DECEMBER 17, 2014
በቅርቡ የፌደራልና የክልል የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊዎች በባህርዳር በተሰባሰቡበት ወቅት የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም ፣ ይህን የተናገሩት የሃይማኖት ተቋም የፖለቲካ ፍላጎት ማራመጃ መሆኑን ለማስረዳት ነው። ዶ/ር ሽፈራው ከአፋር የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ «መንግስት ለምን በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ ይገባል? ለምንስ በአገራችን የሌለ ችግር ያመጣብናል?» በሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
ዶ/ር ሽፈራው ይህንን ለማስረዳት ይጠቅማል ያሏቸውን ምሳሌዎች አቅርበዋል። በጥቅምቱ የሲኖዶስ ጉባኤ የኢሳት ሬዲዮና ቴሌቪዥን የሲኖዶሱን ውሎ በየእለቱ ሲዘግብ የነበረው በማህበረ ቅዱሳን ውስጥ በሚገኙ አባላት አማካኝነት ነው ያሉት ሚኒስትሩ ፣ ግንቦት7 እና ኢሳት ሃይማኖትን ለፖለቲካ እምነት ማራመጃ ለመጠቀም እንደሚፈልጉ ዋናው ማሳያ ነው ሲሉ ደምድመዋል ፕሮቴስታንት ሃይማኖት ለኦነግ አላማ ማስፈጸሚያ እያገለገለ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሩ፣ «ኦነግ ከፕሮቴስታንት አልፎ ዋቄ ፈታንም እየተጠቀመ ነው» ብለዋል አክራሪነት ስልቱን ቀየረ እንጅ አልተሸነፈም ያሉት ዶ/ር ሽፈራው፣ በሚቀጥሉት ወራት በሃይማኖት ተቋማት ላይ፣ በትምህርት ቤቶች፣በወጣትና ሴቶች ማህበራት ሰፊ ዘመቻ እንዲጀመር መክረዋል። በተለይ አዲስ አበባ ስራዎች ቢሰሩም ተመልሶ ማጥ የሚገቡበት በመሆኑ፣ የአዲስ አበባ መዋቅራችን አክራሪነትን አሸነፍኩ ብሎ ሊዝናና እንደማይገባው አሳስበዋል።
ማህበራዊ የመገናኛ ብዙሃን በተለይም ፌስቡክና ትዊተር ትልቅ ችግር እየፈጠሩ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፣ እነዚህን የመገናኛ ብዙሃን ለመጠቀም እቅድና ስትራቴጂ ተነድፎ በሙሉ ጊዜና ሃይል የሚሰራ ሰው መድቦ መንቀሳቀስ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይህን ተግባራዊ ማድረግ የትግሉ ዋናው አካል መሆን ይገባዋል ብለዋል መጪውን ምርጫ በተመለከተ በኋላ ላይ ችግር ሳይፈጠር ከአሁኑ እርምጃዎችን በመውሰድ መንቀሳቀስ እንደሚገባም አክለዋል። በአገሪቱ ያሉ የጸጥታ ሃይሎች በምርጫው ላይ መውሰድ ስለሚገባቸው እርምጃም ውይይት አድርገዋል። የውይይቱ ውጤት እንደደረሰን ለህዝብ የምናቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ማህበረ ቅዱሳን ከቀኖና ጋር በተያያዘ ለመክሰስ የተዘጋጁ የደህንነት መስሪያ ቤት ያደራጃቸው ሰዎች ምክክር እያደረጉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል። ሰዎቹ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ላይ ስልጠና እየወሰዱ ሲሆን፣ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ በማህበረ ቅዱሳን ላይ በሃሰት በመመስከር ማህበረ ቅዱሳን የእኛ ነው በሚል ነባሩን ድርጅት ለማሳገድ እና ለገዢው ፓርቲ ተለጣፊ የሆነ ማህበረ ቅዱሳን ለማቋቋም እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ምንጮቻችን ገልጸዋል። በማህበረ ቅዱሳን ስም ማህተም ከማስቀረጽ ጀምሮ የተለያዩ ህገደንቦችን እያረቀቁ መሆኑን ምንጮች አክለው ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment