የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኦሮሞ ተወላጆች ላይ ተባባሰ መባሉ
የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሞ ተወላጆች ላይ የእስራት፣ የስቃይ፣ የግድያ እና የግፍ ተግባር ይፈፅማል ሲል ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምኒስቲ ኢንተርናሽናል ይፋ ባደረገዉ ሪፖርት ገለፀ። ድርጅቱ ይፋ ባደረገዉ ሪፖርት በሽዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች የእስር የስቃይና የግድያ ሰለባ ሆነዋል።
እንደ ሪፖርቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ይህን ያደረገዉ የሚደርስበትን ተቃዉሞ ለማፈን ሲል መሆኑን ዶይቸ ቬለ ያነጋገራቸው የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል አጥኚ ክሌር ቤስተንን አስረድተዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት ዘገባውን ሃሰት ነዉ ሲል አጣጥሎአል።
«ኦሮሞ በመሆኔ» የሚል ርዕስ የተሰጠዉ የዓለማቀፉ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ድርጅት አምኒስቲ ኢንተርናሽናል ሪፕርት ከ 200 በላይ ምስክርነትን በማየት ያቀረበዉ ዘገባ መሆኑን ያትታል። ከጎርጎረሳዊዉ 2011 እስከ 2014 ዓ,ም ድረስ በትንሹ 5000 ኦሮሞዎች ለእስር መዳረጋቸዉን እንዲሁም የመንግስት ጥቃት የኦሮሞ ባህላዊ ማንነታቸዉን በሰላማዊ መንገድ ለመግለፅ የሞከሩ ተቃዋሚዎችን ተማሪዎችን እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን እንደሚጨምር ሃተታዉ ያሳያል። መንግሥት በኦሮሞዎች ላይ የጥቃት ብትር ማነጣጠሩን በምን ማረጋገጥ ይቻላል ለሚለዉ ጥያቄ በኬንያ የአምንስቲ ኢንተርናሽናል አጥኒ ክሌር ቤስተን እንደሚሉት
በዘገባችን ላይ ያቀረብነዉ ኦሮሞዎች በጎሳ አድሎ እንደሚሰቃዩ ነዉ። ከዚህ ጋር አያይዘንም እኛ የየተመለከትነዉ በኦሮሞ መስተዳድር ሰዎች ሆነ ተብሎ ዒላማ ስለሚሆኑበት አሰራር ነዉ። በኦሮምያ በፌደራል ፖሊስ ጣብያዎችና በእስር ቤቶች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ኦሮሞዎች እንደሚገኙ ብዙ መረጃዎች ይደርሱናል።»
በሪፖርቱ ላይ እንደሚያመለክተዉ የኦሮሞን ባህል ተግባራዊ የሚያደርጉ በ100 የሚቆጠሩ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል። ሰዎቹ ይህን በማድረጋቸዉም መንግሥትን እንደሚፃረሩ ተደርጎ ነዉ የተወሰደዉ። የአምንስቲ ኢንተርናሽናል አጥኚ ክሌር ቤስተን እንደሚሉት የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞ ተወላጆችን የሚያሰቃየዉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደጋፊዎች ናቸዉ በሚል ጥርጣሬ ነዉ። ግፉ የሚፈፀምባቸዉ ሰዎች ደግሞ በሁሉም ሙያና መስክ የተሠማሩ ናቸዉ።
«ገበሪዎች፤ አስተማሪዎች፤የጤና ባለሙያዎች፤የመንግሥት ተቀጣሪዎች ሳይቀሩ በዘፈቀደ ታሥረዋል። ለምሳሌ ተፎካካሪ የንግድ ተቋም ለመመስረት በመሞከሩ (የገዢዉን ሥርዓት) ርዕዮተ ዓለምን ይቃረናል በሚል የታሠረ ተማሪ አነጋግረናል።የኦሮሞ ነፃ አዉጪ ግንባር አባል ነዉ ተብሎ የሚጠረጠር ሰዉዬን ሚስት በማዋለዱ የታሠረ አዋላጅ አነጋግረናል።በማዳበሪያ አቅርቦትና ሽያጭ ቅሬታ ያሰሙ በመቶ የሚቆጠሩ ገበሬዎች ታሥረዋል።ገበሬዎቹ ባሉበት አካባቢ የሚሠራ የግብርና ባለሙያም አብሮ ታሥሯል። የሱ ተግባር የገበሬዎቹን ጥያቄ ለመንግሥት ማቅረብ ነበር።ይሁንና ገበሬዎቹን ለዓመፅ አነሳስተሐል ተብሎ ታሥሯል።»
የምርመራችን የመጀመርያዉ ደረጃ የተፈፀመዉ የህግ ጥሰቶችን ሁሉ መመዝገብ ነበር ያሉት የአምንስቲ ኢንተርናሽናል አጥኚ ክሌር ቤስተን የታፈኑትና የታሰሩትን ሰዎች ሁኔታ ሁሉ ባለመካተቱ ሪፖርቱ የተሟላ አይደለም።
« ይሁንና ከ 2011 ዓ,ም ወዲህ በኦሮምያ የነበረዉ መታመቅ ተከፍቶ በደልን በይፋ መግለፅ የተጀመረበት ግዜ ሆንዋል። ዝምታን ችላ ብሎ ስሞታን የማቅረቡ ሁኔታ ነዉ የተጀመረዉ። እስከዝያ ግዜ ብዙ ያልተናገረዉ የታፈነዉ ሁኔታ በከፊል እንደምንገነዘበዉ የኢትዮጵያ መንግሥት በነፃዉ ፕረስና ነፃ በሆኑ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ላይ እገዳ በማድረጉ ነዉ። ስለዚህም የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሁሉ በየዘርፉ በሰነድ መያዝና ለዓለማቀፍ ማሕበረሰብ መቅረብ ይኖርበታል። የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ይህ ችግር መፍትሄ እንዲያገኝ ፈቃደኛ አይደለም።»
ኦሮሞ ከኢትዮጵያ ትልቁ ብሔረሰብ መሆኑን ያመላከተዉ የአምንስቲ ዘገባ ሁለት መቶ ሰዎች በሰጡት አስተያየት ላይ የተመሠረተ ነዉ። ኬንያ የሚገኙት የአምንስቲ ኢንተርናሽናል አጥኚ ክሌር ቤስተን በሰጡት ቃለ ምልልስ ዓለማቀፉ ማህበረሰብ፤ የተመ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እንዲሁም የአፍሪቃዉ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኮሚሽን በአስቸኳይ ነጻ የሆነ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አጣሪ ቡድን እንዲያሰማራ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ሚንስትር አቶ ሪድዋን ሁሴይን ግን የአምንስቲን ዘገባ አፍሪቃን ለማንቋሸሽ ያለመ፤ የተለመደ ፖለቲካዊ አቋም በማለት አጣጥለዉታል
አዜብ ታደሰ
ተክሌ የኋላt
http://www.dw.de/%E1%8B%A8%E1%88%B0%E1%89%A5%E1%8B%93%E1%8B%8A-%E1%88%98%E1%89%A5%E1%89%B5-%E1%8C%A5%E1%88%B0%E1%89%B5-%E1%89%A0%E1%8A%A6%E1%88%AE%E1%88%9E-%E1%89%B0%E1%8B%88%E1%88%8B%E1%8C%86%E1%89%BD-%E1%88%8B%E1%8B%AD-%E1%89%B0%E1%89%A3%E1%89%A3%E1%88%B0-%E1%88%98%E1%89%A3%E1%88%89/a-18026213?maca=amh-standard_feed-amh-11646-xml
/
%89
No comments:
Post a Comment