ለህንድ ፍትህ ወዳዶች ጥሪው ይቀጥላል ተብሏል
August 31, 2013 02:55
የኢትዮጵያን ለም መሬት ከተቀራመቱት ኢንቨስተሮች መካካል አንዱ የሆነው የህንዱ ካሩቱሪ ከኢትዮጵያ ለቅቆ የሚወጣበት ጊዜ መቃረቡን ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ክፍሎች ለጎልጉል አስታወቁ። አበዳሪዎችና ባለ አክሲዮኖች ፊታቸውን እንዳዞሩበትም ታውቋል። ከዚህ በተጨማሪም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ባዶ ዋይታ የሚያሰማው ኢህአዴግ የያዘው አዲስ አቋም ድርጅቱንና ከድርጅቱ ጋር የቀረበ ግንኙነት አላቸው የሚባሉትን ሃሳብ ላይ ጥሏል።
በምናምንቴ ዋጋ የኢትዮጵያ ድንግል መሬት ባለቤት የሆነው ካሩቱሪ ለጊዜው በገንዘብ ሊተመን የማይችል የተፈጥሮ ደን ሲያወድም የከለከለው አልነበረም። ለጊዜው ማልማት ከሚችለው አቅም በላይ መሬት ወስዶ የተፈጥሮ ደን የጨፈጨፈው ካሩቱሪ ተቃውሞ የገጠመው ገና ከጅምሩ ነበር።
በቦታው ሆነው መረጃ ሲያቀብሉ የነበሩ ወገኖችና ለድርጅቱ ቅርብ የሆኑ እንደሚሉት በጋምቤላ መሬት ወስደው ደን በመጨፍጨፍ ከሰል እያከሰሉና ጣውላ በማምረት ገንዘብ የሰበሰቡ “ባለሃብቶች” መሬቱን ሲነጥቁ ላደረሱት ውድመት እንዳልተጠየቁ ይጠቁማሉ። ካሩቱሪን የተለየ የሚያደርገው የያዘው ሰፊ መሬትና ያደረሰው የጉዳት መጠን እንደሆነ የሚጠቁሙት ክፍሎች ካሩቱሪ ካጋጠሙት ፈተናዎች ሁሉ ትልቁ ባካባቢው የመሬቱ ባለቤቶች ያጣው ተቀባይነት እንደሆነ ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ህንድ በመዝለቅ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶና የኦክላንድ ተቋም ዳይሬክተር አኑራድሃ ሚታል ያካሄዱት ዘመቻ ውጤት እንደሆነ የሚናገሩ አሉ።
ከሁሉም በላይ የኦክላንድ ተቋምና አኢጋን በጋራ ያዘጋጁት ጥናት በአበዳሪዎችና ከፍተኛ ድጋፍ በሚያደርጉ የገንዘብ ተቋማት ዘንድ የፈጠረው ተጽዕኖ ቀላል ጊዜ ቢፈጅም ውጤት እንዳስገኘ የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ። አኢጋን ሰነዱን ወደ አማርኛ በመተርጎም ለንባብ ሲያበቃ፣ “በቦታው ላይ ሆናችሁ ለህይወታችሁ ሳትፈሩ ይህንን መረጃ የሰጣችሁ ሁሉ የአገር ጀግኖች ናችሁ፤ አሁን አትታወቁም። አሁን ልንገልጻችሁ አንችልም። ጊዜና ወቅት ጀግንነታችሁን እስኪገልጹት ግን አትረሱም። ልትረሱም አትችሉም። ብዙ ባይነገርላችሁና ባይዘመርላችሁም ታላቅ ስራ ሰርታችኋልና ክብር ይሁንላችሁ” በማለት ኢህአዴግ ላንቃ ስር ሆነው ለታገሉ ወገኖች ክብር እንደሚገባቸው መናገሩ ይታወሳል።
የካሩቱሪ “ኢቨስትመንት”
በ2000ዓም አካባቢ የሕንዱ ካሩቱሪ ግሎባል ድርጅት 300ሺህ ሔክታር መሬት ከጋምቤላ ክልል አካባቢ በሚወስድበት ጊዜ ዕቅዱ የዓለም ታላቁ የምግብ አምራች ድርጅት በመሆን የቀዳሚነቱን ቦታ ለመውሰድ ነበር። ከአምስት ዓመት በኋላ ግን ሕልሙ ወደ ቅዠት እየተቀየረና የድርጅቱም ተስፋ እየተሟጠጠ ስለመሆኑ የሚያስረዱ ወገኖች ለማስረጃነት የሚያውቁትን መረጃ ያጣቅሳሉ።
ይህንን ታላቅ የትርፍ ተስፋ በመሰነቅ ከአበዳሪዎችና ባለአክሲዮኖች በርካታ ገንዘብ በመሰብሰብ በኢቨስትመንት ላይ የተሠማራው ካሩቱሪ በአሁኑ ወቅት ከመንግሥት በኩል “ከጠበቅነው በታች ነው ያከናወንከው” የሚል ግምገማ ሲቀርብበት፣ የመበደር አቅሙን የሚገመግሙ የፋይናንስ ተቋማት ደግሞ “ለኪሣራ አደጋ የተጋለጠ” በማለት ባንዲራ እንደሰቀሉበት፣ ይህም አበዳሪዎቹን ከማስከፋቱም በላይ ለአክሲዮን ዋጋው መውደቅ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉን ይጠቁማሉ።
በአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄና በኦክላንድ ተቋም አማካኝነት በኢንቨስትመንት ስም የመሬት ነጠቃ ስለሚያደርጉ ድርጅቶች የተሠራው ጥናት ካሩቱሪን፣ የሼህ አላሙዲንን ሳውዲ ስታር፣ ወዘተ ድርጅቶች በመሬት ነጠቃ መሠማራታቸውን አጋልጧል፡፡ ሪፖርቱ ያመጣው ዓለምአቀፋዊ ተጽዕኖና የመብት ጥያቄ ካሩቱሪ “አለማዋለሁ” ብሎ ከወሰደው መሬት ውስጥ አምስት በመቶ ብቻ ማልማቱ ከባለአክሲዮኖቹ የማያፈናፍን የአክሲዮን ዋጋ ማሽቆልቆል ጋር ተዳምሮ ካሩቱሪ ከጋምቤላ ክልል ለቅቆ ለመውጣት እያሰበ እንደሆነ ሁኔታዎቹ ጠንካራ ጠቋሚዎች እንደሆኑ ተመልክቷል።
አንደኛው የሙት ዓመት እየተዘከረላቸው ያለውና “የኢትዮጵያ ፈጣሪ” ተብለው እየተወደሱ ያሉት አቶ መለስ፤ “እኛ የሚያሳስበን ያልሸጥነው (በሊዝ ያልሰጠነው) መሬት ነው” በማለት የኢትዮጵያን ለም መሬት ከነዋሪዎች ላይ በግፍ እየነጠቁ፣ እየገደሉ፣ እያስገደሉ እንዲሁም እያፈናቀሉ በኢንቨስትመንት ስም ሲቸበችቡ የቆዩበት ጣጣ እርሳቸው ወደከርስ ከወረዱም በኋላ ዕዳው የተረፈው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የት እንደሚያደርሰን ለመገመት እንደሚያዳግት የሚጠቁሙ ክፍሎች፣ “የአገሪቱን ጥብቅ የተፈጥሮ ደን ያስጨፈጨፉና እሳት እንዲለቀቅበት የፈቀዱ መሪ የአረንጓዴ ዘመቻ አባትና የልማት ጀግና ብሎ መዘመር፣ በራስና ባገር መቀለድ፣ በትውልድ፣ ባገርና በዜጋ ላይ ግፍ መፈጸም ታላቅ ክብር እንደሚያሰጥ ለመጪው ትውልድ የማስተማር ያህል ታላቅ ውርደት ነው” ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።
ካሩቱሪ የእርሻ ስራውን ለማከናወን 50ሚሊዮን ዶላር በሚጠጋ ወጪ የእርሻ መሣሪያዎችን ገዝቷል፣ 120ኪሜ የሚሆን የውሃ ማስተላለፊያ ገንብቷል፣ 120ኪሜ የጎርፍ መከላከያ ግድብ ሰርቷል፣ 50ኪሜ የሚደርስ የመስኖ ቦይ ሰርቷል፡፡ ሆኖም ባለፈው ዓመት በተከሰተው ጎርፍና ያንንም ተከትሎ ያጋጠመው ኪሳራ ድርጅቱ የኢንቨስትመንት መጠኑን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳይቀጥል ገድቦታል፡፡ ይህም እስካሁን ላወጣቸው የካፒታል ወጪዎች ምላሽ እንዳያገኝ አድርጎታል።
ካሩቱሪ “በቃኝ” ወደማለቱ ነው
እንደካሩቱሪ በ25ሺህ ሔክታር መሬት ላይ 100ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ የጥጥ እርሻና የመፍተያ ፋብሪካ እከፍታለሁ ብሎ ቃል የገባ ሌላ የሕንድ ድርጅት አገር ለቅቆ ወጥቷል፡፡ መንግሥት “በውሉ መሠረት መንቀሳቀስ ስላልቻሉ መሬቱን መልሰን ወስደነዋል” ቢልም የኩባንያው ኃላፊዎች የሚናገሩት ሌላ ነው፡፡ በውሉ መሠረት የተሰጣቸውን መሬት ከወሰዱ በኋላ “5ሺህ ሔክታር መሬቱን በውሉ ውስጥ አልተካተተም” በማለት መንግሥት ፖሊስ ልኮ መሬቱን በግድ መልሶ እንደወሰደው ይናገራሉ። በመንግስት ተግባር መደናገጡን የገለጸው ይህ ድርጅት የኢንቨስትመንት ሥራውን ሆን ብሎ በማጓተት መንግሥት የውል ማቋረጫ ማሳሰቢያ እንዲሰጣቸውና ውሉ እንዲቋረጥ ማስደረጋቸውንና በመጨረሻም ድርጅቱ ሥራውን ዘግቶ ከኢትዮጵያ ለቅቆ መውጣቱን ያስረዳሉ።
ይህንን የሚያስታውሱት ምንጮች ካሩቱሪ በአሁኑ ጊዜ የአክሲዮን ሽያጩ እጅግ እያሽቆለቆለ መምጣቱን ይናገራሉ። በተለይ ባለፉት ጥቂት ወራት የታየው ሁኔታ የድርጅቱ ህልውና አደጋ ላይ ጥሎታል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ዓመት 1000 የህንድ ሩፒ በማውጣት የካሩቱሪን አክሲዮን የገዛ ኢንቨስተር ዛሬ ላይ የአንድ ሺው ሩፒ ድርሻው ወደ 318 ሩፒ ማሽቆልቆሉን ለአብነት ይጠቅሳሉ። በእንደዚህ ዓይነት ኪሣራ መቀጠል የማይፈልጉት ባለአክሲዮኖች ድርጅቱ ወደ ውሳኔ እንዲመጣ ማስገደዳቸው እንደማይቀር ጉዳዩንና የአክሲዮኑን አካሄድ በቅርብ የሚከታተሉ ከግምት ባለፈ ይገልጻሉ።
በውጭ ምንዛሪ እጦትና በትስስር በጋምቤላና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሰፋፊ መሬት እዚህ ግባ በማይባል ሳንቲም የቸረቸረው ኢህአዴግ አሳፋሪ ውል እንደፈጸመ ከተለያየ አቅጣጫ ቅሬታ ቢቀርብበትም ከጥፋቱ ለመመለስ ፈቃደኛ አልሆነም። የአገሪቱን ድንግል መሬት መቸብቸብ ብቻ ሳይሆን የሚመረተውን ምርት ሙሉ በሙሉ ወደ አገራቸው እንዲወስዱ የሚፈቅድ ውል የፈጸመው ኢህአዴግ እስከወዲያኛው በዚህ ተግባሩ እንደሚጠየቅበት የበደሉን መጠን የሚገነዘቡ ሁሉ ይስማማሉ።
ሪፖርተር በነሐሴ 12፤2005 (ኦገስት 18፤2013) እትሙ “ካሩቱሪና ሳዑዲ ስታርን ጨምሮ ሰፋፊ የግብርና መሬት ወስደው ያላለሙ ሊነጠቁ ነው” ከዚህ የሚከተለውን መጻፉ ይታወሳል።
የህንዱ ኩባንያ ካሩቱሪ አግሮ ፕሮዳክትስ፣ የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ሳዑዲ ስታርን ጨምሮ ሰፋፊ የግብርና መሬት ወስደው ያላለሙ ኩባንያዎችን መሬት መንግሥት መንጠቅ ሊጀምር ነው፡፡
መንግሥት በኢትዮጵያ ላለፉት 20 ዓመታት ያልነበረውን በሰፋፊ መሬቶች ላይ የሚካሄድ የግብርና ኢንቨስትመንት ሥራ ላይ በማዋል የግል ባለሀብቶች በግብርና ኢንቨስትመንት ላይ እንዲሳተፉ ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ ቢፈቅድም፣ በዚህ ዘርፍ ላይ የጣለውን ከፍተኛ ተስፋ ሰፋፊ መሬቶችን የወሰዱት ኩባንያዎች በተለያዩ ምክንያቶች እንዳደናቀፉት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በሰፋፊ መሬቶች ላይ የግብርና ኢንቨስትመንትን በማካሄድ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ለግብርናው ዘርፍ ያስቀመጠውን ግብ ለመምታት፣ የግብርና ሚኒስቴር 3.6 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በተለይም በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዘጋጅቷል፡፡
የተዘጋጀውን መሬት እስከ አምስት ዓመት ዕቅዱ መጨረሻ በግብርና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ለመሳተፍ ለሚፈልጉ ባለሀብቶች በመስጠት የግብርና ምርትን 39 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ለማድረስ የዕቅዱ ስትራቴጂ አካል ነው፡፡ ይሁን እንጂ የዕቅድ ዘመኑ ከተጀመረበት ከ2002 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ግብርና ሚኒስቴር ለኩባንያዎች በሊዝ ያስተላለፈው መሬት 470 ሺሕ ሔክታር ብቻ እንደሚሆን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የተጠቀሰውን ሔክታር መሬት የወሰዱት ኩባንያዎች መሬቱን በገቡት ውልና የጊዜ ገደብ ማልማት ቢችሉ በግብርና ምርት ዕድገቱ ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችሉ ቢሆንም፣ ኩባንያዎቹ ግን በገቡት ውልና ዕቅድ መሠረት እየሠሩ አለመሆኑን ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የሚኒስቴሩ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ለአብነት ከሚጠቅሷቸው ኩባንያዎች መካከል የህንዱ ኩባንያ ካራቱሪ አንዱ ነው፡፡ ይህ ኩባንያ በ2002 ዓ.ም. 300 ሺሕ ሔክታር መሬት በጋምቤላ ክልል ቢረከብም በዕቅዱ መሠረት ማልማት አልቻለም፡፡
በመሆኑም ሚኒስቴሩ እ.ኤ.አ. በጃንዋሪ 2012 ከኩባንያው ጋር የገባውን ውል በማደስ 200 ሺሕ ሔክታር የሚሆነውን መሬት እንዲመልስ መደረጉን ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ውል መሠረት ካራቱሪ 100 ሺሕ ሔክታር መሬት ብቻ እንዲያለማ የተወሰነ ሲሆን፣ የተጠቀሰውን መሬትም በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማልማት የሚያስገድድ ውል ተፈጽሟል ብለዋል፡፡ ካራቱሪ መሬቱን ሙሉ በሙሉ አልምቶ ከሆነ ተጨማሪ መሬት እንደሚፈቀድለትም የተሻሻለው የሚኒስቴሩና የኩባንያው ውል እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡
‹‹ይሁን እንጂ ካራቱሪ በተሰጠው የሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥም ቢሆን ከ300 ሺሕ ሔክታር ወደ 100 ሺሕ ሔክታር ዝቅ እንዲል የተደረገውን መሬት ማልማት አልቻለም፡፡ በዚህ መሬት ላይ ሙሉ ለሙሉ መልማት የቻለው አሥር በመቶ አይሆንም፤›› ሲሉ ምንጮች ይናገራሉ፡፡
ከካራቱሪ በተጨማሪ የሼክ መሐመድ አል አሙዲ ኩባንያ የሆነው ሳዑዲ ስታር በወሰደው መሬት ላይ ከሌሎች ኩባንያዎች በመጠኑ የተሻለ ሥራ በማከናወን ላይ ቢሆንም፣ የግብርና ሚኒስቴር ከኩባንያው ጋር በገባው ውል መሠረት እየተፈጸመ እንዳልሆነ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ እስካሁን ለኩባንያዎች ተሰጥቶ ከነበረው 470 ሺሕ ሔክታር መሬት ውስጥ 200 ሺሕ ሔክታሩ ከካራቱሪ ሲቀነስ፣ ሌሎች ዘጠኝ ከሚሆኑ ኩባንያዎች ደግሞ ሙሉ ለሙሉ የወሰዱትን መሬት ማለትም 100 ሺሕ ሔክታር የሚጠጋ እንዲነጠቁ ተወስኖ ኩባንያዎቹ ከአገር እንደወጡ የሚኒስቴሩ ምንጮች አብራርተዋል፡፡
አሁንም ቢሆን ያሉት ቀሪ ኩባንያዎች ካራቱሪና ሳዑዲ ስታርን ጨምሮ የወሰዱትን መሬት የማልማት አቅማቸው ከተጠበቀው በታች መሆኑን ሚኒስቴሩ ባለፈው ወር ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ማመልከቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በዚህ ጥናት ላይ በመወሰንም አዲስ የግብርና ኢንቨስትመንት አስተዳደር ዕቅድ መነደፉን፣ በዚህ ዕቅድ መሠረትም አሁን በሥራ ላይ ያሉ ኩባንያዎች እስካሁን ያላለሙት መሬት እንዲነጠቅ መወሰኑን አስረድተዋል፡፡
በአዲሱ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር መሠረት የግብርና ኢንቨስትመንት ኢኮኖሚ ዞን በግብርና ሚኒስቴር በመቋቋም ላይ ሲሆን፣ በዚህ ዞን ውስጥ ኢንቨስት ማድረግ የሚፈልጉ ኩባንያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሊወስዱት የሚችሉት ትልቁ የእርሻ መሬት አምስት ሺሕ ሔክታር ብቻ እንደሚሆን፣ ይህም አቅማቸው ተገምግሞ የሚሰጥ መሆኑን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡
ሚኒስቴሩ ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት መሬት የወሰዱ ኩባንያዎች ያላቸው የገንዘብ አቅም ውስንነት መሬቱን እንዳያለሙ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ ቢሆንም፣ አንዳንድ ኩባንያዎች ግን በሕገወጥ ሥራ ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውንም ጥናቱ ጠቁሟል፡፡ ሕገወጥ ከተባሉት ድርጊቶች መካከል መንግሥት በዚህ የግብርና ኢንቨስትመንት ለሚሳተፉ ኩባንያዎች የሰጠውን የታክስ ነፃ መብት መበዝበዝ መሆኑን ምንጮች ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ አዲሱን አሠራር ወደተግባር መለወጥ ሲጀምር ካራቱሪ በእጁ ከሚገኘው መሬት ውስጥ ሊቆይለት የሚችለው አሥር ሺሕ ሔክታር ብቻ ሊሆን እንደሚችል ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል፡፡
No comments:
Post a Comment