Friday, October 24, 2014

በአዲስ አበባ ውስጥ የሚታየውን የሃይል እጥረት ለመቅርፍ ረጅም ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ባለሙያዎች ገለጹ

ስማቸው እንደይጠቀስ የፈለጉ በኢትዮጵያ መብራት ሃይል ስር የሚሰሩ ሰራተኞች ለኢሳት እንደገለጹት በአዲስ አበባ የሚታየው የመብራት ሃይል መቆራረጥና መጥፋት ነዋሪውን ለስቃይ እየዳረገው ነው። እናቶች የአቦኩትን ሊጥ ለመጋገር ሲዘጋጁ መብራት ይጠፋና ሊጡ የሚደፋበት ጊዜ መኖሩን የሚናገሩት ሰራተኞች፣ ነዋሪዎች ምሬታቸውን ለመስሪያ ቤቱ በማቅርብ መልስ ሲያጡ የመብራት ሃይል ሰራተኞች ለጥገና ሲንቀሳቀሱ መኪኖቻቸውና ሰራተኞች  በተበሳጩ ሰዎች እንደሚመቱ ገልጸዋል።
መንግስት የከተማውን የሃይል ማሰራጪያ መስመር እንዲያስፋፋ ከአምስት አመት በፊት የቀረበለትን እቅድ ውድቅ በማድረጉ አሁን ለሚታየው ችግር መንስኤ መሆኑን የገለጹት ሰራተኞች፣ በቅርቡ ዶ/ር ደብረጺዮን የማስፋፋፊያ ስራው ለቻይና ኩባንያ መሰጠቱንና እስከ ሰኔ ወር ድረስ እንደሚጠናቀቅ ለህዝብ መናገራቸውን አስታውሰዋል። ይሁን እንጅ ይላሉ ሰራተኞች፣ እስካሁን ድረስ ምንም አይነት ስራ ባለመጀመሩ የተባለው የማስፋፊያ ስራ እንኳንስ በ10 ወር በ5 አመታትም ላይጠናቀቅ ይችላል።
አሁን ያለው መስመር ከ40 አመት በፊት የተዘረጋ መሆኑን  የሚናገሩት ሰራተኞች፣ በተለይ አዲስ ለሚገነባው የባቡር መስመር ማንቀሳቀሻ ሃይል ከየት እንደሚገኝ ግራ እንደገባቸው ተናግረዋል። ዶ/ር ደብረጺዮን ለባቡሩ የሃይል አቅርቦት የሚሆን ሚኒ-ሰብስቴሽን በአጭር ጊዜ እንሰራለን ብለው ህንዶች ቃል እንደገቡላቸው ለሰራተኞች ቢናገሩም፣ አብዛኞቹ ሰራተኞች በስራው ስኬት ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ገልጸዋል።
መንግስት በአዲስ አበባ ያለውን የሃይል አቅርቦት ለማሙዋላት በመቸገሩ ከፍተኛ ሃይል ለሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ሃይል በመፈረቃ ለማከፋፈል እንደሚገደድ አስታውቋል።
በተመሳሳይ ዜና ደግሞ ቆጣሪ ለማግኘት ተመዝግበው የሚጠባበቁ ዜጎች ቁጥር አሁንም ከፍተኛ መሆኑን ሰራተኞች ገልጸዋል። ከ3 አመት በፊት የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ማስተር ሜትር የሚባል ቆጣሪ ለማምረት ከኮርፖሬሽኑ 15 ሚሊዮን ብር ቢቀበልም፣ ቆጣሪዎቹን በተባለው ጊዜ ለማድረስ ሳይችል በመቅረቱ በርካታ ዜጎች ገንዘብ ከፍለው አገልግሎቱን ሳያገኙ ቀርተዋል። መከላከያ ኢንጂነሪንግ በተመሳሳይ መንገድ ትራንስፎርመሮችንና ሌሎች እቃዎችን ለመስራት ከኮርፖሬሽኑ ገንዘብ ቢቀበልም፣ እቃዎችን በተባለው ጊዜና ጥራት ለማምረት ባለመቻሉ፣ ተጨማሪ ችግር እየተፈጠረ ነው።
በተነሱት ቅሬታዎች ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን አስተያየት ለማካተት የተደረገው ሙከራ አልተሳካም።

No comments:

Post a Comment