Friday, March 13, 2015

የኢትዮጵያ ወታደሮችን ጨምሮ በአስር የሚቆጠሩ ሰዎች በአሸባብ ጥቃት ተገደ

አሸባብ በጣም መዳካሙን የሶማሊያ መንግሥትና ደጋፊዎቹ መናገር ከጀመሩ ከሁለት ዓመት በላይ ተቆጠረ።ሶማሊያ ግን የአክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ጥቃት ተለይቷት አያዉቅም።ሆቴሎች፤ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፅሕፈት ቤቶች፤ አብያተ-መንግሥታት፤ መስሪያ ቤቶች፤ የጦር ሠፈሮች፤ አዉሮፕላን ማረፊያዎች፤ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ሁሉም ይጠቃሉ፤ ሁሌም ይሸበራሉ።
የሶማሊያዉ አክራሪ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን አሸባብ በደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ትልቅ ከተማ ባይዶዎ የሚገኘዉን የዓለም አቀፍ ድርጅቶች፤የጦርና ሐይልና የአካባቢያዉ መስተዳድር ፅሕፈት ቤትን ደበደበ።የሶማሊያ መንግሥት ባለሥልጣናት እንዳስታወቁት በጥቃቱ አካባቢዉን ይጠብቁ የነበሩ የኢትዮጵያ ወታደሮችን ጨምሮ በአስር የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፤ ወይም ቆስለዋል።ከሟቾቹ ሰወስቱ ጥቃቱን ያደረሱን የአሸባብ ታጣቂዎች እንደነበሩ ተገልጧል።
ሶማሊያ ዉስጥ በጥብቅ ከሚጠበቁ አካባቢዎች አንዱ ነዉ።እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር በ2000 የሶማሊያ መሪዎች ጊዚያዊ መቀመጫ ሥለነበር አካባቢዉ ፕሬዝዳንታዊ ቤተ-መንግሥት በመባል ይታወቃል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፤ የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ መስተዳድር፤ የሶማሊያ መንግሥትና ኢትዮጵያ ጦር ማዘዣ፤ የባይድዎ አዉሮፕላን ማረፊያ እዚያ ነዉ።ከሞቃዲሾ ቀጥሎ ሁለተኛዉ የሶማሊያ የነቭርቭ ማዕከል።
ዛሬ ግን በአሸባብ ታጣቂዎች ተደፈረ።በቦምብ፤ መትረየስ፤ ባዙቃ ተኩስ ተተረማማሰ።ግን ላጭር ጊዜ።በሞቃዲሾ የዶቸ ቬለ ተባባሪ ዘጋቢ መሐመድ ዑመር ሁሴይን የሆነዉን እንዲሕ ይገልፀዋል።
«እንዳልከዉ ነዉ።ጠንካራ ጥበቃ የሚደረግለት አካባቢ ነዉ።ዛሬ ግን በአካባቢዉ አቆጣጠር ከጠዋቱ አራት ሠዓት ግድም በግምት 15 የሚሆኑ በቅጡ የታጠቁ የአሸባብ ሸማቂዎች ድንገት ጥቃት ከፈቱበት።ታጣቂዎቹ አካባቢዉን ከሚጠብቁት የኢትዮያ ወታደሮች ጥንካራ አፀፋ (ጥቃት) ስለገጠማቸዉ ካደረሱት የከፋ አደጋ ማድረስ አልቻሉም።ይሁንና የኢትዮጵያዉያኑን መከላከያ ጥሰዉ ፕሬዝዳንታዊዉ ቤተ-መንግሥት ቅጥር ግቢ መግባት ችለዋል።»
በቅርቡ በተዋቀረዉ የሶማሊያ አስተዳድር መሠረት ከክፍለ-ሐገርነት ወደ አስተዳደርነት ያደገዉ የደቡብ ምዕራብ ሶማሊያ ግዛት ፕሬዝዳንት ሸሪፍ ሐሰን ሼኽ አደን ጥቃቱ በደረሰበት ሰዓት ቤተ-መንግሥቱ ዉስጥ ነበሩ።ቀድሞ የሶማሊያ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የነበሩት አደን ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳረፍ ከሚችሉ የሶማሊያ መንግሥት ፖለቲከኞች አንዱ ናቸዉ።ከዛሬዉ ጥቃት አምልጠዋል።ሌሎች ግን እንደሳቸዉ አልታደሉም።
«በመጨረሻ ባገኘሁት መረጃ መሠረት ሰወስት የመንግሥት ወታደሮች፤ አምስት ሰላማዊ ሰዎችና የአፍሪቃ ሕብረት ጦር አባላት የሆኑ ሁለት የኢትዮጵያ ወታደሮች ተገድለዋል።»የሶማሊያ መንግሥት ባለስልጣናት ጥቃቱን ከከፈቱት ታጣቂዎች ቢያንስ ሰወስቱ መገደላቸዉን አስታዉቀዋል።ይሁንና ባለሥልጣናቱ ሥለሟች ቁስለኞቹ ቁጥር የሚሰጡት መረጃ ይለዋወጣል።
የአፍሪቃ ሕብረት ጦር በተከታታይ ከፍተኛ ጥቃት ያደረሰበት አሸባብ በጣም መዳካሙን የጦሩ አዛዦች፤ የሶማሊያ መንግሥትና ደጋፊዎቹ መናገር ከጀመሩ ከሁለት ዓመት በላይ ተቆጠረ።ሶማሊያ ግን የአክራሪዉ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ጥቃት ተለይቷት አያዉቅም።
ሆቴሎች፤ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ፅሕፈት ቤቶች፤ አብያተ-መንግሥታት፤ መስሪያ ቤቶች፤ የጦር ሠፈሮች፤ አዉሮፕላን ማረፊያዎች፤ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ሁሉም ይጠቃሉ፤ ሁሌም ይሸበራሉ።አሸባብ ትናንት ወንላ ወይን የተባለችዉን ከተማ አጥቅቶ በትንሽ ግምት ሰባት ሰዎችት ገድሏል።ትናንትናዉኑ ሞቃዲሾ ዉስጥ አንድ ታዋቂ ሆቴል አጠገብ በፈነዳ ቦምብ ቢያንስ አንድ ሰዉ ተገድሏል።ጋዜጠኛ መሐመድ ዑመር ሁሴይን የአሸባብን ስልት «መትቶ-መሮጥ» ይለዋል።
«አሸባብ ከሶማሊያ ሙሉ በሙ ጠፍቷል ማለት አንችልም።አሁንም አሉ።ጥቃት ያደርሳሉም።እንደዱሯቸዉ ግን አይደሉም።አሁን የሚያደርጉት ምንድነዉ መትቶ-መሮጥ ነዉ።ለምሳሌ ዛሬ ባይደዎን አጠቁ፤ ነገ ባይዶዎን አይደግሙም ሌላ ቦታ ነዉ የሚያጠቁት።»
በርግጥም ዛሬ ዛሬ ባይዶዎ ናት።ነግስ?

No comments:

Post a Comment