Sunday, November 2, 2014

የሕዝብ ልሳን በመሆን መስዋዕትነት የሚከፍሉትን መታደግ የዜግነት ግዴታችን ነው

Global-Alliance-for-Ethiopians-300x152
ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት
ሳውዲ አረቢያ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ በጅምላ የተፈፀመው ኢ-ሰብዓዊ ግፍ አስቆጥቶት ለወገን አለኝታነቱን ለማሳየት በመላው ዓለም የተቀጣጠለው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የወለደው የአገር ወዳዶችና የወገን ተቆርቋሪዎች ትብብር ዛሬም በአገራችን እየተባባሰ የመጣው የዜጎች መብት ጥሰት ሰለባ የሆኑትን ለመታደግ ጥረቱን ቀጥሏል፡፡
‘ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብት’ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት የታፈነው ሕዝብ ልሳን በመሆናቸው ለስደት ተዳርገው በጎረቤት አገር በችግር ላይ ለሚገኙ ጋዜጠኞች ማድረግ ስለሚቻለው ዕርዳታ ዕቅድ በማውጣት ላይ እያል ከመካከላቸው አንዱ አቶ ሚሊዮን ሹሩቤ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ የቀብሩ ሥነ ሥርዓት ቤተሰብና ዘመድ በሚገኝበት በክብር እንዲከናወንና ለአገሩ መሬት እንዲበቃ ለማድረግ አብረውት የተሰደዱት ጋዜጠኞች ባቀረቡት ጥያቄ መነሻነት አስክሬኑን ለማጓጓዣ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከትብብሩ ሂሳብ ወጭ ሆኖ እንዲላክና በአስቸኳይ የእርዳታ ማሰባሰብ ጥረት ተድርጎ እንዲተካ ተወስኖ በሥራ ላይ ማዋል ከተጀመረ በኋላ የሟቹ እህት ወደ ስፍራው በመምጣቷና ወጪውም ከሌላ ምንጭ የሚሸፈን ስለሆነ ቤተሰቦቹ ዕርዳታው የማያስፈልጋቸው መሆኑን በማስታወቃቸው ትብብሩ ቀደም ሲል ባወጣው ዕቅድ መሠረት የተቀሩትን ጋዜጠኞች በመታደጉ ሒደት ላይ ለማተኮር ወስኗል፡፡
ለሟች ዘላለማዊ እረፍትን ለቤተሰቦቹም መፅናናትን እንመኛለን፡፡
የሕዝብ ልሳን በመሆናቸው ብቻ በፈጠራ ወንጀል እየተከሰሱ ለእስራትና ለስደት የተዳረጉ ጋዜጠኞች የሚከፍሉት መስዋዕትነት ታላቅ ባለውለታ ስለሚያደርጋቸው ትብብሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰሞኑን ከአሰባሰበው ገንዘብ ለ25ቱ ጋዜጠኞች የዕለት ኑሮ መጠነኛ ድጎማና የተሻለ የኑሮ ዋስትና ወደሚያገኙበት የሚሸጋገሩበትን ሒደት ለማፋጠን እንዲውል፤ በተጨማሪም በአገር ቤት ለእስርና ከሕልውና ለመፈናቀል የተዳረጉትን ወገኖች ለመታደግ የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በሚያግዝ መልኩ እየተጠና በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
ይህም ትብብሩ ለተመሠረተበት የኢትዮጵያውያንን የመሰብሰብ፣ ሃሳብን በነፃ የመግልጽ፣ በማንኛውም ሥፍራ ተንቀሳቅሶ የመኖርና የመሥራት፣ የግል ሃብት ባለቤት የመሆን፣ በፍርድ ቤት ያለአድልኦና የፖለቲካ ጫና ትክክለኛ ፍትህ የማግኘት፣ የማምለክና በአገራቸው ጉዳይ በእኩልነት የመሳተፍ፣ መሠረታዊና ሰብዓዊ መብቶቻቸውን የማስከበር ዋንኛ ዓላማ አካል በመሆኑ ለምናቀርባቸው ሕዝባዊ ጥሪዎች በጎ ምላሽ በመስጠት የሚተባበሩትን ሁሉ እያመሰገንን ወደፊትም ቅድሚያና ትኩረት በምንሰጠው የኢትዮጵያውያን መብት ተሟጋችነት ቀጣይ እንቅስቃሴ ንቁ ተሳትፏችሁና ትብብራችሁ እንዳይለየን እናሳስባለን።
በአገር ወዳዶች ዓለም አቀፍ ትብብር የኢትዮጵያውያን ሁለንተናዊ መብት ይከበራል።
ዋሽንግተን ዲሲ ጥቅምት 21 ቀን 2007 ዓ.ም.
ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት

No comments:

Post a Comment