Thursday, November 13, 2014

መንግሥት የእነ አቶ ታምራት ላይኔን 18 ሚሊዮን ብር ወረሰ

- 206 ሺሕ ብርና ስምንት ተሽከርካሪዎችን መረከቡን ገልጿል
አቶ ታምራት ላይኔ 12የሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸውና 18 ዓመታት በእስር እንዲቀጡ ተወስኖባቸው የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔና ወ/ሮ ሻዲያ ናዲም ላይ መንግሥት በፍትሐ ብሔር መሥርቶ በነበረው ክስ በመርታቱ 18 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
እነ አቶ ታምራት በሕገወጥ መንገድ ከአገር በማውጣት 1000 ቶን ቡና ሸጠዋል በሚል፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ መሥርቶት የነበረውን የፍትሐ ብሔር ክስ በመርታቱ፣ ፍርድ ቤቱ ግንቦት 5 ቀን 2005 ዓ.ም. የቡናውን ዋጋና ወለዱን በተናጠል እንዲከፍሉ ውሳኔ ማስተላለፉን ፍትሕ ሚኒስቴር አስታውሷል፡፡
ጉዳዩን ሲከታተል የከረመው በፍትሕ ሚኒስቴር የፍትሐ ብሔር ዳይሬክቶሬት፣ ጥቅምት ወር 2007 ዓ.ም. 18 ሚሊዮን ብር ገቢ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ፍርደኞቹ በ1990 ዓ.ም. 26 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው ቢሆንም፣ እስካሁን ሳይከፈል በመክረሙ ዘጠኝ በመቶ ወለድ ሲታሰብ 70 ሚሊዮን ብር መድረሱንም ፍትሕ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
በአቶ ታምራት ላይኔ ልጅ ብሌን ጌታቸው ስም በባንክ ተቀምጦ የነበረን 206,000 ብርና ስምንት ተሽከርካሪዎች ለመንግሥት ገቢ መደረጋቸውንም ሚኒስቴሩ አክሏል፡፡
የፍትሐ ብሔር ፍርድ አፈጻጸሙ የዘገየው በጉዳዩ ውስብስብነት የተነሳ መሆኑን የጠቆመው ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ቀሪው ዕዳ በቀጣይ ገቢ የሚሆንበትን ሁኔታ በማመቻቸት እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡
ሪፖርተር

No comments:

Post a Comment