Saturday, June 15, 2013

አንድነት ፓርቲ ለመድረክ ምላሽ ሰጠ፤ የተደበቀውን አፍረጠረጠው

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ መግለጫ
በመሠረቱ ፓርቲያችን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) መድረክ እንዲመሠረትና አሁን ያለበት ደረጃ እንዲደርስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ድርጅት ነው፡፡ ለመድረክ መፈጠርና መጎልበት በአደረገው ጉልህ ተሳትፎ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለበት መሆኑን መድረክም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡   
የግምገማው ግኝቶች በየትኛውም ገጽና ቦታ የመድረክ ፕሮግራም፣ መተዳደሪያ ደንብና የስምምነት ሰነድ በመድረክ አባል ድርጅቶች በጋራና በሙሉ ስምምነት መጽደቃቸውን አላስተባበለም፡፡ አልካደምም፡፡ በተጨማሪም መድረክ እንደ አንድ የፖለቲካ ኃይል በኢትዮጵያ ሕዝብ ህሊና ውስጥ ከፍተኛ ተስፋን የፈጠረ ብቻ ሳይሆን አዲስ የጉዞና የአሠራር አቅጣጫን የቀየሰ መሆኑን ጭምር አንድነት ያውቀዋል፡፡ ያምንበታልም፡፡  
መድረክ ከመቀናጀት ወደ ግንባር የተሸጋገረበት ሂደትም ብዙ ችግሮችና ድክመቶች ቢኖሩትም በአባል ድርጅቶች ሙሉ ስምምነትና ፍቃደኘነት መሆኑን አንድነት አምኖ የሚቀበለው እውነታ ነው፡፡ በመሆኑም የመድረክ ድክመቶች፣ ስህተቶችና ችግሮች በሙሉ አንድነት ፓርቲም አብሮ የሚጋራውና የሚጠየቅበት ነው፡፡ የግምገማው ዓላማ ችግሮችንና ድክመቶችን ወደ ሌሎች የመግፋት (blame-shifting) አባዜ አለመሆኑን አበክረንና አጠንክረን እንዲታወቅልን እንፈልጋለን፡፡   
በአባል ድርጅቶች መካከል ስምምነት ያልተደረሱባቸው የፕሮግራምም ሆነ የህገ-ደንብ ጉዳዩችም በቀጣይ ውይይቶች ለማቀራረብ እንደሚሞከርና ይህ ካልተሳካም መድረክ የመንግሥት ሥልጣን ሲይዝ በሕዝብ ውሳኔ መፍትሔ እንዲያገኙ እንደሚደረግም ሙሉ ስምምነት ያገኘ ጉዳይ መሆኑ እውነት ነው፡፡ 
የመድረክ መግለጫ፣ ችግርች የሚጀምረው በመጀመሪያ ያልተካሄዱ ጉዳዩችን እንደተካሄዱ አርጎ ከማቅረቡ ላይ ነው፡፡ ሁለተኛውና መሠረታዊው ችግር ደግሞ ድርጅቶች በአንድ ወቅትና ሁኔታ ተስማምምተውና ወደው የተቀበሉት ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ ላይ ግምገማ ማካሄድ የለባቸውም የሚለው ነው፡፡ በሌላ በኩልም በአንድ ወቅትና ሁኔታ የተወሰኑ ሰነዶችን ፓርቲዎች በስምምነት ስለተቀበሉት ብቻ ሰነዶችን ትክክል ያደርጋቸዋል የሚለው ግንዛቤ ነው፡፡ ባጠቃላይ ሕይወትና በውስጡ ያሉ ክስተቶች በሙሉ የማያቋርጥ የለውጥ ሂደትና እንቅስቃሴ አካል ናቸው፡፡ በመሆኑም በማንኛውም ሥነ አመክኖ (Logic) ሰነዶች ከወቅት፣ ከጊዜና ከሁኔታዎች አኳያ (አንፃር) ይፈተሻሉ፣ ይገመገማሉ ይሻሻላሉ፣ ይለወጣሉም፡፡ 
በመግቢያው ላይ እንደተቀመጠው የግምገማው ዓላማ የመድረክ ድክመቶች የሚስተካከሉበትና ጥንካሬዎቹ የሚጎለብቱበት ሁኔታ እንዲፈጠርና ብሎም ትግሉ የሚፈልገውን ሁለንተናዊ አቅም ለመፍጠር እንዲቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአንድነት ፓርቲ ምን ዓይነት ሚና መጫወት ይገባዋል የሚለውን ጭምር ለመፈተሽ ነው፡፡ በግምገማው ሂደትም የታዩት ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ 
ሀ) ለአለፉት በርካታ ዓመታት በተቃዋሚ ጎራ አብሮ ላለመስራት ፈታኝ ሆኖ የቆየውን የኢትዮጵያ ብሔርተኘነትና ብሔር ላይ በተመሰረቱ ፓርቲዎች መካከል የነበረውን ክፍተት በተወሰነ መልኩ ማጥበቡ በአዎንታነት የሚታይ ቢሆንም፤ መድረክ ከተመሠረተ አራት ዓመት ቢያልፈውም በፕሮግራም ልዩነቶች ላይ አንድም ቀን ውይይት አለማካሄዱና ደንበቦችንም ቢሆን አብረን የቆየንባቸውን ጊዜያት ያገናዘበና ትግሉ የሚጠይቀው ደረጃ የሚመጥን ለውጥ አለማድረጉን ነው፡፡ ይህም አንዱ ዋና ምክንያት በመሆኑ መድረክ ከተመሠረተ ጀምሮ ፓርቲዎቹ የመድረክ አባል ለመሆን ያለመቻላቸው ነው፡፡ 
ለ) የመድረክን ሕገ-ደንብ በኢ-ዴሞክራሲያዊነት ለማስቀመጥ አስገዳጅ የሆነው አንዱ ምክንያት ፓርቲዎች የመተማመንና የአብሮ የመስራትን መንፈስ መፍጠራቸውና ከ4 ዓመት በኋላም በሙሉ ድምጽ ስምምነት ማለፍ ያለባቸው ጉዳዮች መኖራቸው ጭምር ነው፡፡ የቪቶ ሥልጣን የተሰጠውም የፓርቲዎችን ፍላጎትና ስጋቶች ለማስተናገድ ነው የሚለውም በግምገማው ተገቢ ሆኖ ባለመገኘቱ ነው፡፡ ትልቅ ቦታም ሊሰጠው ይገባ የነበረው ለሕዝብና ለአገር ፍላጎትና ስጋቶች ስለ ነበር ነው፡፡ 
ሐ) በግንባሩ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት እያንዳንዱ የመድረክ አባል ፓርቲዎችና አመራሮች በአባል ድርጅቶች ላይ አፍራሽ አስተያየት ከመስጠት መቆጠብ አለባቸው የሚል ሆኖ ሳለ በተለያዩ ጊዜያት በተደጋጋሚ በአንድነት ፓርቲና በአመራሮቹ ላይ የተሰነዘሩ አፍራሽና ጎጂ አስተያየቶችን በግልጽ በማስቀመጥ ፓርቲዎችና አመራሮች ወደ ትክክለኛው አቅጣጫና መስመር ይመለሱ ዘንድ አባሎችና ሕዝቡም የራሱን ገንቢ አስተዋጽአ እንዲያደርግ ነው፡፡ ከሁሉም በጣም ቅር የሚያሰኘው የመድረክ መግለጫ አፍራሽ አስተያየቶችን ሃሳብን በነፃነት ከመግለጽ መብት ጋር ማያያዙ ነው፡፡ በምን መመዘኛ ነው፡- 
‹‹አንድነት ዶ/ር ነጋሶን ሊቀመንበር አድርጎ ቢመርጥም የአማራ ፓርቲ ወይም የአዲስ አበባ ልሂቃን ፓርቲ መሆኑን መካድ አያስፈልግም›› 
‹‹የአንድነት አዝማሚያ በደቡቦች፣ በአረና እንዲሁም በኦሮሞ ላይ የበላይነትን ለማሳየት ነው››
‹‹ አንድነቶች ፌዴራሊዝምን አይወዱም ፌዴራሊዝሙን የሚጠሉት አማራሮች ናቸው››
‹‹ ከዶ/ር ነጋሶ ውጭ መሪዎቹ አማሮች ናቸው፡፡ ይህን የምለው ስለማውቀው ነው››
‹‹ ህብረ ብሔራዊ ፓርቲ ሲዳማ ወለጋ ወ.ዘ.ተ ሄዶ ድምጽ ማግኘት አይችልም››
‹‹ ኦሮሞ አማራ ክልል ሄዶ ምረጡኝ ቢል ድምጽ አያገኝም፡፡ ኦሮሞ ከሆነ 
ለምን ኦሮሞ ፓርቲ አይገባም አማራው ኦሮሞ አገር ሄዶ አይመረጥም›› 
ይህን የተናገሩት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ናቸው፡፡ በሌላ በኩልም ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ በተደጋጋሚ፡- 
1. የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን መመረጥ የሚያውቀው ኢህአዴግ ነው፡፡ የእሳቸው መመረጥ የኢህአዴግ አሻጥር ነው፡፡ 
2. ስንትና ስንት የዴሞክራሲ አርበኞች ባሉበትና ደጋግመው በምርጫ ያሸነፉ ሰዎች እያሉ አንድ ተወዳዳሪ ብቻ አሸንፋል መባሉ አሳፋሪ ነው ብለዋል፡፡ 
የደቡብ ህብረት ፓርቲ በአቀረበው የክስ ማመልከቻ፡- 
አንድነቶች ‹‹በአቋራጭ ሥልጣን የሚልፈጉ የነፍጠኛ አቋም ያላቸው ናቸው›› እነዚህ አነጋገሮች አፍራሽና አጥፊ ፕሮፓጋንዳ አካል ናቸው፡፡ ከላይ በአንድነት ፓርቲ ላይ ከተሰጡ አስተያየቶች መካከል የተወሰኑቱ ‹‹ጠባብ ብሔርተኝነት›› ባህሪያት የማያመላክቱ ከሆነ ምንን ነው የሚያመላክቱት? ሌሎችንም ምሳሌዎችንና ድርጊቶችንም መጨመር ይቻል ነበር፡፡ ሁኔታው በአጭሩ ለመተው ሲባል እንጂ፡፡ 
መ) ግምገማው የአንድነትን ብሔራዊ ምክር ቤትን፣ የሥራ አስፈፃሚውንና በመድረክ የአንድነት ተወካዮች ሚና በትኩረት የተመለከተውና የሰሉ ሂሶችን እንደየ ተጠያቂነታቸው ደረጃ የአሳረፈባቸው እንጂ እንዲያው ችግሮችን ወደ መድረክና አባል ፓርቲዎች የወረወረ አይደለም ወደ ውጭ እንዳየ ሁሉ ወደ ውሰጥም አይቷል፡፡ 
ሠ) በመጨረሻም ግምገማው የመፍትሔ አሳቦችን በአጭር ጊዜና በረጅም ጊዜ በመከፋፈል ጠቃሚ አስተያየቶችን ሰጥቷል፡፡ በተለይም ተቀዋሚ ፓርቲዎች አሁን የሚንቀሳቀሱበት የፖለቲካ ምህዳር እጅግ ፈታኝ የሆነበት ወቅት በመሆኑ የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲ በአገራችን ጠንካራ መሠረት እንዲይዝ የተቃዋሚ ኃይሎች የመጠላለፍ፣ የመጠፋፋት ፖለቲካ የትም እንደማያደርስ በመገንዘብ በመተጋገዝ በአብሮ መስራት መንፈስ አብሮ መቆም እንዳለባቸው ነው፡፡ የሚያሳየው ከአብሮ መሥራት ውጭ በአገራችን ውስጥ ለውጥ ሊመጣበት የሚችልበት እድል ዝግ እንደሆነ ነው ያመላከተው፣ ያሳየው፡፡ ማንኛውም ፓርቲ የቱንም ያህል ትልቅነኝ ቢልም፣ ትልቅ ቢሆንም ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበትን ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ብቻውን ሊወጣው እንደማይችል ነው የታመነበት፡፡ 
እውነታውና የግምገማው ዓላማና ግኝቶች ይህ ሆኖ ባለበት ሁኔታ አንድነትን በመድረክ አፍራሽነት ለመፈረጅ መሞከር ‹‹ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ›› ያስመስለዋል፡፡ ይልቁንም አንድነት ለግምገማውም ሆነ በተግባር ያረጋገጠው ለመድረክ ጥንካሬ ብርታትና ወደ ፊት መራመድ እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ አሁንም በትጋት እንደሚሰራ በድጋሚ ያረጋግጣል፡፡ ግምገማዎችን ማካሄድና ውስጣዊ ድክመቶች አንጥሮ በማውጣት ከዚያም ትምህርት አግኝቶና እርምት አድርጎ መራመድ ‹‹ኢህአዴግን ነው የሚጠቅመው፤ ሕዝብን ያሳዝናል›› በሚል መርህ በሽፍንፍን መጓዝ ከአገኘነው ተሞክሮ አፃር ሲታይ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ 
በመጨረሻም ለመድረክ የምናሳስበው ቁም ነገር የተፈፀሙን የአካሄድ ስህተት ምክንያት በማድረግ የግምገማውን ይዘት አልቀበልም ማለቱ ማንንም እንደማይጠቅም በድጋሚ ተመልክቶ በይዘቱ ላይ ውይይት እንዲከፈት እንዲያደርግ በአጽኖት እንጠይቃለን፡፡ ይህ እስከሆነ ድረስ የአብሮ መስራቱና መተባበሩ ተግባር አሁንም ይቀጥላል፡፡
ሰኔ 5 ቀን 2ዐዐ5 ዓም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment