ኢህአዴግን በጓሮ ድርድር የጠየቀበት ሰነድ ተተረጎመ!
“የመሬት ነጠቃ” ዜጎችንና የተፈጥሮ ሃብት እየበላ ነው
በልማትና ኢንቨስትመንት ስም ኢህአዴግ ለውጪና ለራሱ ሰዎች እየቸበቸበ ያለውን መሬት አስመልክቶ የኦክላንድ ተቋምና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በጋራ ያዘጋጁት ጥናታዊ ዘገባ አማርኛ ትርጉም በሳምንቱ መጨረሻ ይፋ ይደረጋል ተባለ። የመሬት ነጠቃ ዜጎችን እያፈናቀለና ውድ የተፈጥሮ ሃብትን እየበላ ነው።
እመራቸዋለሁ ለሚለው ህዝብና አገር ደንታ የሌለው ኢህአዴግ፣ በመረጃ ለሚያጭበረብራቸው ዜጎች የተሟላና የተመጣጠነ ዘገባ እንደሚያቀርብ የተነገረለት ይህ ሰነድ በአማርኛ ተተርጉሞ ይፋ እንደሚሆን የገለጸው የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የሚዲያና የህዝብ ግንኙነት ዴስክ ነው።
የጋራ ንቅናቄው የህዝብ ግንኙነት ዴስክ በተለይ ለጎልጉል በሰጠው መረጃ በጥናቱ ሰለባዎች፣ የኢህአዴግ ባለስልጣናት፣ ኢንቨስተሮች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎች፣ የቅርብ ምስክሮች፣ የተለያዩ ከዓለምአቀፍ ተቋማት የተገኙ መረጃዎች፣ መንግስት ራሱ ይፋ ያደረጋቸው መረጃዎችና ለጥናቱ አስፈላጊ የተባሉ አኻዞች ተካተውበታል።
በዚሁ መሰረት ኢህአዴግ በልማትና በኢንቨስትመንት ስም “ጥቅም ላይ ያልዋለ መሬት” በማለት ለንግድ ማቅረቡና፣ ይህም በመደረጉ አገሪቱ ውስጥ ልማት እንደሚስፋፋ የሚሰብከው ስብከት ያለ አንዳች ማስተባበያ እርቃኑን የሚያስቀረው ሪፖርት በዋናነት የተዘጋጀው መረጃ ለጠማው ህዝብ እንደሆነ ዴስኩ አስታውቋል።
አገራቸውን፣ መሬታቸውንና መንግስትን አምነው የሚኖሩ ዜጎችን በገንዘብ በመለወጥ ያፈናቀለውና እያፈናቀለ ያለው ኢህአዴግ፣ ምትክ የሌላቸውን እድሜ ጠገብ የተፈጥሮ ደኖች ጨፍጭፏል፤ አቃጥሏል፤ አውድሟል። ሰፊ መሬት ምድረ በዳ አድርጓል። ያለ አንዳች ምክርና ውይይት ዜጎችን አፈናቅሎ ለመከራ ዳርጓል። ንብረታቸውንና ማሳቸውን እንደ ባዕድ በዶዘር ጠርጎባቸዋል። ለመቃወም በሞከሩ ወገኖች ላይ የባዕድ ወራሪ ሃይል ይፈጽመዋል ተብሎ የማይገመት ወንጀልና መከራ አድርሷል። የጋራ ንቅናቄው የሚዲያ ዴስክ እንዳለው ኢህአዴግ ይህንን ሁሉ ሲፈጽም ጎን ለጎን ዜጎችን በመረጃ እያጭበረበረና እያስራበ በመሆኑ አሁን ይፋ የሚደረገው ሪፖርት ታላቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
ለጋሽ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፍ ማህበረሰብና አበዳሪ ድርጅቶች አቋማቸውን እንዲመረምሩ ለማስቻል ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑንን ያወሳው የጋራ ንቅናቄው “የመሬት ወረራው መቆሚያ የሌለው፣ እንዲያውም በቀጣይነት የሚከናወን በመሆኑ ይፋ የሚደረገው ይህ መረጃ አገር ቤት ገጠር ሳይቀር ዘልቆ እንዲገባ ለማድረግ ዝግጅቱ ተጠናቋል” በማለት አስረድቷል። ይሁን እንጂ መረጃው እንዴት እንደሚሰራጭ ዝርዝር ማብራሪያ አላቀረበም።
ወደፊት ጥናትና ምርምር የሚያካሂዱ ተቋማትም ሆነ ግለሰቦች ሊጠቀሙበት እንዲችሉ ተደርጎ በዝርዝር የቀረበው ይህ ሪፖርት፣ በእንግሊዝኛው ጥቅል ጥናት ውስጥ በሰባት የአፍሪካ አገራት ተከፋፍሎ የተዘጋጀ ሲሆን ወደ አማርኛ በተቀየረው ትርጉም ውስጥ ሙሉ ትኩረት የተደረገው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እንደሆነ ተመልክቷል።
“በኢንቨስትመንት ስም የሚፈጸም የመሬት ነጠቃ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ በሦስት ዓቢይ ምዕራፎችና በበርካታ ንዑሳን ክፍሎች ተከፋፍሎ የተዘጋጀው ከ110 ገጽ በላይ የሆነው የአማርኛው ጥናታዊ ሪፖርት “የሰከነው” ትግል ውጤት እንደሆነ የመረጃ ዴስኩ አስታውቋል። በቅርቡ የጋራ ንቅናቄው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ ህንድ በመሄድ ያነሳሱት የትግል አብሮነት ስሜት ያነሳሳ ነበር፡፡ ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ ሰኞ ዕለት በአሜሪካው ምክርቤት ለውይይት በመሬት ነጠቃ ጉዳይ ላይ የቀረበውና ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠውን ይህንኑ የመሬት ነጠቃ ጉዳይ በምክርቤት ተገኝተው ገለጻ ከሰጡት መካከል አቶ ኦባንግ አንዱና ዋንኛው መሆናቸውን የሚዲያ ክፍሉ ጨምሮ አስታውቋል፡፡
ይህም ለመሆን የቻለውና ጉዳዩ በከፍተኛ ደረጃ ተደማጭነት እያገኘ የመምጣቱ ሁኔታ ከፍተኛ ድል እየሆነ ከመምጣቱ የተነሳ ኢህአዴግ የሚተማመንባቸውንና ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ የሆኑ አገራትንና ተቋማት እጅ የማስጠምዘዝ ሁኔታ ሊያስከትልበት እንደሚችል በመገንዘብ ካድሬዎቹን በየቦታው በማሰማራት ከፍተኛ የውስወሳ ዘመቻ እያካሄደ እንደሚገኝ ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ በዚህ ረገድ የጋራ ንቅናቄው እጅግ ከፍተኛ ሥራ ላይ የተጠመደ መሆኑን ጨምሮ ተገልጾዋል፡፡
የጋራ ንቅናቄው አክሎ በሰጠው ማሳሰቢያ አደራም አስተላልፏል። በሳምንቱ መጨረሻ ይፋ የሚደረገው ይህ ጥናታዊ ሪፖርት ምንም እንኳ የጋራ ንቅናቄው ንብረትና የኮፒ ራይት ያለው ቢሆንም “ሪፖርቱን ለማራባትና ለማሰራጨት የሚፈልጉ ሁሉ ለሪፖርቱ ባለቤትና አዘጋጆች ጨዋነት የተሞላው እውቅና ሊሰጡ ይገባል” ሲል ጥሪውን አቅርቧል። በማያያዝም በሚቻላቸው መንገድ ሁሉ ሪፖርቱን ለማራባት ለሚተባበሩ ወገኖች ከወዲሁ ምስጋናውን አቅርቧል። ሪፖርቱ እንዲደርሳቸው ለሚፈልጉ ሁሉ በኢሜል ለመላክ ፈቃደኛ በመሆኑ በሚከተለው አድራሻ media@solidaritymovement.org ጥያቄ ቢያቀርቡ እንደሚተባበር አመልክቷል። የመሬት ነጠቃን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ የሚያካሂደውን እቅድን መሰረት ያደረገ ትግል አጠንክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጧል።
http://www.goolgule.com/land-grab-report-translated/
No comments:
Post a Comment