ችግሩ ውስብስብ ስለሆነ መንግሥት በአስቸኳይ ጣልቃ ይግባ ብለዋል
September 5, 2013 06:04
በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሚኖሩ ከ2,500 በላይ ደንበኞች የአክሰስ ሪል ስቴት መሥራች፣ ሥራ አስኪያጅና የቦርድ ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ኤርሚያስ አመልጋን፣ በጋራና በአንድ አቋም ሆነው ለመፋረድ ነሐሴ 26 ቀን 2005 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ባደረጉት ስብሰባ ተስማሙ፡፡
ቤት ገንብተው ሊያስረክቧቸው ባደረጉት ስምምነት ሩብ፣ ግማሽና ሙሉ ክፍያ መፈጸማቸውን የሚናገሩት ደንበኞች፣ አቶ ኤርሚያስን በጋራ ለመፋረድ የተስማሙት፣ ገንዘባቸውን ለማስመለስ በተናጠል ወደ ፍርድ ቤት መሄዳቸውንና የሪል ስቴቱ ንብረት ነው በሚል ንብረት ለማሳገድ ወይም የኪሳራ ውሳኔ ለማስወሰን መንቀሳቀሳቸውን በመተው፣ አቋማቸውን አንድ በማድረግና በመስማማት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የተወሰኑት በተወካዮቻቸው፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ራሳቸው በስብሰባው ላይ በመገኘት በቅርቡ ከተሰየመው ቦርድና ቤት ገዢዎችን በመወከል የተቋቋመው ዓብይ ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርት ካዳመጡ በኋላ፣ አቶ ኤርሚያስ የሠሩት ሥራ ውስብስብና በእነሱ መቼም ቢሆን ሊፈታ እንደማይችል በመተማመን መንግሥት ጣልቃ እንዲገባላቸው በጋራ ለመጠየቅ ተስማምተዋል፡፡
በጠቅላላ ስብሰባው ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ጨምሮ አሥር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እንዲገኙላቸው ጠርተው እንደነበር የገለጹት ኮሚቴዎቹ፣ በስብሰባው ላይ የተገኙላቸው የፍትሕ ሚኒስቴርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተወካዮች ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ ተወካዮቹም የተበደሉትን ወገኖች ስሜት በመመልከት በጉዳዩ መንግሥት ጣልቃ እንደሚገባበት ቃል እንደገቡላቸው አክለዋል፡፡
አቶ ኤርሚያስ እዚህ ባሉ ወኪላቸው አማካይነት እንደገለጹላቸው፣ በደረቅ ቼክ ምክንያት ተመሥርተውባቸው ከነበሩት አራት ክሶች ሦስቱን አዘግተዋል፡፡ የሚቀራቸው አንድ ክስ ነው፡፡ ይኼንንም ለማዘጋት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚፈጽሙና የሠሩት ሥራ ወንጀል መሆኑን ማመናቸውን፣ ቤት ገዢዎቹ ተባብረዋቸውና የመንግሥት አካላትን ጠይቀውላቸው ምሕረት ካደረጉላቸው፣ ወደ አገር ቤት ተመልሰው የችግሩ መፍትሔ አፈላላጊ ሊሆኑ እንደሚችሉ መናገራቸውን ኮሚቴው ገልጿል፡፡
የአክሰስ ደንበኞች እንደሚሉት በአሁኑ ጊዜ ዓለም አንድ መንደር በመሆኗ፣ እንኳን ግለሰብ ማንም ቢሆን በአንድ አገር ውስጥ ወንጀል ፈጽሞ በሌላኛው አገር የሚደበቅበት ጊዜ አይደለም፡፡ በመሆኑም አቶ ኤርሚያስ ይኼንን ተገንዝበው በመመለስ የመፍትሔው አካል መሆን አለባቸው ይላሉ፡፡ የማይመጡ ከሆነ መንግሥት ወይም የፌዴራል ፖሊስ በኢንተርፖል አማካይነት እንደሚያስመጣቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
እያንዳንዱ ቤት ገዥ በተለያየ አገር ተሰዶ ያጠራቀመውን ጥሪት ለልጆቹ በማሰብና በአገሩ ተመልሶ ለመኖር ካለው ጉጉት የተነሳ ክፍያ በመፈጸሙ፣ ችግሩ መከሰቱን ሲሰማ ሁሉም በየፊናው ወደ ፍርድ ቤት ማምራቱን ኮሚቴዎቹ ገልጸዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ የፈጸሙት ድርጊት ውስብስብ ማለትም አንድን ንብረት በአራትና በአምስት ቦታ አያይዘውት ስለሄዱ፣ ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሳይሆን ለሁሉም ተጐጂ ዜጐች መፍትሔ ሊያስገኝ የሚችለው መንግሥት ጣልቃ በመግባት አስተዳደራዊ መፍትሔ ሲሰጥ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ሁሉም ተጐጂዎች በየግላቸው ወደ ፍርድ ቤት በመሄድ የኪሳራ ውሳኔ ለማስወሰን መሯሯጣቸውን ትተው፣ በአንድ አቋም መንግሥትን እየተማፀኑ መሆናቸውንም ኮሚቴው አስታውቋል፡፡
መንግሥትና የኢትዮጵያ ሕዝብ በደላቸውን እንዲሰማላቸው ሰላማዊ ሠልፍ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ያለው የመንግሥት ምላሽም አስደሳችና ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ (ምንጭ: ሪፖርተር
No comments:
Post a Comment