Tuesday, April 9, 2013

መሬት ነጠቃ ለአሜሪካ ም/ቤት ሊቀርብ ነው

capitol_003

በአሜሪካ የተወካዮች ምክርቤት በአፍሪካ፣ በዓለምአቀፍ ጤና፣ በዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብቶችና ዓለምአቀፋዊ ድርጅቶች ንዑስኮሚቴ ሊቀመንበር የሆኑት ክሪስ ስሚዝ ከፍተኛ አማካሪና የአፍሪካ ኤክስፐርት የሆኑት ግሬጎሪ ሲምፐኪንስ ስብሰባውን እንደሚመሩትም ከወጣው መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡
በአፍሪካ የሚካሄደውን የመሬት ነጠቃ አስመልክቶ በተጠራው ስብሰባ ላይ መግለጫ ከሚሰጡት አፍሪካውያን መካከል ጋናዊው ምሁር ዶ/ር ጆርጅ አዪቴ የሚገኙበት ሲሆን ከኢትዮጵያ ብቸኛው ተጠቃሽ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ናቸው፡፡ ከኦክላንድ ተቋም ጋር በመሆን አቶ ኦባንግ የሚመሩት የጋራ ንቅናቄ በቅርቡ በአማርኛ ተተርጉሞ ይፋ የሚሆነውን ጥናታዊ ዘገባ ማዘጋጀቱ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ በመሬት ነጠቃ ላይ የተዘጋጀውን ዘገባ የጠቀሰው የስብሰባው መጥሪያ በጉዳዩ ላይ አኢጋን ያከናወነውን የምርመራ ሪፖርት ጠቅሷል፡፡
በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የሥራ ጉዳዮች ላይ በመጠመድ በዋሺንግተን ዲሲ ከተማ የሚገኙትን አቶ ኦባንግን ጎልጉል በስልክ ባነጋገረበት ወቅት እንደተናገሩት ድርጅታቸው መነሻውንና መድረሻውን እንዲሁም የሚያከናውነውን ተግባራት በዕቅድ የሚፈጽም መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ የጋራ ንቅናቄው ለዚህ ዕውቅናና ስብሰባ መጠራቱ በራሱ ታላቅ ድል መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የሰላማዊ ትግል ከወረቀት የማያልፍና የአቤቱታ ማስፈረም (የፔቲሽን) ትግል ብቻ እንዳልሆነ በቅርቡ ሕንድ በመሄድ በዚሁ የመሬት ነጠቃ ጉዳይ ላይ ያደረጉት ስብሰባና ውይይት በኢንቨስትመንት ስም በኢትዮጵያ መሬት እየዘረፉ ላሉት ኩባንያዎች ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረባቸው እንደማስረጃ ጠቅሰዋል፡፡
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ካለበት ድርጅታዊና አገራዊ ግዴታ አኳያ የአሜሪካ ምክርቤት ሕግ አውጪ አካላትን በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ እያሳወቀና እየወተወተ መሆኑን የተናገሩት አቶ ኦባንግ፤ በተለይ በቅርቡ የሚካሄደውን ምርጫ፣ የፖለቲካ እስረኞችን ሁኔታ፣ ከየቦታው እየተፈናቀሉ ያሉትን ዜጎች፣ አፋኝ የሆኑትን የመያድና የጸረ-ሽብርተኝነት ሕጎችን እንዲሁም የመንደር ምስረታንና አስገድዶ ማስፈርን በተመለከተ በርካታ ጉዳዮች በተጠናከረ ሁኔታ እየሠራበት እንደሆነ በተለይ ለጎልጉል ገልጸዋል፡፡ በመጪው ሰኞ በሚደረገው ስብሰባ የሚገኘውን ውጤት ካሁኑ በግልጽ ለመናገር ባይቻልም ስብሰባው ከላይ ከተጠቀሱት ጉዳዮች አንዱ እንደመሆኑ ወደፊት በምክርቤት ለሚደረጉ ውሳኔዎች እንደ ግብዓት እንደሚያገለግል አስታውቀዋል፡፡
በአፍሪካ እየተካሄደ ስላለው የመሬት ነጠቃ 11የአፍሪካ አገራትን የሚወክሉ 11 ድርጅቶች ኅብረት በመፍጠር ተጽዕኖ ከማድረግ እስከ ፖሊሲ ማስቀየር ሥራ እየሠሩ መሆናቸውና ከእነዚህም ድርጅቶች መካከል ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ አንዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡
የሰኞው ስብሰባ መርሃግብር ይህንን ይመስላል፡፡

http://www.goolgule.com/congress-briefings-on-land-grab/

No comments:

Post a Comment