ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት ሴራ
(ቅዱስ ሃብት በላቸው)
ድርጊቱ ከተፈፀመ ዓመታት ቢቆጠሩም የጊዜ ርዝመት የሚያደበዝዘው ነገር አይደለምና ዛሬ የትውስታዬን ማህደር ጎርጉሬ ይህንኑ ላካፍላችሁ ወደድኩ። በአንድ ወቅት የፋሺሽት ኢጣሊያ ጦር ለጨፈጨፋቸው ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ መሃል አዲስ አበባ 6 ኪሎ ላይ የቆመው ታሪካዊው የሰማዕታት ሃውልት ለምን እንደሆነ ለህዝብ ሳይነገር ድንገት ዙሪያውን ይታጠርና ተሸፍኖ ከእይታ እንዲሰወር ይደረጋል።
በርግጥ በወቅቱ አጥብቆ ለጠየቀ ሰው የታጠረው ለእድሳት እንደሆነ ቢገለጽለትም ይህ ምክኒያት ግን በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነትን አላገኘምና የሚደረገውን ነበር በሩቅ ሆነው በአንክሮ የሚከታተሉ ሰዎች ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም። በርግጥ የብዙዎች ስጋት ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተጣላውና የአገራችንን ሰንደቅ ዓላማ “ጨርቅ!” እያለ በሚያንቋሽሽ ሰው የሚመራው የሕወሃት መንግስት የቀዳማዊ ኃይለስላሴን ምስል ሊያነሳው ይችል ይሆናል የሚል ነበር።
ከቀናት ቆይታ በኋላ ከአጥሩ ውስጥ ውር ውር ሲሉ የሰነበቱት ጥቂት ሰዎች ስራቸውን ጨርሰውና መከለያቸውንም አፈራርሰው ዞር ሲሉ ጉዳዩን በትኩረት ሲከታተል የነበረው ጋዜጠኛ አበራ ወጊ ወደሃውልቱ ያመራል። (ጋዜጠኛ አበራ ወደ በሃገራችን ሰፊ ተቀባይነት ከነበራቸው የነፃ ፕሬስ ጋዜጦች አንዷ የሆነችው የማዕበል ጋዜጣ አዘጋጅ የነበረ ሲሆን አሁን በስደት አሜሪካ ውስጥ ይኖራል።) እንደደረሰም በቅድሚያ ዓይኑ የተወረወረው የቀዳማዊ ኃይለስላሴ ምስል ወደተቀመጠበት የሃውልቱ አካል ነበር። እንዳለ ነበርና ተንፈስ አለ። ወደ ሌላ አቅጣጫ ዞሮ በዓይኑ ሌላ ነገር ፍለጋ ሲማትር ግን ሃውልቱ ሲሰራ በላዩ ላይ ከተቀረፁት ፅሁፎች መካከል አንዱ እንደሌለ አስተዋለ። ይህ ጽሁፉ እንዲህ የሚል ነበር….
“ቢነገር፣ ቢወራ፣ ቢተረክ፣ ቢፃፍ፤
ፍፃሜ የለውም፣ የፋሺሽቶች ግፍ።”
በርግጥ ይህ ሃውልት በቀጥታ ተያያዥነት ያለው ከሰባ ዓመታት በፊት በአገራችን እጅግ ዘግናኝ ግፍ ከፈፀመው የፋሺሽት ኢጣሊያን ጦር ጋር ነው። ስለዚህም በሃውልቱ ላይ የሰፈሩት ፅሁፎች በሙሉ ይህንኑ አረመኔ ወራሪ ጦር የሚመለከቱ እንጂ፣ ትናንት ትግራይ ጫካ ውስጥ ተወልዶ የአገራችን ጠላቶች እየተንከባከቡ ያሳደጉትን አገር በቀሉን ፋሺሽት ሕወሃትን የሚመለከት አይደለም። ነገር ግን የሕወሃት መሪዎች ግን ፅሁፉን አልወደዱትምና ስራዬ ብለው በመነሳት ፅሁፉ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል ከተቀመጠበት ስፍራ ላይ እንዲፋቅ አደረጉ።
ታዲያ ይህ ፅሁፍ ከሃውልቱ ላይ ቢፋቅም፣ ከኢትዮጵያውያን ልብ መፋቅ አይኖርበትም ያለው ጋዜጠኛ አበራ ወጊም ይህንኑ በማዕበል ጋዜጣ ለህዝባችን ይዞት ይቀርባል። ሆኖም ጉዳዩ አንድ ሰሞን “ጉድ ! ጉድ!” ተባለለትና በዚያው ተዘንግቶ ቀረ። እንዲያውም ቂመኞቹ ወያኔዎች ተሸሽገው የሰሩትን ታላቅ የቅርስ ውድመት ተከታትሎ ለህዝብ ያደረሰውን ይህን ትጉህ ጋዜጠኛ ወዲያውኑ እስር ቤት በመወርወር ቁጭታቸውን ለማስተንፈስ ሞከሩ። ዛሬ ጋዜጠኛውም በስደት ሃገር ሲኖር፤ ሃውልቱም ያለዚህ ፅሁፍ ቆሞ ይገኛል። ምናልባት ሌሎችም ነገሮች ከሃውልቱ ላይ ተነስተው ይሆናል!
ምን ይሄ ብቻ!! ከአንድ ወር በፊትም በአገር ውስጥ ብዙዎቻችንን ያስገረመና ያሳዘነ ነገር መፈፀሙ የሚዘነጋ አይደለም። ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ ፋሺሽት ኢጣሊያ አገራችንን በወረረችበት ወቅት የጦሩ አዛዥ የነበረና በሚልዪን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ያስጨፈጨፈ አረመኔ እንደሆነ ይታወቃል። እንዲያውም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ይህ ሰው በዓለም አቀፍ ችሎት ቀርቦ የ12 ዓመት እስራት የተፈረደበት ብቻ ሳይሆን ስሙም በጦር ወንጀለኞች መዝገብ የሰፈረ ነው። ይህ ሁሉ እየታወቀ ታዲያ በቅርቡ ኢጣሊያ ውስጥ ለርሱ መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ቤተመዘክርና የመናፈሻ ቦታ ተሰርቶ በስሙ ተሰይሞለታል።
ይህ ያስቆጣቸው ኢትዮጵያውያን ተሰባስበው መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም በሕጋዊ መንገድ በአዲስ አበባው የኢጣሊያ ኤምባሲ ፊት ለፊት መጋቢት የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ሲያደርጉ፣ የህወሃት መንግስት ሰልፈኞቹን ሰብስቦ በማሰር ለፋሺሽቱ ጦር ያለውን አጋርነት ዳግም አስመስክሯል። በርግጥ ብዙዎቻችን ጠንቅቀን እንደምናውቀው ታላላቆቹ የህወሃት መሪዎች የተገኙት ለሆዳቸው አድረው አገራችንን በድፍረት ከወረረው የፋሺሽት ኢጣሊያ ጦር ጋር በመወገን ብዙ ጥፋትና ውድመት ካደረሱ ባንዳዎች ጉያ ነው።
ሰሞኑን ደግሞ የዘንድሮውን የትንሳዔ በዓል ድምቀት ያደበዘዘ ሌላ “ጉድ ! ጉድ!” የምንልበት አዲስ ክስተት አጋጥሞናል። እንደሚታወቀው አዲስ አበባ ላይ ሊሰራ የታቀደው የባቡር ሃዲድ ግንባታ የታላቁን ኢትዮጵያዊ አርበኛ፣ ሰማዕትና የሃይማኖት አባት የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሃውልት ካልተነሳ እንዴት ተደርጎ! በማለቱ በፀሎተ ኃሙስ ዕለት ይኸው ሆኗል። በርግጥ እቅዱ ለህዝብ ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ የማህበረሰባችን ዋነኛ ጥያቄ የነበረው “የባቡር ሃዲዱ ለምን ሃውልቱ በቆመበት ስፍራ እንዲሄድ ተፈለገ? ሌላ አማራጭ አቅጣጫ ጠፍቶ ነው ወይ?” የሚል ቢሆንም ከመንግስት ወገን የተሰጠው ምላሽ ግን “ግንባታው ሲጠናቀቅ ይመለሳል” የሚልና ሙያዊ አስተያየት ያልታከለበት ነበር። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ቅርሶችን እያወደመ፣ ይህንን የተቃወሙትንም እያሰረ፣ እያሳደደና እየገደለ ካለንበት ከደረሰው ከሕወሃት ቋሚ ባህሪ በመነሳት ብቻ ሳይሆን፣ ባቡርን ያህል ነገር ባጠገቡ እየተምዘገዘገ፣ ይህንኑ የአቡነ ጴጥሮስን ሃውልት ሕይወታቸው ባለፈበት በዚሁ ታሪካዊ አደባባይ ላይ ዳግም እናየዋለን ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው እላለሁ።
ሃውልቱ ሲነሳ ቦታው ድረስ በመሄድ የታዘቡት ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው በዕውቀቱ ስዩም በፌስ ቡክ እንዳካፈለን ከሆነ በዕለቱ የሚደረገውን ነገር ቆሞ ከሚያየው ሰው ይልቅ የፌዴራል ፖሊሱ ቁጥር ይበልጥ ነበር። ሕዝባችን በዚሁ ጉዳይ ከወራት በፊት የነበረውን የተቃውሞ ጉም ጉም አስታውሶ ወይ ረብሻ ይከሰት ይሆናል ብሎ ፈርቶ ቀርቷል፣ ወይንም በየቤቱ ሆኖ ስለ ስለመጪው የትንሳዔ በዓል፣ እንዲሁም እጅግ ስላሻቀበው የዶሮና የእንቁላል ዋጋ፣ አብዝቶ በመጨነቅ ላይ ነው፣ አለያም በየቤተክርስቲያኑ ደጅ በፀሎት እየተጋ ነው ያለው። ለሶስት ወር ያህል ሲያለማምደን ቆይቶ እኛም አንድ ሰሞን ተንጫጭተን ስለተውነው አመቺ ጊዜ ጠብቆ በክሬን ያስፈነቀለውን ሃውልት ወስዶ ብሄራዊ ሙዚየም ውስጥ ዘግቶበታል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን በመገናኛ ብዙሃን ከሰነዘሩ ሰዎች መካከል በእጅጉ የገረመኝና ያሳዘነኝ ግን የጠቅላይ ቤተክሕነት ዋና ፀሃፊ የሆኑት ብፁእ አቡነ ሕዝቅዔል ከኢሳት ራድዪ ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ምላሽ ነው። (May 2/2013) አቡነ ህዝቅዔል “ለልማት ስለሆነ ችግር የለውም” በማለት ነበር በመንግስት አፍ የመለሱት። እንዲህ አይነቱ ምላሽ እንኳንስ የቤተክርስቲያኗ አስተዳዳሪ ተብሎ ከተሾመ የሊቀ ጵጵስና ማዕረግ ካለው አባት አይደለም፣ በደጀ ሰላም ካደገ ተራ ምዕመንም እንኳን የሚጠበቅ አልነበረም። በርግጥ አቡነ ሕዝቅዔል ከቀናት በፊትም (Apr 30/2013) በዋልድባ መነኮሳት ላይ እየተፈፀመ ስለሚገኘው ፀሃይ የሞቀው በደልና ግፍ ዙሪያ በዚሁ ራድዪ ጣቢያ ተጠይቀው ሲመልሱ “እማምላክን! ምንም የማውቀው ነገር የለም! ገና ካንተ መስማቴ ነው” ሲሉ በመሃላ ጭምር በድፍረት ተናግረው ነበር። አወቁም አላወቁም ከተጠያቂነት ሊያመልጡ የሚችሉበት መንገድ የለምና፣ እንዲህ አይነቱ ምላሽ “የጠቅላይ ቤተክህነት ስራ አስኪያጅ” ተብሎ ከተሾመ እንደርሳቸው ሊቀ ጳጳስ የሚጠበቅ አልነበረም። ይህ ደግሞ እንደ አቡነ ጴጥሮስ ለእውነት ሲል ራሱን ለመስዋዕትነት የሚያቀርብ አይደለም፣ ሕዝብ የሚያውቀውን እውነት እንኳን በአንደበቱ ለመመስከር የሚደፍር የሃይማኖት አባት ማጣታችን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን ቤተክርስቲያናችን በምን አይነት ሰዎች እየተዳደድረች እንደምትገኝ የሚያመላክት ነው።
ገና የአገሪቷን ስልጣን በሃይል እንደተቆናጠጠ ተንደርድሮ መቶ ብር ላይ የነበረውን የአርበኛ ምስል በማንሳት ኢትዮጵያን ጠብቀው ላቆዩልን ቀደምት አባት እናቶቻችን ያለውን ጥላቻ በግልጽ ያሳየን ህወሃት፣ ከሁለት አሰርት ዓመታት በኋላ እንኳን በውኑ ዓለም ያሉ የማንነታችን መገለጫ የሆኑ ቋሚ ቅርሶቻችንን ከማውደም የተቆጠበበት ጊዜ የለም። ለወደፊቱም ቢሆን ይህን ባህርይውን ይተወዋል ተብሎ አይታሰብም። በዚህም መሰረት ቀጣዩ ተልዕኮው የደብረ-ጽጌ (አራዳ)ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ፊት ለፊት የሚገኘውን የአጤ ምኒልክ ሃውልትን በልማት ስም ማስወገድ ሊሆን ይችላል። ገና በረሃ ሳለ ጀምሮ በርካታ አብያተ ክርስቲያናትን የዘረፈና ያወደመ፣ ዛሬ ደግሞ እድሜ ጠገቡን የዋልድባ ገዳም በልማት ስም የደፈረ አካል ነገ የቅዱስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን ላፍርስ ብሎ ላለመነሳቱ ምን ማስተማመኛ አለን? እንዲህ አይነቱን ጥፋት ለመከላከል በ1984 ዓ.ም የተቋቋመው የአገር ቤቱ “የኢትዮጵያ ቅርስና ባለአደራ ማህበር” እንዲያውም የጥፋቱ ዋነኛ ተዋናይ መሆኑን ነው የምናውቀው። ከሳምንታት በፊት እንኳን የአዲስ አበባዋን የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን ይዞታ የሆነውን ደን ጨፍጭፎ ለመሸጥ ያወጣውን ጨረታ በመቃወም ቤተክርስቲያኗ በፍርድ ቤት ክስ መስርታ እንደነበር ይታወሳል።
ስለዚህም አንድ ነገር በተከሰተ ቁጥር በተናጠል የምናሰማው ጩኸት ውጤት አላስገኘልንምና በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር የምንኖር ኢትዮጵያውያን ተደራጅተን እየወደሙና እየተዘረፉ ያሉት የአገራችን ቋሚ ቅርሶች ተጠብቀው ለተተኪው ትውልድ ባግባቡ መተላለፍ የሚችሉበትን መንገድ መቀየስ ይገባናል። በርግጥ በዚህ በኩል የማያወላዳው አስተማማኝ መፍትሄ ይህንን የኢትዮጵያዊነት ጠላት የሆነ አምባገነን ስርዓት ከስሮ መንግሎ መጣል እንደሆነ ማንም አይስተውም። ይህ እስከሚሆን ድረስ ግን ዝም ብለን መመልከት አይገባንምና በተለይም ሰሜን አሜሪካ ላይ አስቀድሞ የተመሰረተው “የኢትዮጵያዊነት ውርስና ቅርስ ማሕበር”ም ሆነ ሌሎች መሰል ተቋማት ራዕያቸውን በማስፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያውያንን አስተባብረው ለመንቀሳቀስ ቢሞክሩ የተሻለ ውጤት ሊገኝ ይችላል ብዬ እገምታለሁ።
No comments:
Post a Comment