Wednesday, April 24, 2013

የኦነግ አባል በመሆን የሽብር ተግባር ለመፈጸም ተንቀሳቅሰዋል የተባሉ ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ


• ተጠርጥረው ከተከሰሱት 20 ግለሰቦች ሦስቱ ነፃ ተደረጉ
የአገሪቱን ሕገ መንግሥት በመፃረር የኦሮሚያ ክልል እንዲከፋፈልና እንዲገነጠል፣ በሕገወጥ መንገድ በሚንቀሳቀሰው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በሚባለው ቡድን አባል በመሆን ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል በሚል ተጠርጥረው፣ ክስ ከተመሠረተባቸው 20 ግለሰቦች መካከል 17ቱ ሚያዝያ 15 ቀን 2005 ዓ.ም. በፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡
የፌደራል ከፍተኛ ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸው ጥፋተኛ የተባሉትን ተከሳሾች ክስ የሚመረምረው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አራተኛ የወንጀል ችሎት ነው፡፡ ጥፋተኛ የተባሉትና ዓቃቤ ሕግ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ያረጋገጠባቸውን የወንጀል ድርጊት ባቀረቧቸው የመከላከያ ምስክሮቻቸውና ሰነዶች ማስተባበል ያልቻሉት ጌትነት ገመቹ (ቅፅል ስም ከድር ኢዘዲን)፣ ምትኩ ጌታቸው፣ ኢብሳ አለሙ፣ ጌቱ አሰፋ (ቅፅል ስም ከፍያለው አደሪ)፣ ተስፋ ሞተራ፣ መገርሳ ኩማ፣ ደምሴ ዳበሳ፣ ዋጋሪ ዲሪቢሳ፣ ደሳለኝ ደበል፣ ጌታቸው ብሩ፣ ጫላ አብዲሳ፣ ሐሞዛ አብዱ፣ ኮ/ር ረጋሳ ፈቀደ፣ ደርባቸው አመንቴና ለቺሳ ኢዶሳ ናቸው፡፡
ጥፋተኛ ከተባሉት 17 ተከሳሾች መካከል ሦስቱ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍላተ ከተሞች የሚኖሩ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ 14ቱ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ዞኖች የሚኖሩ ናቸው፡፡ የተጠረጠሩበትን የሽብር ወንጀል በመከላከል ነፃ የሆኑት ደግሞ ተካልኝ አበራ፣ ሙህዲን አባቡልጉና ካሊድ መሐመድ የሚባሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡
አንደኛ ተከሳሽ ስሙን በመቀየር ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ ወደ ኬንያ ስሎሎ ወታደራዊ ማሠልጠኛ በመግባት፣ የኦነግ ካድሬ አመራርነት ሥልጠና መውሰዱን ክሱ ይገልጻል፡፡
በመመልመል፣ በማሠልጠን፣ መዋጮ በመሰብሰብ፣ በሴል በማደራጀት፣ አመራር በመስጠትና በ2003 ዓ.ም. የኦነግን ተልዕኮ የያዘ 56 ገጽ ያለው የቅስቀሳ ጽሑፍ በማሰራጨት፣ ‹‹ከኦነግ ዓላማ ወደኋላ ያለ ሰው ሞት ይጠብቀዋል›› ብሎ በማስፈራራትና ሌሎች የሽብር ድርጊቶችን በመፈጸም የኦነግን ተልዕኮ ተግባራዊ ለማድረግ ሲሠራ እንደነበር ክሱ ይዘረዝራል፡፡
ሌሎቹም ጥፋተኛ የተባሉት ተከሳሾች የኦነግ ዓላማ ፍፃሜ እንዲያገኝ በመንቀሳቀስ፣ የቅስቀሳ ጽሑፎችን በማሰራጨት፣ በተለያዩ የቀበሌ ገበሬ ማኅበር አካባቢዎች የሚኖሩ ሰላማዊ ዜጐችን በመመልመልና ለሽብር እንዲነሱ በመገፋፋት፣ የአገሪቱን የፖለቲካና የግዛት አንድነት በመንካት ወንጀል ውስጥ እንዲሳተፉ ሲያደርጉ እንደነበር የዓቃቤ ሕግ ክስ በዝርዝር ያብራራል፡፡
ዓቃቤ ሕግ 32 የሰዎች ምስክሮች፣ ዘጠኝ የሰነድና ሁለት የኤግዝቢት ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ፣ ያስመሰከረና ያስረዳ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱ ክሱንና ማስረጃውን ከሕጉ ጋር በማገናዘብ ሁሉም ተጠርጣሪዎች እንዲከላከሉ ብይን መስጠቱን ትናንትና ፍርድ ሲሰጥ አስታውሷል፡፡
ተከሳሾቹ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ የዓቃቤ ሕግን ማስረጃ ለማስተባበል ቢሞክሩም፣ ከሦስቱ በስተቀር 17ቱ ማስተባበል አልቻሉም ብሎ ጥፋተኛ ብሏቸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግን የቅጣት ማክበጃና የተከሳሾቹን የቅጣት ማቅለያ ሐሳብ ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment