እስከ ዳግማይ ትንሣኤ ድረስ ብዙም ረፍዷል አይባልምና የክርስትና ሃይማኖት ተከታዮች እንኳን ለ2005ዓ.ም የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ፡፡ ለቀጣዩ በዓልም ሁላችንንም በሰላም ያድርሰን፡፡
ዛሬ ዕለቱ የፋሲካ ማግሥት ነው፡፡ ያ ሁሉ ግር ግርና ወከባ የታየበት ሃይማኖታዊ በዓል የአንድ ዓመት ዝግጅት የፈጀ እንዳልመሰለ በአንድ ቀን ማግሥት አለቀና ብዘውን ሰው ኦና ቤት አሸክሞ አለፈ፡፡ የወጉን ለማድረስ ከዘመድ አዝማድ የተበደረውንና የተለቀተውን፣ ከመሥሪያ ቤቱ ብድር በመጠየቅ ተዝቆ የማያልቅ ዕዳ ውስጥ የገባውን፣ በውጪም በሀገር ቤትም ከሚገኝ በሀብት የተሻለ ዘመድና ጓደኛ ገንዘብ ቀለዋውጦ ቤቱን እንደጎረቤቱ ለማድረግ የባዘነውን፣ በልመናም በዝርፊያና በስርቆትም በሙስናና በወንጀል ድርጊትም ከሰው ላለማነስ ሲል ዕለቷን አሸብርቆና ደምቆ ለማለፍ የዋተተውን ሁሉ ዛሬ ብናየው ‹እንዲህ ልጠግብ በሬየን አረድኩ› እንዳለችው ሴት በባህል ተፅዕኖ ምክንያት በሠራው አልባሌ ነገር ትናንትን የኋሊት እየተመለከተ ሲጸጸት ልናስተውል እንችል ይሆናል፡፡ ዋናው ጉዳይ ግን ፋሲካም ብዙዎችን ዕዳ ውስጥ ነክሮ ሌሎች 364 ቀናትን ዐርፎ ሊመለስ - እንደገናም በተለመደው የሺዎች ዓመታት አዚሙ ጅሎችንና ከሃይማኖት ያፈነገጠ የሆድ ተዝካር አምላኪዎችን ሊያቂያቂል ወደሰገባው ተመልሷል፡፡ እንደወትሮው ሁሉ በሰሞኑ በዓልም ብዙ አየን፡፡
ሰውነት ሳይላላጥ፣ ኪስ ሳይራቆት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ስትኖር ሃይማታዊንም ይሁን ሕዝባዊ በዓላትን ማክበር ደስ ይላል፡፡ በመልካም ዘመን እነዚህ በዓላት እስኪደርሱ ድረስ ያቁነጠንጣል፡፡ ‹መቼ በደረሱ› እያስባለ በደስታና በሃሤት ባህር ያስዋኛል፡፡ በአሁኑ ወቅት የሚታየው ሀገራዊ ድባብ ግን የተለዬ በመሆኑ እንዲያ እንድንሆን የሚያደርግ ሳይሆን በተቃራኒው “በዓል ጥንቅር ብሎ ይቅር! ደጉን ዘመን እያስታወሰ በትዝታ ማዕበል ከሚያላጋኝ ይልቅናስ በዓል የሚባል ነገር ከነጭርሱ ባይመጣ ይሻለኛል፡፡ በዓል የሚያምረው ለባለጊዜዎች ነው፡፡ ለእነሱ ደግሞ በዓመት ሦስትና አራት ቀናት ብቻ ሣይሆኑ ሠርክ በዓላቸው ነው፡፡ ምን ሲጎድልባቸው?” በሚል ጥልቅ ሀዘን ውስጥ የሚከት አሰቃቂ ሁኔታ ነው እየታዬ ያለው፡፡
ከፍትህና ፀጥታ ጉዳዮች በተጓዳኝ የአንድ ሀገር የጤንነት ደረጃ ከሚለካባቸው ዋና ዋና መክሊቶች መካከል አንድኛው የገንዘብ የመግዛት አቅም ነው፡፡ የገንዘቡ የመግዛት አቅም እየተልፈሰፈሰ ሄዶ ዜጎች ብዙ ገንዘብ ይዘው የሚገዙት ነገር ግን ጥቂት ከሆነ በዚያ ሀገር ውስጥ አንዳች ትልቅ ችግር ለመከሰቱ ዓይነተኛ ምልክት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የቅርብና የሩቅ ጊዜ የታሪክ መዛግብት ቢፈተሹ ይህን እውነት የሚያጠናክሩ ክስተቶችን አናጣም፡፡ ለምሳሌ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ወንደላጤዎች የመኝታ ቤቶቻቸውን ግድግዳዎች በዚያን ጊዜው ፋይዳቢስ የጀርመን የገንዘብ ኖቶች እየለጠፉ ያሳምሩ ነበር ይባላል – በእጅጉ ጋሽቦ ትርጉመቢስ ሆኖ ነበርና፡፡ ሶቭዮት ኅብረት በምትፈራርስበት ወቅት አንድ ዶላር በዚያን ወቅት ጥምቡን በጣለው ሺዎች ሩብል ይተረጎም ነበር፡፡ በምዕራባውያን ማዕቀብ ክፉኛ የተመታችው ዚምባብዌ የአሁኑን እንጃ እንጂ ቀደም ሲል ከጀርመን በባሰ መልክ አንድ ኪሎ ቲማቲም ለመግዛት የሀገሪቱን ገንዘብ በዶንያ ተሸክሞ መሄድ ያስፈልግ ነበር፡፡ አሁንም የአሁኑን እንጃ እንጂ ሶማሊያ በፈራረሰች የመጀመሪያዎቹ ዓመታት ውስጥ የዚህችን ሀገር ትላልቅ የገንዘብ ኖቶች እዚህና እዚያ ወዳድቀው ማግኘት ያልተለመደ አልነበረም፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየን በነዚህ ሀገራት ውስጥ የሆነ ተስቦ ወረርሽኝ ገብቶ ሕዝቡንና መንግሥታቱን እያመሰ መሆኑን ነው፡፡ ገንዘብ ዋጋ አጣ ማለት በተዛዋሪ ሕይወት ዋጋ አጣ ማለት ነው፡፡ በምድር ለመኖር ደግሞ የገንዘብ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡ መሬት የሥጋ እንጂ የነፍስ መኖሪያ አይደለችምና ገንዘብ በቀጥታ ከደም ዝውውር ጋር የተሣሠረ ነው፡፡ ገንዘብ ባይኖር ኖሮ የአሁኑ የዓለም ቅርፅ የተለዬ እንደሚሆን ለመናገር ነቢይ መሆንን አይጠይቅም፡፡ አዳሜ የሚገዳደለውና ትርጉም በሌለው ሁኔታ የሚተላለቀው ከገንዘብ ጋር በተገናኘ ነው፡፡ የድንበር ግጭት፣ የሃይማኖት ልዩነት፣ የዘር መድሎ ወዘተ. ሽፋኖች እንጂ ትክክለኛዎቹ እውነተኛ የጠብ መንስኤ አይደሉም፡፡ ገንዘብና ገንዘብ ሊገዛው የሚችለው ማንኛውም ነገር ሁሉ አስፈላጊነቱ በአንድ ጀምበር ቢያከትም በሃይማኖት ስምም ይሁን በዘርና በቀለም ወይም በሌላ ምክንያት የተቀሰቀሱና አሁን በዓለም የምናያቸው ቁርቋሶዎች ሁሉ በአንድ አዳር እንደጤዛ በረገፉ ነበር፡፡ የሆድ ነገር ሆድን እየቆረጠ አንዱን ከአላስካ ወደ ሣይቤሪያ ይወስዳል፤ ሌላውን ከራስ ዱሜራ ወደራስ ካሳር ይነዳዋል፡፡ ሆድ መጥፎ ነው፡፡ ‹ሆዳም ፍቅር አያውቅም› መባሉም በጣም ትክክል ነው፡፡
የኢትዮጵያን ገንዘብ ስናይ በተለይ በአሁኑ ወቅትና በአጠቃላይ ደግሞ ከግንቦት 97 የጨነገፈ ሀገራዊ ምርጫ ወዲህ እጅጉን አሳሳቢ የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ የወያኔውን መንግሥት የውሸት አቅማዳነት የሚገነዘብ ወገን በወያኔ የሚደሰኮረው “ግሽበቱ ከሁለት አሃዝ ወደ አንድ አሃዝ ወረደ፤ ሕዝቦቻችን ሆይ ደስ ይበላችሁ!” ዓይነቱ ይሉኝታቢስ ቱሪናፋ አይታለልም፡፡ እውነቱ እንዲህ ነውና – እቀጥላለሁ፡፡
በሰሞኑ የዓመት በዓል ገበያ ልጀምር፡፡ ደመወዜ ከሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመለስ ዜናዊ ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡ ይሁንና እርሱ ከዚያች ከኔ ከምታንስ ወርሃዊ ምንዳው እንደምንም ቆጥቦ እንዳንዳንዶች ተጨባጭ መረጃና ግምት ከሦስት ቢሊዮን የበለጠ ዶላር ማጠራቀም ሲችልና ከዚሁ ገንዘብ የሚበልጥ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረት ሲያፈራ እኔ ዓመት በዓሉን የዋልኩት እንደሚከተለው ነው፡፡ የታሪክ ምፀትና አሽሙር ማለትም እንደዚህ ዓይነቱ ገጠመኝ ነው፡፡
ዶሮ 155 ብር – ብዙም ወፍራም አይደለም፡፡ ቀይ ሽንኩርት በጣም ቀንሶ በሰባት ብር ሒሣብ አምስት ኪሎ፡፡ ቅቤ በጣም ከመወደዱ የተነሣ ኪሎው በአማካይ ብር 190 በመግባቱ አልገዛሁም – በዘይት ተሠራ፡፡ ዕንቁላል አንዱን በብር 2፡50 ሒሣብ – ስምንት፡፡ የሥጋ ቅርጫ – ጥሩው ሥጋ – በአማካይ 1800 በመግባቱ ሦሥት ኪሎ ሥጋ በ300 ብር ገዛሁ፡፡ አረቂ ባህል ነውና ለአክፋይ መውሰድ ስለነበረብኝ ከ15 ብር ሽቅብ ወጥቶ በ70 ብር ገዛሁ፡፡ ለልጆች አዲስ ቀርቶ ልባሽ ልብስም መግዛት አልቻልኩም፡፡ በዋዜማው ከጓደኞች ጋር ለመጫወት በ‹ዳች ፔይ ሲስተም›(እኛም – ‹ጨዋታ በጋራ ክፍያ በግል› እንለዋለን) ለሦስት ጃምቦ ድራት ብር 33…
ይህን ኑዛዜ መሰል ንስሃ የምነግራችሁ ወድጄ አይደለም፡፡ እኔ ‹የወፍራም ደመወዝ› ባለቤት ሆኜ በዚህ መልክ በዓሉን በቁጥቁጥ ሳሳልፍ ከኔ የባሰው ድሃማ እንዴቱን ይሰቃይ? ስንቱ ይሆን ጥርኝ ቆሎ እያማረው ቤቱን ዘግቶ በዓሉን ያሳለፈ? እንዳይለምን እያፈረ፣ እንዳይተወው በርሃብ እየተሰቃዬ ለመኖር ሲል ብቻ በሰቆቃ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ስንቱ ይሆን? ማነው የሚያስብለት? ፈጣሪስ የት ገባ? ምን ደበቀው? ምን እያዘጋጀ ይሆን? ቁናውን ሰፍቶ ለመጨረስ ስንት አሠርት ዓመታት ይፈጅበታል?
በመሠረቱ የሀገራችንም ይሁን የዓለማችን ሀብት በሸሃኔና በግራም እየተለካ ለሁላችንም እኩል ይሸንሸን የሚል ፍላጎትም ሆነ ቅዠት የለኝም፡፡ ከፍ ሲል እንደተናገርኩት ምድር የውድድር ቦታ ስለሆነች የልዩነት መኖር የግድ ያህል ነው፡፡ ነገር ግን ሊኖረን በማይገባ የተንቦረቀቀ ልዩነት አንዱ በርሀብ ሊሞት ሲያጣጥር ሌላው በቁንጣን ሊሞት ወረፋ መያዝ ያለበት አይመስለኝም፡፡ የተናግዶታችን(transaction) ትሥሥር ሲፈተሸ በእጅጉ የተፋለሰና ለጥቂቶች ብቻ ክፉኛ ያዘመመ ነው፡፡ ሀብታሙ ለምን ሀብታም ሊሆን እንደቻለ ለማየት አይፈልግም፡፡ በድሃው ትከሻ ሚሊዮኔርና ቢሊዮኔር ከሆነ በኋላ በራሱ ብቸኛ ልፋት የከበረ ይመስለዋል፡፡ ነገር ግን ያ ስህተት ነው፡፡ እንደኔ ሀብታም ጭንቅላት ቢኖረው ኖሮ የዓለማችን ችግሮች በግማሽ መፍትሔ እንደሚያገኙ ይሰማኛል፡፡
የትም እንሂድ ሀብታም በራሱ ጥረት ብቻ ሀብታም አልሆነም፡፡ እየበዘበዘና የድሆችን ጉልበት እያለበ ነው አንድ ሀብታም ሀብታም የሚሆነው የሚል ፅኑ እምነት አለኝ፡፡ አንድ ሰው ምን ቢለፋ 60 ቢሊዮን ዶላር ሊኖረው አይችልም ወይም ቢያንስ ሊኖረው አይገባም፡፡ በፎርብስ ግምት መሠረት በዓለማችን ሊኖሩ እንደሚችሉ ከተገመቱ ሁለትና ሦስት ሺህ ቢሊየኔሮች መካከል በትክክል ሠርቶና ለሚያሠራቸው ሰዎች ትክክለኛ የላባቸውን ዋጋ ከፍሎ የከበረ ሰው ለማግኘት በእጅጉ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንድ ቢሊዮኔር ለአንድ ውሻው የሚመድበውን የወር በጀት ለአንድ ሠራተኛው ቢመድብ ሠራተኛው ዕድለኛ ነበር፡፡ ነገር ግን በአራቱም ማዕዘን ብናይ ሰዎች ለሰዎች ሲከፉና ተገቢውን የጉልበት ዋጋ ሲከለክሉ፣ እነሱ ሕዋን ሳይቀር ሲጎበኙ ሠራተኞቻቸው ግን አስፕሪን እንኳን መግዛት እያቃታቸው በህመም ሲሰቃዩ ለመመልከት ተገድደናል፡፡ ለዚህ ሳይሆን ይቀራል ክርስቶስ ‹ ሀብታም መንግሥተ ሰማይ ከሚገባ ይልቅ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል› ማለቱ?
ነገር በነገር እየተጣለፈ የት ጀምሬ ምንን ይዤ ወደየት መሄድ እንዳለብኝ ዘነጋሁት እንጂ አነሳሴ ስለኢትዮጵያ ገንዘብ መጋሸብ በመጠኑ ለማውራት ነበር፡፡ ይሁን፡፡ ዋናው ቁም ነገር፣ ቁም ነገር መናገሬ ነው – ቁም ነገር ተናግሬ ከሆነ፡፡
በሀገራችን ገንዘቡ የማሽላ እንጀራ ከሆነ ቆይቷል፡፡ ሀገሪቱ ባለቤት የሌላት እስክትመስል ድረስ በኳስ አበደች ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን፡፡የፖለቲካውን አመራር ማን ይያዘው ማን ሌላ ነገር ነው፡፡ ማንም ይያዘው ለጊዜው እሱ የማያሳስበን ዜጎች እየበዛን መጥተናል፡፡ ዝንጀሮዋ ‹ቀድሞ የመቀመጫየን› እንዳለችው ቀምሶት የሚያድረው ምናምኒት የሌለው ዜጋ ቁጥር ሀገር ምድሩን እያጥለቀለቀው በሚገኝበት ሁኔታ የፖለቲካውን ልጓም ወያኔ ይያዘው ቻይና ትጋልበን አናውቅም(ቻይና በማይረባ ሸቀጦቿ አጥለቀለቀችን! በጣት በሚጠረቆስ ቱቦላሪ ብረት፡፡)፡፡ ኢኮኖሚው ግን ክፉኛ በመናጋቱ የገንዘባችን የመግዛት አቅም ቃላት ከሚገልጹት በላይ ወድቋል፡፡ ገንዘብ ወድቆ ኢኮኖሚው ጠንክሯል የሚባለው ፈሊጥ አይገባኝም፤ ‹የኑሮ ውድነቱ መንስኤ የኢኮኖሚው ዕድገት ነፀብራቅ ነው› መባሉም መራራ ቀልድ ነው፡፡ አዲስ አበባና አካባቢዋ በወያኔ ሀብታሞችና በጫማ ላሾቻው የተገነቡ ሕይወት አልባ ባዶ ሕንፃዎች፣ የዱርዬው መንግሥት በብድርና በተራድዖ ከሚያገኘው ብዙ ገንዘብ ውስጥ ጥቂቱን በማውጣት የሚሠሩ የአስፋልት መንገዶች የኑሮ ውድነቱን ረገብ ሊያደርጉት አልቻሉም፡፡
ተመልከቱ እንግዲህ፡፡ የአንድ ሰው ዝቅተኛ መንግሥታዊ ደመወዝ ብር 400 አካባቢ ነው፡፡ በየሻይ ቤቱና ቡና ቤቱ የሚሠሩ ወገኖቻችን ደመወዝም በመጠነኛ ቲፕ ይደጎማሉ እንጂ ከዚህ የሚበልጥ አይደለም፡፡ ከጉለሌ ተነስቶ ሜክሲኮ የሚሠራ የጥበቃ ሠራተኛ አራት መቶና አምስት መቶ ብር በወር ደርሶት ምኑን ከምን እንደሚያደርገው አስቡት፡፡ ግዴለም በሌላው ትርፍ ሰዓቱም ይህንኑ ያህል ገንዘብ ሠርቶ (ሠርቆ አላልኩም!) ያገኛል ብለን እናስብና በስምንትና ዘጠኝ መቶ ብር ወርሃዊ ጥቅል ገቢ እንዴት ሊኖር እንደሚችል እናስበው፡፡
ትራንስፖርቱ ብቻ በከተማ አውቶቡስ ተጓጉዞ በወር ከ300 ብር በላይ ይፈጅበታል፡፡ ጥቁር ጤፍ 1600 ብር ነው – በኩንታል፡፡ ድሃ ደግሞ ልጅ መውለድ ይወዳልና የቤተሰቡን ብዛት አስቡት፡፡ ቤት ኪራይ በቀላሉ አይገመትም – አዲስ አበባ ላይ አንዲት ሦስት በአራት የሆነች መናኛ ክፍል ቤት ከ800 ብር በታች ማግኘት አይሞከርም፡፡ ሰው እርስ በርሱ ተባልቶ ሊያልቅ ነው፡፡ መብራት፣ ውሃ፣ ስልክ፣ ተቀማጭ፣ ሕክምና፣ ልብስ፣ የልጆች ትምህርት፣ መዝናኛ… የመሳሰለው ለአንድ ተቀጣሪ ኢትዮጵያዊ የህልም ያህል እንጂ እውን ሊሆን አይችልም፡፡ አመጋገቡም እጅግ የወረደ በመሆኑ በቁሙ ሞቱን ተሸክሞ የሚዞርና ትንሽ በሽታ ዘወር ብትልበት መቋቋም የሚያቅተው ተንጠራዋዥ ነው፡፡ የአብዛኛው ሕዝብ ችግር እንግዲህ ይታያችሁ፡፡ ብዙው ዜጋ በምጽዋትና በዲያስፖራው ድጋፍ እየኖረ እንጂ በእውነተኛው ደመወዙ መኖር ካቆመ ቆይቷል፡፡ ሠርቶ ከሚኖረው ይልቅ እንዲሁ በተዓምር የሚኖረው ይበልጣል - ብቻ ግን ይመሻል ይነጋል፡፡ ይህ የተፈጥሮ ሕግ እስካሁን አልተቀየረም፡፡ ይህን ዓይነት በመንፈስም በሥጋም በአእምሮም የደከመ ሕዝብ ማስተዳደር ለአምባገነኖች በጣም ቀላል ነው፡፡ ነገሩ የቁጥር ጉዳይ አይደለም፡፡ የደከመን ሕዝብ መቶ ሚሊዮንም ይን አንድ ቢሊዮን በቀላጤም በወንጭፍም ማስተዳደር ይቻላል፡፡ በሌሎች ሀገሮች በአንድ ወር ደመወዝ ስድስት ወራትን መኖር ይቻል ይሆናል፤ በኢትዮጵያ ግን በአንድ ወር ደመወዝ በጣም ጎበዝ የሆነ ዜጋ ለሦስት ቀናት ሊኖር ይችላል – ከልደታ እስከ ባታ፡፡ ቀሪዎቹን 27 ቀናት በምትሃት የሚኖር ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲያምጽ መጠበቅ አስቸጋሪና ተዓምር መሥራትን ይጠይቃል፡፡ ተስፋ ሁሉ ተሟጦ የመጨረሻው የምፅዓት ዘመን ሲመጣ ግን መተንበይ የሚያስቸግር ሊቢያ-ሦርያዊ ዕልቂትና ትርምስ እንደሚፈጠር ከወዲሁ መገመት አይከብድም፡፡ ያ ጊዜ መምጣቱ ለማይቀረው እስኪያልፍ ያለፋል፡፡
ለዚህ ነው አባቶች በሥነ ቃላቸው፤
“እንዲህ ጨሶ ጨሶ የነደደ እንደሆን፤
ያመዱ ማፍሰሻ ሥፍራው ወዴት ይሆን?”
በማለት የአንድን ክፉ ድርጊት የመጨረሻ መጥፎ ውጤት የሚጠቁሙት፡፡
ተቀጣሪው ዝቅተኛ ደመወዝተኛ የሚኖረው ሞቶ ነው፡፡ እኛም አለን የምንለው የምንኖረው ሞተን ነው፡፡ የሞተውን ካልሞተው ለመለየት ምናልባት ዘርህን መጠያየቅ ሳያስፈልግ የሚቀር አይመስለኝም፡፡ ኅሊና ያለህ ካልሆንክ በስተቀር ከገዢው መደብ ተፈጥረህ አትራብም ብቻ ሳይሆን ዓለም ልታቀርብ የምትችለው መልካም ነገር ሁሉ ይኖርሃል፡፡ አንፋሽ አከንፋሽ ከሆንክም በመነጽር ውስጥ እየታየህ ሊኖርህ የሚገቡ የተወሰኑ ንብረቶች እንዲኖሩህ ይደረጋል፡፡ ሀብት ንብረት ብቻ ሳይሆን መላው እስትንፋስህ በወያኔዎች ቁጥጥር መሆኑን መዘንጋት የለብህም፡፡ አንተ ምንም እንኳን ታማኝ ሎሌ ብትሆንም ‹እባብ የወጣበትን ጉድጓድ አይስትም› በሚለው ነባር ብሂል የሚያምኑት ወያኔዎች የአንተን ዘላቂ ወዳጅነትና ቀናነት የሚያዩት በጥርጣሬ ነው፡፡ እንደትሮይ ፈረስ ከተጠቀሙብህ በኋላ አሽቀንጥረው የሚጥሉበት ብልሃት አላቸው – ጥፋት ባይኖርህም እንኳን፡፡ ያም ጥፋትህ ምናልባት አማራ ሆነህ መገኘትህ ሊሆን ይችላል፡፡ አለዚያም ተስቶህ የኢትዮጵያን ስም በስስት አንደበት አቆላምጠህ አንስተህም ሊሆን ይችላል፡፡ ብቻ የዐይንህ ቀለም ካስጠላቸው የሚመዙብህ ካርድ አያጡም – ያም ካርድ የተዘጋጀልህ ገና በጧት ነው፡፡ በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ለአስተማማኝ ብልጽግናህና ኩፍስ ሕይወትህ ዋናው መሠረት የዘርህ ማንነት ነው ወዳጄ፡፡
በተረፈ ጉዳችን ብዙና እየተንተከተከም ያለ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ገቢህን በራስህ የምትወስን ከሆንክ ጌታ ነህ፡፡ ሊስትሮ ከኔ ይሻላል፡፡ ለአንድ ጫማ ከሦስት ብር ጀምረው ያስከፍላሉ፤ ግንበኛና አናጢን አረቂ ቤት የምታገኛቸው ከስንት አንዴ ነው – ‹የጥንቱ ትዝ አለኝ› ብለው ሲመጡ፡፡ ዛሬ እነሱ በቀን ከ200 በታች አይገኙም – ቢራና ድራፍት ቤት ነው መዝናኛቸው፡፡ አንተ ወደታች አንዳንዶች ወደላይ፡፡ ጊዜ ነው፡፡ አንስቶ ያፈርጥሃል ወይ አንፈራፍሮ ሲያበቃ ያነሳሃል፡፡ ተራ የጉልበት ወዛደር በቀን ከ60 ብር በታች አይቀመስም፡፡ እንዲቀንሱልህ ብትጠይቅ ‹እንዴት እንኑር?› ይሉሃል፡፡ እውነታቸውን ነው፡፡ ተራ ሽሮ በተራ ቡና ቤት 40 እና 50 ብር ነው፡፡
ሀኪም ቤት ብትሄድ ዘረፋ ነው፡፡ የመንግሥት ሀኪም ቤት በቁሙ ሞቷል፡፡ ለምትቀደድበት ሰንጢና አልኮል ራስህ ግዛ ልትባል ትችላህ፡፡ አለቃ የለ – ምነዝር የለ – ሁሉም ዘበናይ ነው፡፡ አዛዥና ታዛዥ የለም፡፡ ሰው ቢሞት ግድ ያለው የለም፡፡ የትም ሂድ ሆስፒታሉ ሁሉ ትርምስ ነው፤ በሀገሪቱ አንድም ሰው ጤናማ አይመስልህም፡፡ ልክ እንደፖሊስ ጣያውና እንደፍርድ ቤቶች ሁሉ ሀኪም ቤቶችም በሰው ጢም ብለው ነው የሚውሉ፤ ሀኪም የለም በሽተኛ ግን ሲጉላላና ሲሞት ይውላል፡፡ በግዴለሽ ህክምና የሚሞተው ደግሞ አይነሣ፡፡ አንተው ግዴለህም ተበለሻሽተናል፡፡
የግሎቹ ጋ ከሄድክ ተኝተህ ለመታከም ለአንድ አዳር የሚያስከፍሉህ የአልጋ ኪራይ ከሼራተን አዲስ ሱትሩም ዋጋ ቢበልጥ እንጂ አያንስም፡፡ ሀኪም ወደክፍልህ በገባ በወጣ ቁጥር ትራስጌህ በሚቀመጥ ወረቀት ላይ ምልክት እየጫረ ሒሣብህን ያንረዋል፡፡ ጉንፋን አሞህ ብትገባ ቁርጭምጭሚትህን ራጅ እንድትነሣ ሊያዝዙህ ይችላሉ – ‹ምክንያቱም› ይልሃል ዶክተሩን ስትጠይቀው – ‹ምክንያም የጉንፋን ጥንተ አመጣጥ ሲጠና አነሳሱ ከቁርጭምጭሚት ነው፤ እዚያ ላይ ካጣነው ብብትህ ሥር ሊገኝ ስለሚችል እሱን ራጅ እናነሳዋለን› ሊልህ ይችላል፡፡ ዋናው ለደልቃቃ ኑሯቸው የሚሆናቸውን ወፋፍም ገንዘብ ለነሱ መስጠትህ ነው፡፡ ሙያዊ ሥነ ምግባር ተቀብሯል፡፡ በነዚህ ሀኪም ቤቶች ሌላው ቀርቶ ለካርድ የምትከፍለው ብቻ የትዬለሌ ነው – ልጅህ እንዲወለድ ብትሄድባቸው ልጁን ራሱን የሰጡህ ይመስል – አንተ ከመነሻው እንዳልለፋህበት – ለአምስት ደቂቃ የማዋለድ አገልግሎት በአሥር ሺዎች እንድትከፍል ብትጠየቅ አንተም እነሱ በመሥሪያ ቤትህ መጥተው ግልጋሎትህን እንዲያገኙ ከመዛት በስተቀር የምትከስበት የሕግ አንቀጽ የለም፡፡ ሕጉ ለሌቦች ያመቸ ነው – ዘመነ ብላ ተባላ፡፡ ለጠላትህም አይሁን እንጂ ሞተህ ሬሣህ እንኳን ቢወጣ ያለ የሌለ ሒሣብ ቆልለው ሀዘንተኛን ሲያስጨንቁ ፈጣሪ መኖሩን የረሱ ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ ሁሉም ተያይዞ ሆዳም – አጋሰስ ሆኖልሃል፡፡ ይሉኝታ ጠፍቶ ሆድ ነው የነገሠው፡፡
በዚህ መሀል እየተጎዳ ያለው ድሃው ነው፡፡ በዚአከ ለዚኣየ ሀብታሙና አጭበርባሪው ርስ በርስ እየተጠቃቀመ ሲኖር መድረሻ ያጣውና የፖለቲከኞቹና የነጋዴዎቹ የአልጠግብ ባይነት ደዌ ሰለባ ሆኖ ለማያባራ እዬዬ የተጋለጠው ቀድሞ ንዑስ ከበርቴ ይባል የነበረውን የማኅበረሰብ ክፍል ጨምሮ ወደታች ያለው ሕዝብ ነው፡፡ የንግድ ሥርዓት የለም፤ የመንግሥት ሥርዓት የለም፤ ሀገሪቱ በደመነፍስና በስሜት ብቻ እየተነዳች ናት፡፡ ይህ የዕውር ድንብር ጉዞ እስከመቼ እንደሚቀጥል በግልጥ አናውቅም፡፡ ግን ይህም የሚያልፍ መሆኑ እርግጥ ነው፡፡ ሲያልፍ ግን ወዮ ለመዥገሮችና ለትኋኖች! የአልቅቶች ዘመን ያቃል፡፡ የፍየል ዘመን እያበቃ ነው፤ የበጎች ዘመን እየመጣ ነው፡፡ ያኔ በሠፈሩት ቁና መሠፈር አይቀርምና ልብ ያለው ልብ ይበል፡፡ ሆድ መጥፎ ነው፡፡ የሚያስርበንም ሆነ የሚያጠግበን ሆዳችን ነው፡፡ ለሆድ መኖርን አቁመን ለኅሊናችን መኖርን ካልጀመርን ቆመንም ሞተንም ሙታን ነን፡፡ በአንዲት እንጀራ ለሚቆዘር ሆድ ብለን ሚሊዮኖችን ብናስለቅስ መጨረሻችን እንደማያምር ግልጽ ሊሆንልን ይገባል፡፡ በድጋሚ መልካም ዐውደዓመት፡፡
No comments:
Post a Comment