Monday, May 13, 2013

የእነ መላኩ ፈንታ ጉዳይ… (በተመስገን ደሳለኝ)


እነ መላኩ ፈንታ ጉዳይ… (በተመስገን ደሳለኝ)

ከአንድ ወዳጄ ጋር ሃያ ሁለት አካባቢ ምሳ በልተን ስናበቃ እንደሌላው ቀን ሹፌሬ ስላልነበር በኮንትራት ታክሲ ወደቤቴ (አሲምባ) አመራሁ፡፡ ታክሲው በውለታችን መሰረት የቀበናን አደባባይ ዞሮ ሲቆም፣ እኔም ሂሳቤን አወራርጄ ወረድኩ፡፡ ሆኖም ጥቂት እርምጃ እንደተራመድኩ ያላስተዋልኳቸው ሁለት ሰዎች አጠገቤ ደርሰዋል፡፡ በዕድሜ እኩዮቼ ይመስላሉ፡፡ አንዱ ቀጭንና ቀውላላ ነገር ነው፤ ሌላኛው ደግሞ ቁመቱ መካከለኛ ሆኖ፣ ደልደል ያለ ሰውነት አለው፤ ሁለቱም ‹‹ጠይም›› የሚባሉ ናቸው፡፡ ቀውላላው፡-ዜናን በጨዋታ፤ የተሜን ድምፅ ሰማሁት!

‹‹ሰላም ተመስገን!›› አለኝ፣
‹‹ሰላም!›› መለስኩኝ፡፡
‹‹ልናናግርህ ፈልግን ነበር?››
‹‹ይቅርታ አላወኳችሁም፡፡››
‹‹አንተ አታውቀንም! እኛ ነን የምናውቅህ››
‹‹የት ነው የምታውቁኝ? ማለቴ በምን መልኩ…››
‹‹እሱን ተወው! የእኛ ማንነትንም እንድንነግርህ አትጠብቅ፣ ይገባሃል ብለን እናስባለን!›› አለ እስከአሁን ዝም ብሎ የነበረው ደልዳላው ሰው፡፡ ሆኖም ቀውላላው ጓደኛው አቋርጦት ቀጠለ፡-
‹‹ ምን መሰለህ? ሰሞኑን እነ መላኩ ፈንታ እንደታሰሩ ታውቃለህ፤ እናም የእነርሱ ጉዳይ የእኛ ብቻ ነው፤ አንተን አይመለከትህም፡፡››
‹‹አልገባኝም! ይህ ምን ማለት ነው?››
‹‹በቃ! በዚህ ጉዳይ ላይ ትንተና፣ ማብራሪያ እፅፋለሁ ምናምን እያልክ አትድከም ለማለት ነው!›› ቆጣ ባለ መልኩ መለሰልኝ-ደልዳላው ሰው፡፡
ከትከት ብሎ መሳቅ አማረኝ፤ በጣም መሳቅ! ሆኖም ለምን እንደሆነ አልውቅም-አልሳቅኩም፡፡ በግልባጩ ድንገተኛ ንዴት በመላ ሰውነቴ ሲሰርፅ ታወቀኝ፡፡ ከሰከንዶች በኋላም እስከአሁን ሲናገር ትህትና ያልተለየው ቀውላላው ሰው እንዲህ ሲል አግባባኝ፡-
‹‹እየውልህ፣ መንግስት ሰዎቹን ያሰረው በወንጀል ላይ በመሰማራታቸው ከመሆኑ በተጨማሪ ለህዝብና ለሀገር ጥቅም ነው፤ ስለዚህም ገና ፍርድቤት ስለሚቀርቡ፣ ምርመራውም ስላላለቀ አንተ በፅሁፍህ ተሳስተህ፣ ለሌሎችም የተሳሳተ መረጃ እንዳታስተላልፍ ለመምከር ነው፡፡››
‹‹ስለምክራችሁ በጣም አመሰግናለሁ! ነገር ግን እኔ የምሰራውን አውቃለሁና ለስራዬ መካሪ አያስፈልገኝም›› ስል ባለመካከለኛ ሰውነቱ አቋረጠኝና፤ ከቅድሙ በባሰ የቁጣ ቃል መናገሩን ቀጠለ፡-
‹‹ስማ! ልንመክርህ ወይም ልናባብልህ አይደለም የመጣናው፤ በቃ በማያገባህ ጉዳይ መግባት እንደሌለብህ ልንነግርህ ነው!››
ይህን ጊዜም አነጋገሩ በስሱ አስቆጣኝና፡-
‹‹እየወልህ! እናንተ ማንም ብትሆኑ ግድ አይሰጠኝም፤ ኋላ ኪሳችሁ ያለው መታወቂያም አያሳስበኝም፡፡ እስከዛሬ ድረስ የማደርጋትን እያንዳንዷ ነገር አስቤበትና አምኜበት ነው፤ ማስፈራሪያችሁ እኔ ጋ ቦታ የለውም፡፡ ምናልባት ‹ይህንን ጻፍ፤ ይህንን አትጻፍ› ስትሏቸው ትዕዛዛችሁን በመፈፀም ያስለመዷችሁ ጋዜጠኞች ካሉ ወደእነርሱ ልትሄዱ ትችላላችሁ›› ብዬ
መንገዴን ልቀጥል ስል፣ ትሁቱና ቀውላላው ሰው፡-
‹‹ተመስገን ብታስብበት መልካም ነው!›› አለ፣
‹‹ምንም የማስብበት ነገር የለም፤ ይልቅ አለቃችሁን ንገሩት፣ ሰሞኑን እንደናንተ አይነት ፀጉረ ልውጦች በቤቴ አካባቢ በዝተዋልና ሰብስብልኝ፣ ይሄ አንድም ስራ መፍታት ነው፤ ሁለትም የሀገር ሃብት ማባከን ነውና! ብሎሀል በሉት››
…ከዚህ በኋላ ቤቴ ገብቼ ስለገጠመኜ ማሰብ ስጀምር መልስ የሚያስፈልጋቸው ጥያቄዎች በአእምሮዬ ተመላለሱ፡- በዚህች ሀገር ላይ ምን እየተደረገ ነው? እነማን፣ በእነማን ላይ እያሴሩ ነው? መላኩ ፈንታ የታሰረው እውነት በሙስና ብቻ ነውን? ኢህአዴግስ ዕውን ሙስናን ለመከላከል ቆረጦ ተነስቷል?አሁን ማ ይሙት በሙስና መጠየቅ ከተጀመረ መላኩ ነው የመጀመሪያ የሚሆነው? ወይስ…
(የሆነ ሆኖ ይህችን የሞነጫጨርኩት ‹‹አይመለከትህም!›› ያሉኝ ሰዎች እንደሚመለከተኝ ይረዱ ዘንድ ነውና፣ በቅርቡ በስፋት የምመለስባቸውን የመነሻ ሃሳቦች አስቀምጬ ልሰናበት)
1. መላኩ ፈንታ በባህርዳሩ ስብሰባ ላይ ‹‹የህወሓት ስውር እጆች›› እንደሚደግፋቸው የሚነገርላቸውን ሁለት መቶ ነጋዴዎች በስም ጠቅሶ ‹‹አላሰራ አሉኝ፤ አስቸገሩኝ!›› ብሎ ሪፖርት ማቅረቡ ያስቆጣው አካል በእስሩ ላይ መኖር አለመኖሩን፤ አዜብ መስፍን በዛው ጉባኤ ላይ ‹‹መለስ ብቻ ነው በደሞዝ የኖረው›› የሚል ጥቆማ ከማቅረቧ ጋር ተያያዥነት አለው ወይስ የለውም?
(ስለሰውየው ብቃትና ከሙስና የፀዳ ስለመሆኑ በስፋት ይነገር እንደነበር አውቃለሁ፤ በአናቱም የኢህአዴግ አመራር ሆኖ ከሙስና የራቀ ይኖራል ብሎ ማሰብ በእጅጉ ይከብዳል፡፡ በእርግጥ ‹‹የመላኩ ችግር›› ተብሎ ሲነገር እስማ የነበረው ከመልከ መልካምነቱ ጋር ተያይዛ የምትነሳ ጉዳይ ነች-ቶሎ በፍቅር መሸነፍ፡፡ በነገራችን ላይ መላኩ ከሆኑ ጊዜያት በፊት ዱባይ ውስጥ የመኪና አደጋ ደርሶበት እንደነበረ ይታወሳል፡፡ ለስራ ጉዳይ ሄዶ ግን አልመሰለኝም)
2. መቼም የማይካደው ሀቅ መላኩ ፈንታ ለፓርቲው ባለውለታ መሆኑ ነው፡፡ ይኸውም በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ ኢህአዴግ ‹‹አይደግፉኝም›› ያላቸውን ነጋዴዎች የተለያየ ምክንያት እየለጠፈ እንደአኮሰመናቸው ይታወሳል፡፡ ይህንን የስራ ሂደት ካሳኩት ‹‹ዋነኞቹ አስፈፃሚዎች›› መካከል ደግሞ እርሱ ይመራው የነበረው መስሪያ ቤት ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ እናም እዚህ ጋር የሚነሳው ጥያቄ ዛሬ መላኩ ፊቱን ከጠላት ወደወዳጅ (የስርዓቱ አውራ ጣት ወደሆኑ ነጋዴዎች) ማዞሩ የመዘዘው ጦስ በድርጅቱ ውስጥ ለተፈጠረው ልዩነት ‹‹መያዣ›› (የአብርሃም በግ) አድርጎት ይሆናል ብሎ መከራከር ይቻል ይሆን? መላኩስ ይህንን ጥያቄ ያቀረበው በራሱ ተነሳሽነት ነው? ወይስ ‹‹አይዞህ›› ብሎ አደፋፍሮት ሲያበቃ የከዳው ቡድን አለ?
3. በኢህአዴግ ውስጥ የእስክንድር ነጋ ጉዳይ ልዩነት ፈጥሯል፡፡ እነ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ እንዲፈታ ይፈልጋሉ፡፡ ብአዴንም ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ ይህንን ሃሳብ ይደግፋል፡፡ እናም እነዚህ ልዩነቶች መስፋታቸው ይሆናል ሁለት የብአዴን አመራር አባል የሆኑ ሚንስትሮችን በአንድ ሳምንት ውስጥ ‹‹የነቀላ››ው ሰላባ አድርጓቸው ይሆን?
4. እንዲህ አይነቱ እስር እና ድንገት ከሃላፊነት መባረር በመላኩና በብርሃን ብቻ ይቆማል? ወይስ ይቀጥላል? ከቀጠለስ ወደ እነማን ያመራል?
ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን ለማስከበር ማንኛውንም መስዋዕትነት መክፈል የሁላችንም ግዴታ ነው!

No comments:

Post a Comment