Wednesday, May 14, 2014

የወለጋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በፖሊሶች ተደበደቡ

የወለጋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በፖሊሶች ተደበደቡ
May 14, 2014
ግንቦት ፮ (ስድስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-መንግስት በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ጓደኞቻቸው እንዲፈቱላቸው በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ሲያቀርቡ የነበሩ የወለጋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ ወደ ግቢው ዘልቀው በገቡ የፌደራል ፖሊስ አባላት ሲደበደቡ መዋላቸውን ተማሪዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል። 

የግቢው ተማሪዎች ጥያቄያቸውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ በማቅረብ ላይ ሳሉ፣ የፌደራል ፖሊስ አባላት ወደ ውስጥ ሰብረው በመግባትና የጪስ ቦንብ በመወርወር ተማሪውን በሰደፍና በዱላ መደብደባቸውን ተማሪዎች ገልጸዋል።

ተማሪው እንደሚለው በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ቆስለው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል። በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ታፍሰው ደዴሳ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ወደሚገኝ እስር ቤት መጋዛቸውን ገልጿል።

በወለጋ የሁሉም አካባቢ ተማሪዎች በአንድነት ድምጻቸውን ሲያሰሙ መዋላቸውን አክሎ ገልጿል

በሌላ ዜና ደግሞ ከአዳማ ዩኒቨርስቲ 5 ተማሪዎች ተይዘው መታሰራቸውን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

የደህንነት ሃይሎች ወደ ግቢ በመግባት ከ20 በላይ ተማሪዎችን ይዘው የወሰዱ ቢሆንም፣ 5 ተማሪዎችን አስቀርተው ሌሎችን መልቀቃቸው ታውቋል። ከ20 በላይ የድሬዳዋ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች መታሰራቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በሌላ ዜና ደግሞ በጊምቢ እና በምእራብ ወለጋ የሚኖሩ ከሌሎች አካባቢ የመጡ ሰዎች መረጋጋት መጀመራቸውን ለኢሳት ገልጸዋል

የኢህአዴግ መንግስት ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ በኦሮምያ ክልል የተነሳውን ተቃውሞ የትኩረት አቅጣጫ ለማስለወጥ የተለያዩ አሉባልታዎችን የሚነዙ ካድሬዎችን ማሰማራቱን ኢሳት በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል።


No comments:

Post a Comment