ ይበቃናል፡፡ ተከሳሾቹ ለፖሊስ በምን ሁኔታ ቃላቸውን እንደሰጡ እና የአንድ ምስክር እማኝነትን (ምንም እንኳ ችሎቱ በዝግ የተካሄደ በመሆኑ የሁሉንም የሀሰት መስካሪነት ሙሉ ለሙሉ ማጋለጥ ባይቻልም፣ ዳኞቹ ራሳቸው ባሳለፉት ውሳኔ ላይ የተጠቀሰው የአንድ የምስክር ቃል ይህንን መከራከሪያ ያስረግጥልናል)
የመርማሪዎቹ ‹‹ችሎታ››…
የጥፋተኝነታቸው ማሳያ የሆነው የኮሚቴው አባላት ለፖሊስ የሰጡት ቃል ተብሎ በሰነድነት የቀረበው በድምሩ 413 ገፅ ሲሆን፤ ይህ ምርመራም በምን መልኩ እንደተካሄደ በቅርቡ ታሳሪዎቹ በተለያዩ ሚዲያዎች ባሰራጩት ደብዳቤ ላይ የፍትሕ ስርዓቱን ገመና እና በዚች አገር ሰብዓዊ መብቶች ምን ያህል ዋጋ እንዳጡ ልብ የሚሰብሩና በድንጋጤ ዓቅል የሚያስቱ መከራዎቻቸውን ጭምር በመዘርዘር ነግረውናል፡፡ በደብዳቤው ላይ ዓቃቢ-ሕግ ክስ መመስረቻ ያደረገውን ቃላቸውን ፖሊሶቹ ፈልፍለው የደረሱበት የመርማሪነት ‹‹ጥበብ››ን እንዲህ በማለት ነበር የገለፁት፡-
‹‹…በማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ ስነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ስቃይ ደርሶብናል፡፡ ከአስራ አራት ሰዓታት በላይ ያለ እረፍት ቀጥ ብለን እንድንቆም በማድረግ፣ ጀርባችን እስኪላጥ ራቁታችንን በሽቦ በመግረፍ፣ በሰንሰለት በማሰር እና አይናችንን በጨርቅ በመሸፈን የውስጥ እግራችን እስከሚላጥ ገልብጦ በመግረፍ፣ ቀንና ማታ አሰቃቂ በሆነ ምርመራ እና በድብደባ ብዛት እንቅልፍ በመንሳት፣ ፂማችንን በመንጨትና እንድንላጭ በማስገደድ፣ ከአቅም በላይ የሆነ ስፖርት በግድ በማሰራት፣ ብልት በመግረፍ፣ ‹ልጅህን እንገድለዋለን! ሚስትህን አስረን በፊትህ ቶርች እናደርጋታለን! ብልትህ ላይ የውሃ ሃይላንድ በማንጠልጠል መሀን እናደርግሀለን!› እያሉ በማስፈራራት ከፍተኛ የሆነ እንግልትና ስቃይ አድርሰውብናል፡፡ …በክረምት ቀርቶ በበጋ እንኳ ቅዝቃዜው በማይቻለው ‹ሳይቤሪያ› ተብሎ በሚጠራው ጨለማ ክፍል አጉረውናል፡፡ መቋቋም የሚያዳግተውን የማሳቃያ ስሌታቸውን በመጠቀም ያላሰብነውንና ያልሰራነውን ‹እመኑ! ተናገሩ! ፈርሙ!› ብለው አስገድደውናል፡፡››
ወደድንም ጠላንም የሀገራችን እውነተኛ ገፅታ ይሄ ነው፡፡ በአናቱም ታሳሪዎቹ የደረሰባቸውን ግፍና መከራ የሚያረጋግጡልን ገፊ-ምክንያቶች፣ የመጀመሪያው ከዚህ ቀደም የተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት እና የፕሬስ ነፃነት ተሟጋች ድርጅቶች ማዕከላዊን በተመለከተ ያወጧቸው ሪፖርቶች ሲሆን፤ ሁለተኛው ታሳሪዎቹ ራሳቸው ይህንኑ የጭካኔ ተግባር በዝርዝር ጠቅሰው በመርማሪ ፖሊሶቹ ላይ በፍርድ ቤት ክስ መስርተው የነበረ መሆኑ ነው፤ ሶስተኛው ደግሞ መንግስት ‹ጅሃዳዊ ሀረካት› በሚል ርዕስ ያዘጋጀው ‹ዶክመንተሪ ፊልም› በድጋሚ እኩለ ሌሊት ላይ በተላለፈበት ወቅት የማዕከላዊ መርማሪዎች የኮሚቴው ሰብሳቢ የሆነውን አቡበከር መሀመድን እጁን በሰንሰለት የፊጥኝ አስረው ሰብዓዊነቱን በሚያንቋሽሽና መንፈሱን በሚያሸማቅቅ ሁናቴ ቃሉን ሲቀበሉ በቴሌቪዥን መስኮት መመልከታችን ነው፡፡
የዓቃቢ-ሕግ ምስክር ሲባል…
ለዚህ ሙግት ማሳያ የማደርገው ከዓቃቢ-ሕግ ምስክሮች መሀል አንዱ የሰጠውን የምስክርነት ቃል ነው፤ ይህ ግለሰብ በ21ኛ ተከሳሽ ሼኽ ጣሂር አብዱልቃዲር መኖሪያ ቤት ሽጉጥ ከነጥይቱን ጨምሮ የተለያዩ ማስረጃዎች በብርበራ ሲገኝ መመልከቱን በችሎቱ ፊት በፈጣሪው ስም ምሎ ተናግሯል፤ የሚገርመው ነገር ግን ይህ አይደለም፤ ዳኞቹ በሰጡት ውሳኔ ላይ እንደሚከተለው ማለታቸውን መስማታችን እንጂ፡-
‹‹እነዚህ ማስረጃዎች (ሽጉጡም ጨምር) አልቀረቡም፤ ዓ/ሕግም በማስረጃ ዝርዝርና በሰነድነት አልጠቀሳቸውም፤ ሌላ ማስረጃም አልቀረበም፡፡››
እንግዲህ በዝምታ ተገርሞ ከማለፍ በቀር ‹ታዲያ ምስክሩ ከየት አምጥቶ ነው ስለመሳሪያው የዘባረቀው?› የሚል ጥያቄ ማቅረብ አይቻልም፤ ቢቀርብም አጥጋቢ መልስ አይገኝለትም፤ ለምን ቢሉ ሀገሪቱ ኢትዮጵያ ነቻ!! ያውም ኢህአዴግ በብረት መዳፉ ጨፍልቆ የሚገዛት ምስኪን ሀገር፡፡ ...መቼም ይህ ተጨባጭ እውነታ እንዲህ ገሀድ መውጣቱ በዚህ ፀያፍ ተግባር ውስጥ የቀጥታ ተሳትፎ ያልነበራቸውን የገዥው ፓርቲ አመራርንም ሆነ አባላትን ጭምር የአትንኩኝ ባይነት ንዴት ይቀሰቅስ እንደሆነ እንጂ፣ ስለሕገ-መንግስት፣ ሕሊና፣ ሕዝብና አገር በድፍረት መናገር (ጥብቅና መቆም) የሚችሉበት ሞራል ይኖራቸዋል ብሎ ማሰብ ተላላነት ነው (በነገራችን ላይ የሀገሬ የፍትሕ ደጆች እንዲህ የዘቀጡ መሆናቸው ሲጋለጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ በድህረ-ምርጫ 97ም የፈጠራ ማስረጃዎች እና
ሓሳዊ ምስክሮች ምን ያህል ነግሰውበት እንደነበረ ታይቷል፡፡ የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ‹‹የቃሊቲው መንግስት›› እና የአንተነህ ሙሉጌታ ‹‹የተዋረደው ፍርድ ቤት›› መፃህፍት ሂደቱን በቦታው የነበርን እስኪመስለን ድረስ በውብ ቋንቋ ከሽነው በዝርዝር ተርከውልናል)
ከቤተ-ክህነት ጀርባ…
በርግጥ ከቤተ-ክህነት ‹የእምነት ነፃነት ይከበር!› ጥያቄ ጋር በቀጥታ ተያይዞ ለአስከፊው የቃሊቲ ማጎሪያ የተዳረጉ መንፈሳውያን መሪዎች እስካሁን የሉም፡፡ ይህ ግን የአገዛዙ ‹እርኩስ መንፈስ› በደጆቿ ዙሪያ አልረበበም እንደማለት አይደለም፡፡ ፓትሪያርክን አባርሮ ሌላ መሾም፣ እነአቦይ ስብሃትን የመሳሰሉ የፓርቲው አንጋፋ መሪዎች በአደባባይ ‹‹አንድም ከመንግስት ነፃ የሆነ ጳጳስ የለም!›› ከማለት አልፈው፣ ‹‹ነፃ የሆነ ጳጳስ ካለ እሸልመዋለሁ›› እስከሚለው ተሳልቋቸው ድረስ ያሉ ማረጋገጫዎች የሚያሳዩት የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ነውና፡፡ በተለይም በያዝነው ዓመት የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ ወራት ውስጥ ብቻ በቤተ-ክህነቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የገባውን ስውር እጅ እና የእምነቱን የአስተምህሮ መንገድ፣ ከኑፋቄው በመለየትም ሆነ በተለያዩ መንፈሳዊ ተግባሮቹ ስመ-ገናና የሆነውን ‹‹ማህበረ ቅዱሳን›› ላይ የተሸረበውን መንግስታዊ ተንኮል ‹‹ቀጣዩ የኢህአዴግ ዒላማ ማህበረ ቅዱስን ይሆን?›› እና ‹‹ኢህአዴግና የኃይማኖት ነፃነት›› በሚሉ ፅሁፎች እዚሁ መፅሄት ላይ ቀደም ሲል በስፋት ስላወሳናቸው ዛሬ መድገሙ አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ ይሁንና ጣልቃ ገብነቱን የሚያመላክቱ ሁለት አዳዲስ ማሳያዎችን የአጀንዳውን ተጠይቅ ለማጠናከር እጠቅሳቸዋለሁ፡፡
ወረራ-ሲኖዶስ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢህአዴግ ለ‹‹አውራ ፓርቲ››ነቱ ዋስትና የእምነት ተቋማትንም በ‹መንፈሳዊ ክንፍ›ነት ከጎኑ የማሰለፍ ግዴታ ውስጥ የከተተው ይመስል፣ ከፍተኛ ባጀት መድቦና ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት እንደሆነ መታዘብ ይቻላል፡፡ ባሳለፍነው ወርሃ ጥቅምት መደበኛው የሲኖዶሱ ጉባኤ በተደረገበት ወቅት፣ ለመጪው ግንቦት አጠናቅቀው እንዲያዘጋጁ ኃላፊነት ለሰጣቸው አራት አባላቱ ያስተላለፈው ውሳኔ፡- ‹‹ዘጠኝ እጩ ጳጳሳትን መልምላችሁ አቅርቡ!›› የሚል ነበር፡፡ ሆኖም ከቤተ-ክህነት ምንጮቼ ባገኘሁት መረጃ፣ መንግስት የፊታችን ግንቦት ወር በሚደረገው ጉባኤ ላይ ሹመታቸው ፀድቆ በቀጥታ የሲኖዶሱ አባል መሆን በሚችሉት ዘጠኙ ጳጳሳት ምልመላ ላይ ረዥም እጁን እየከተተ መሆኑን ነው፡፡
እንደሚታወሰው ነባሩ የቤተ-ክህነት የጳጳሳት የአመራረጥ መስፈርት የሚከተሉት ናቸው፡- ‹‹በምንኩስና የኖረ (ትዳርም ልጅም ያሌለው)፣ መንፈሳዊውንም ሆነ ዓለማዊው ትምህርቱን በሚገባ ያጠናቀቀ፣ ከአንድ በላይ ቋንቋ መናገር የሚችል፣ እውነትና ሀሰትን የማይናገር፣ አስካሪ መጠጥ የማይጠጣ፣ እድሜው ሃምሳ ዓመት የደረሰ፣ በሚያገለግለበት ቦታ ምስጉን መሆኑ የተረጋገጠ…፡፡›› ይሁንና ጀግናው ኢህአዴግ ደግሞ የፖለቲካ ታማኝነትን በተጨማሪነት ለመክተት ‹አክራሪ ያልሆነ› እና ‹ልማታዊ የሆነ› በሚሉ ሁለት መስፈርቶች ሸፋፍኖ በለመደው ስውር እጁ ተፅእኖ በማድረግ በሲኖዶሱ ውስጥ ያለውን ጉልበት ለማጠናከር እየሞከረ እንደሆነ ማረጋገጤ ለተጠየቁ እንደ አንድ ማሳያ ሊወሰድ ይችላል ብዬ አስባለሁ፡፡
የለውጡ አንድምታ…
ከወራት በፊት የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስ ሆነው በሲኖዶሱ የተሾሙት አቡነ እስጢፋኖስ፣ በአቡነ ቴውፍሎስ ዘመን ፀድቆ ይሰራበት የነበረውን ‹ቃለ-አዋዲ› ለማሻሻል ይሁን ለመሻር ባይታወቅም አዲስ ጥናት አጥንቶ እንዲያቀርብላቸው ኃላፊነቱን ለማህበረ ቅዱሳን ይሰጣሉ፡፡ ማህበሩም በአጭር ጊዜ ውስጥ ‹‹የአዲስ አበባ የሀገረ-ስብከት የአደረጃጀትና አሰራር ለውጥ ጥናት›› በሚል ርዕስ የቤት ስራውን አጠናቅቆ ያቀርባል፡፡
ነገር ግን የመዋቅርንና የአሰራር ለውጥን ጨምሮ ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበት ዘመናዊ የፋይናንስ ስርዓት እንደተካተተበት የተነገረው የጥናቱ ረቂቅ መሰናዳቱን ተከትሎ ገና ከአሁኑ ከአንዳንድ የደብር አስተዳዳሪዎች ዘንድ ከባድ ተቃውሞ እየደረሰበት ነው፡፡ እንደ ምንጮቼ መረጃ ሁናቴው በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት ሀገረ-ስብከቱንም ሆነ የደብር አስተዳዳሪዎችን መከፋፈሉ አይቀሬ ነው፡፡
ይህንን ጉዳይ እዚህ ጋ ያነሳሁት የመንግስትን ጣልቃ ገብነት ያሳያል በሚል ነው፡፡ ይኸውም የጥናቱ ይዘት በወሬ ደረጃ በመናፈሱ ብቻ ‹‹መተግበር የለበትም!›› የሚል ተቃውሞ እያሰሙ ያሉ አንዳንድ ጳጳሳት እና የደብር አስተዳዳሪዎች ‹‹መንግስት ከጎናችን ስለሆነ፣ ከእርሱ ጋር እንነጋገርበታለን››፣ ‹‹ይህ ህግ መፅደቅ የለበትም፣ አለበለዚያ ሪፖርት ለምናቀርብለት አካል ሪፖርት እናደርጋለን››፣ ‹‹አርፋችሁ
ብትቀመጡ ይሻላችኋል››፣ ‹‹እርሶንም (አቡነ እስጢፋኖስን) ከሥልጣንዎት እናወርዶታለን››… እና መሰል ማስፈራሪያዎችን አቡኑ ቢሮ ድረስ በመሄድ መናገራቸው ነው፡፡
በጥቅሉ እነዚህ ሁነቶች ስርዓቱ በቤተ-ክህነት የውስጥ አስተዳደር ምን ያህል ጠልቆ እጁን እንደሰደደ ያስረግጡልኛል ብዬ አምናለሁ፡፡
‹‹ድምፃችን ይሰማ›› ወዴት ተሰወረ?
ባሳለፍነው ሳምንት ሁለተኛ ዓመቱን የደፈነው የሕዝበ-ሙስሊሙ ‹‹የእምነት ነፃነት ይከበር!›› ጥያቄ፣ በተለይም ‹‹መፍትሄ አፈላላጊ›› ተብለው የተመረጡት የኮሚቴ አባላት ለእስር ከተዳረጉ በኋላ የተቃውሞ ንቅናቄው ሲመራ የቆየው ‹‹ድምፃችን ይሰማ!›› የሚል መርህ ባነገቡ አስተባባሪዎች እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ፍፁም ሰላማዊውን እና ሕጋዊውን መንገድ በመከተል የጁምዐን ሶላት እየጠበቁ የኮሚቴው አባላት በአስቸኳይ ከተጣሉበት የስቃይ ጎረኖ እንዲወጡና ያነሷቸው የመብት ጥያቄዎችም ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ እንዲመለሱ አዲስ አበባን ጨምሮ በሌሎችም የሀገሪቱ ከተሞች ያስተባበረው የተቃውሞ ድምፅ ዛሬ በቦታው የለም፡፡ በግልባጩ መስጊዶቹ በከባድ ፀጥታ የተመቱ መስለዋል፡፡
ከማሕበራዊ ሚዲያዎች እስከ የእጅ ስልክ መልዕክት መለዋወጫዎች፤ ከበራሪ ወረቀቶች እስከ ፍትህ ሬዲዮ ድረስ ያሉ የመረጃ ማስተላለፊያ ዘዴዎችን እጅግ በሰለጠነ መንገድ ይጠቀም የነበረው የ‹‹ድምፃችን ይሰማ!›› ተቃውሞ፣ በዘንድሮው የዒድ በዓል ወቅት በእምነቱ ተከታዮች ላይ መንግስት ከወሰደው መጠን የለሽ የጭካኔ እርምጃ በኋላ ዳግም አልተከሰተም፡፡ ይሁንና ምንም እንኳ በበዓሉ ዋዜማ አስተባባሪዎቹ የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ለጊዜው ለማቋረጥ መወሰናቸውን ቢያሳውቁም፣ በስርዓቱ የአመራር አባላት ዘንድ ያለው አተያይ ግን ተቃውሞውን በኃይል መቆጣጠር እንደተቻለ ነው፡፡ በርግጥም ይህ አይነቱ የተሳሳተ መደምደሚያ ይመስለኛል የኮሚቴው አባላትን ውሃ በማይቋጥር ክስ ‹‹ጥፋተኛ›› ብሎ እንዲከላከሉ እስከመወሰን ድረስ የልብ-ልብ የሰጠው፡፡
የሆነው ሆኖ አገዛዙ የእስልምና እምነት ተከታዮችን በአህባሽ እና ሓሳዊ ሰባኪያን ከፋፍሎ ለማዳከም ያደረገው ሙከራ ቢከሽፍም፣ ዛሬም የተነሱት ሕጋዊ የመብት ጥያቄዎች መልስ ካለማግኘታቸውም በላይ፣ በእነዛ ፈታኝ ጊዜያት ሚሊዮኖችን ወክለው በድፍረት ከፊት መስመር የተሰለፉት ንፅሃን የኮሚቴው አባላት በእስር እየማቀቁና ለተለመደው የፖለቲካ ፍርደ-ገምድል ውሳኔ እያመቻቿቸው ስለመሆኑ የ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› አስተባባሪዎች ይዘነጉታል ተብሎ አይገመትም፡፡ በአናቱም ይህ ሁናቴ እንደ ልጅነት ዘመን፣ የሚታሰረው ታስሮ፣ የሚገደለው ተገድሎ፣ የሚሰደደው ተሰዶ… ሲያበቃ ‹ዳቦ ተቆረሰ፣ ዕቃቃው ፈረሰ› ተብሎ በየፊናችን የምንበታተንበት አይነት ጨዋታ አለመሆኑን ማስታወሱ አግባብ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
የመውጫው መንገድ
ኢህአዴግ ያለፉትን ሃያ ሁለት የሰቆቃ ዓመታት በስሁቱ የ‹አብዮታዊ ዲሞክራሲ› ርዕዮተ-ዓለም ብያኔ ሀገሪቱንና ሕዝቧን ለአስከፊ ድህነት፣ ለመራራ ጭቆና ዳርጓል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ባነበረው መከፋፈልና አለመተማመን የሥልጣን ዕድሜውን ያለስጋት ማራዘሙ ተሳክቶለታል፡፡ ጥያቄውም ከዚህ የሚነሳ ቢሆንም፣ ምላሹ በቅርቦቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከታየው የሙስሊሙ ሰላማዊ የትግል ስልት ጋር የሚተሳሰር ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ማንኛውም የመብት ጥሰት የሚያሳስበው ዜጋ ይህን ክቡድ መንፈስ ከመቀላቀል የተሻለ አመራጭ የለውምና (በነገራችን ላይ የኮሚቴው አባላት በቀጠሮ ከሚቀርቡበት የፊታችን ጥር 22 ቀን ጀምሮ ችሎቱ ለታዳሚ ክፍት በመሆኑ ያለአንዳች የኃይማኖት ልዩነት ወደ ፍርድ ቤት በመትመም ከጎናቸው ታላቅ የሕዝብ ደጀን መኖሩን ማሳየቱ መንፈሳቸውን ለማበርታት መልካም አጋጣሚ ነው)
በጥቅሉ ሰማያዊ ነፃነታቸው በፖለቲካ ጉልበት እየተናደ የመጣው የሁለቱ ኃይማኖት ልሂቃንና ተከታዮች ዛሬ ከመቼውም ጊዜ በላይ የጎንዮሽ መተያየታቸውን ገርቶ፣ የብሔር ልዩነትን አዘልሎ በአንድ አውድ ሊያሰባስባቸው የሚችል ገፊ-ምክንያት አላቸው፡፡ እናም ስርዓቱ እርስ በእርስ በጥርጣሬና በስጋት እንዲተያዩ ለማድረግ በተንሸዋረረ የ‹‹መቻቻል›› ፕሮፓጋንዳ ስም እየዘረጋው ያለውን የረቀቀ ወጥመድ በመሻገር፣ የአደባባይ ተቃውሞዎችን በጋራ በማስተባበር የማያቋርጥ ጫና ፈጥረው ለቤተ-አምልኮዎቻቸው ‹‹ነፃነታችንን መልሱልን!?›› አንገብጋቢ ጥያቄ መፍትሄ ማስገኘት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ከግብ ለማድረስ በተለይም ከ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› ውጤታም እንቅስቃሴ ጥቂት ገፆችን በመገንጠል ሰፊ መዋቅር ያለው ‹‹ማሕበረ ቅዱሳን›› ደጋግሞ ቢከልሰው ካለፈ ቁጭት ራሱን መታደግ የሚችልበትን የመውጫ ቀዳዳ ማግኘቱ ብዙ አያለፋውም፡፡
በመጨረሻም ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› ከታሳሪዎቹ የኮሚቴው አባላት መካከል አንዱ የሆነው ካሚል ሸምሱ ሐምሌ 8 ቀን 2004 ዓ.ም እንደ ተናገረው ጠቅሶ በማሕበራዊ ድህረ-ገፆች ያሰራጨውን መልዕክት የርዕሰ-ጉዳያችን መደምደሚ ይሆን ዘንድ ወደደሁ፡-
‹‹የዚህች ሀገር ሰላም ፀጥታ ነው፤ ዲሞክራሲን ማስፈን የሚቻለው፤ የሕግ የበላይነትን ማስከበር የሚቻለው በጋራ ነው፤ እኛም የእዛው አካል ስንሆን ነው፤ የአንዱ መብት ተከብሮ የሌላው ተጥሶ ሊሆን አይችልም! አንደኛው የሕገ-መንግስት ክፍል ተከብሮ ሌላኛው ተደፍጥጦ ሊሆን አይችልም! ሰላምን ነው የምንዘምረው! ለሰላም ነው የምንታገለው! ጥያቄያችንን በሰላማዊ መንገድ እንሄድበታለን!››
ኢትዮሚድያ -- Ethiomedia.com
Subscribe to:
Post Comments (Atom)
No comments:
Post a Comment