ከአንድነት ፓርቲና ከ 33ቱ ፓርቲዎች የተሰጠ መግለጫ
አንድነት ፓርቲ ከ33ቱ ፓርቲዎች ስብስብ ጋር በመሆን ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ ለማድረግ ያቀዱት ሰላማዊ ሰልፍ በገዢው ፓርቲ (መንግስት) ክልከላ ሠልፉ ሊደረግበት ወደነበረው መስቀል አደባባይም ሆነ በአማራጭ ነት ያቀረቡት 9 አደባባዮች እንዳይንቀሳቀስ ተደርጎ ከአንድነት ፓርቲ ጽ/ቤት እስከ ቀበና አደባባይ ባለው አስፋልት ላይ ቁጥሩ ከ80 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተገኙበት ደማቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ ተደርጓል፡፡
ለዚህ ደማቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ የአንድነት ፓርቲና የ33ቱ ፓርቲዎች አመራሮች አባላትና ደጋፊዎች ያደረጉት ያላሰለሰ ጥረትና ሕዝቡ የመንግሥትን ፀጥታና የፖሊስ ኃይሎች ማስፈራራት አልፎ የላቀ አዎንታዊ ምላሽ ከፍተኛ ድርሻ አበርክተዋል፡፡ የአንድነት ፓርቲና የ33ቱ አመራር ህዝቡ ለሰጠው አመርቂ ምላሽ ከፍ ያለ ምስጋና እያቀረቡ፣በቀጣይ ለሚደረገው ወሳኝ ትግል ታላቅ የማበረታቻ እርሾ መሆኑን ያምናል፡፡ ከዚህም ሕዝቡ አመራር ካገኘ ለመብቱና ነፃነቱ ወደ ኋላ የማይል መሆኑንና በሕዝቡ ውስጥ ከፍተኛ የለውጥ ፍላጎት መኖሩን ያረጋገጥንበት፣ ትዕይንት ሲሆን በተጨማሪ ሠላማዊ ትግል በጋራ አመራር ከተያዘ ውጤታማ መሆኑን አምነናል፡፡
ሆኖም ከዚህ ሕዝባዊ ንቅናቄ የተማርነው ሌላ ነገር ቢኖር በአገራችን ያለውን የአስተዳደርና የህግ ጉዳይ ጥያቄ ውስጥ መውደቁንና ገዢው ፓርቲ በየትኛውም ደረጃ በሕዝብ በሚነሱ ጥያቄዎች በከፍተኛ ሥጋት ውስጥ የወደቀ መሆኑን ነው፡፡
የአዲስ አበባ መስተዳድርና የፌዴራሉ መንግሥት ለሰልፉ ዕውቅና ሰጥቻለሁ ቢልም የተለያዩ አስተዳደራዊ ደንቃራዎችን በመፍጠርና የማናውቃቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በመፍጠር የቅስቀሳ ሥራችንን በማደናቀፍና ሕዝቡ ወደ ሰልፉ እንዳይወጣ በማድረግ በተግባር ሠልፍ የማይደረግባት አገር ለመፍጠር ሣይታክት ተግቶ ሰርቷል፡፡ ቀስቃሾችና አመራሮችን አስሯል መኪናዎችን አግቷል፡፡ በዚህ ውስጥ ማለፍ የተሣካ ሕዝባዊ ንቅናቄ በመፍጠራችን ከዚህ በመነሳት አንድነት ፓርቲና 33ቱ በጋራ በተጠናከረ መንገድ በመላው አገሪቱ ቀጣይና ተከታታይ ሕዝባዊ ንቅናቄ የማድረግ አስፈላጊነትን ተምረንበታል፡፡
ስለሆነም በአገር ቤትም ሆነ በውጭ አገር የምትገኙ የሠላማዊ ሕዝባዊ ንቅናቄ ደጋፊዎቻችን በሙሉ ለእስከዛሬው በድጋሚ እያመሰገንን ለቀጣዩ የጋራ ሥራችን እንደተለመደው ከጎናችን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
አንድነት ፓርቲና 33ቱ ፓርቲዎች የተሰጠ መግለጫ
መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም
መስከረም 19 ቀን 2006 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment