“ … አንተም ሆንክ ማንም ኢትዮጵያዊ ውጪ ያሉትን ጨምሮ ቢደግፉን ደስ ይለናል። በዚህ መንገድ ሂዱ ብለው እንዲጠመዝዙን ግን አንፈልግም። … ሰላማዊ ትግል የምትሉት ለውጥ አያመጣም ይሉናል። እንደዚህ የምትሉ ከሆነ ከፈለጋችሁ ገንዘብ አትርዱን እንላቸዋለን … ኢህአዴግን እንደ መንግስት እውቅና አንሰጠውም” ከዶ/ር ነጋሶ የተመረጡ መልሶች መካከል የተጠቀሱ ናቸው። በዚህና በሌሎች ምክንያቶች ዶ/ር ነጋሶ ሊሞገቱ ሄደው ሞገቱ የሚል ርዕስ ለጽሁፌ መረጥኩ።
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አንድነትን በመወከል ሬዲዮ ፋና በሚያዘጋጀው የ”ሞጋች” ቃለ ምልልስ ክፍለ ጊዜ ላይ ተገኝተው ነበር። ቃለ ምልልሱ ከመጀመሩ በፊት “ጋዜጠኛው” ፕሮግራሙ ፈረንጆቹ እንደሚሉት “ሃርድ ቶክ አይነት ነው” አለ። ይህን ጊዜ ቀልቤን ሳበኝ። የቢቢሲው የሃርድ ቶክ ክፍለጊዜና የጠያቂው ጠልቆ የመግባት ችሎታ ታየኝና ዶ/ር ነጋሶ ሲዝረከረኩ ለመስማት ተዘጋጀሁ።
ጥያቄ ተጀመረ። ዶ/ር ነጋሶ መመለስ ቀጠሉ። የመጀመሪያዎቹ ጥያቄዎች የተለመዱ፣ የተረገጡ፣ የተሰለቹና በየመድረኩ ብዙ የተባለላቸው ሆኑብኝ። ዶ/ር ነጋሶም ሳይቸገሩ ከፈገግታ ጋር መለሱ። በመነሻው የቀረቡትን የተለመዱ ጉዳዮች በመዝለል በሶስት ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሪፖርት ለማዘጋጀት ወሰንኩ።
ስለ ጠያቂው
ጠያቂው ጋዜጠኛ ነጋሶን ሲጠይቅ ላዳመጠ ጋዜጠኛ ሳይሆን ትክክለኛ ስሙ “ካድሬ” ነውና በዚህ ይስተካከል። መጀመሪያ ላይ “ይባላል፣ ይነገራል፣ ይደመጣል፣ አስተያየት ይሰጣል …” በማለት አግባብ ያለው አካሄድ ተከተለና በኋላ ላይ ግምገማ ፍርሃቻ ነው መሰል ነጋሶን አላናገር ብሎ ጭልጥ ያለ ክርክር ውስጥ ሲገባ ከኋላው አቶ ሴኩ ቱሬ ጌታቸው ምናምን የሚያሳዩት ይመስል ነበር። ያም ቢሆን “ገራም”፣ ቀስ ብሎ የሚናገርና በድርጅት ፍቅር የደረቀ አይመስልም።
የግራ ዘመም ስለመሆናቸው
ነጋሶ አሁን የሚመሩት አንድነት ፓርቲ የሊብራል ፖለቲካ እሳቤ አቀንቃኝ ነው። እሳቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ “የግራ ዘመም” ፖለቲካ አፍቃሪ ነበሩ። ኢህአዴግ ውስጥም ዋናው የልዩነታቸው መሰረት የግራውን መንገድ በትክክል መከተል ያለመቻልና የመበረዝ ችግር ነው። ዛሬ ምን ተገኘና ነው አዲስ አቋም የተያዘው በሚል ጠያቂው ያነሳው ሃሳብ የስሙን ያህል ባይሆንም ሙግት አስነስቶ ነበር። ጥያቄው ግን ምላሽ ያገኘው ውይይቱ ሲያልቅ ነው።
“ግራ ዘመም ምንድነው” አይነት ጥያቄ አንስተው ከዓለም ወቅታዊ ሁኔታ ጋር መመሳሰል አግባብ እንደሆነ በማስገንዘብ አስተያየታቸውን የሰጡት ነጋሶ፣ “ትክክለኛ” የሚሉትን ሶሻሊዝም እንደሚናፍቁ አልሸሸጉም። ይህ አስተሳሰባቸውና እምነታቸው አንድነት ከሚከተለው መንገድ ጋር እንዴት ሊጣጣም እንደሚችል የገለጹት ግን ዓለምን መምሰል በሚለው እሳቤ ነው። ጠያቂው በውይይቱ ማሳረጊያ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት በድጋሚ ይህንኑ ጉዳይ አንስቶ ነበር። ነጋሶ ግን “አንድ ሰው ድንጋይ አይደለም። አቋሙን መቀየር ወንጀል አይደለም” በሚል ዘጉት። አዎ፣ አቋም ለያውም በፖለቲካው ጎዳና የሚቀያየር፣ ዓለምን እያዩ የሚበውዙት የካርታ አይነት ጨዋታ ነው። እናም “እሰይ አበጀሁ” አይነት መልስ መልሰው ተሰነባበቱ።
የጣመኝ የ“ፈርሙ” ክርክር
የምርጫ የስነ ምግባር ኮድ ጉዳይ ለዚህ ሪፖርት አቅራቢ ምርጥ የተባለና የነጋሶ የህግ ግንዛቤ በቀላሉ ነገሮችን በማስረዳት ጎልቶ የወጣበት ነበር። እንዲህ ተባባሉ። ጠያቂው “የምርጫ ስነ ምግባር ኮዱን ብትፈርሙ ምን ትሆናላችሁ?” አለ። “አዋጅ በሆነ ጉዳይ ላይ ለምን እንፈርማለን። እንደዚህ ከሆነ ባገሪቱ በየጊዜው በሚወጡ ህጎች ላይ እንፈርማ?” የነጋሶ ውድ መልስ ነበር።
ጥያቄ፦ ብትፈርሙ ምን ይጎዳችሁዋል …?
ነጋሶ፦ ለምን እንፈርማለን? ለህዝብ ጥቅም ሁላችንም ስንሰራ ኢህአዴግ በሚለው ተንበርክከህ ኢህአዴግን በምርጫ በማጀብ አይደለም …
ጥያቄ፦ ጉዳት አለው ህዝቡ ይጎዳል? ህግ ሆኗል አይደለም?
ነጋሶ፦ የስነ ምግባር ኮዱ ብቻውን በቂ አይደለም፤…. የኢህአዴግ አዲሱ ሊቀመንበር በመጀመሪያው ንግግራቸው ያሉትን አልሰማህም?
ጥያቄ፦ … ምን ጉዳት ይደርስባችኋዋል?
ነጋሶ፦ እነሱ ቢወያዩና ችግራቸውን ቢያስወግዱ ምን ችግር አለው?
ጥያቄ፦ ፖለቲካ አብሮ የመኖር ጥበብ ነው። አብሮ መስራት ጥቅም አለው፤
ነጋሶ፦ ያ! ያ! አብሮ መስራት በእኩልነት ነው እኮ!! ኢህአዴግ አንድ የፖለቲካ ሃይል ነው ወይስ አይደለም? ለምን እንበረከካለን? ንግረኝ?
ጥያቄ፦ ለህጉ ትገዙ አይደል?
ነጋሶ፦ ያ!! እኮ፤ አዋጅ ሆኖ በወጣ በስንት ህግ ላይ እንፈርማለን? ይህ ከሆነ ፓርላማ ቢስማማም ባይስማማም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሁሉም ጉዳዮች ላይ መፈረም አለበት ማለት ነው፤
በቀጣይ ወደ ሌላ የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ አልፉ። ማጠቃያው ላይ አነሳዋለሁ፡፡
ለስደተኞችና ለስደተኛ አስተሳሰብ ትገዛላችሁ?
ጠያቂው ሊሞግት ያሰበበት ዋናው ጉዳይ መድረክም ሆነ አንድነት ከዲያስፖራው ጋር ያላቸውን ግንኙነት በሚያውጣጣና በትጥቅ ትግል ከሚያምኑ ወገኖች ጋር ለመደመር ነበር። ከውጪ ሃይሎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር፣ እንደሚታሙና ለዚህም መረጃ እንዳለው አንስቶ ላቀረበው ጥያቄ ማሰሪያ ያደረገው “አገር ቤት ያለውን ህዝብ አክብሮት አትሰጡትም። ለስደተኛና ለስደተኛ አስተሳሰብ ልዩ አክብሮት አላችሁ” የሚል ነበር።
ነጋሶ ከወትሮው ለየት ብለው ፖለቲካኛ የሆኑበትን መልስ የሰጡት ዲያስፖራውም ሆነ ማንም፣ ጋዜጠኛውን ጨምሮ ቢደግፉዋቸው ደስተኛ መሆናቸውን በማመለካት መልስ ጀመሩ። አስከትለውም “በየኤምባሲው ደጅ አይታጡም” እንባላለን አሉ። ነጮቹ የሚሰጡት ድጋፍ ለተሰጠበት ዓላማ እንዳልሆነ ለምን አትናገሩ ይባላል? በማለት ጠየቁ።
ስለ ዲያስፖራውና “ስደተኛ አስተሳሰብ” ስለተባሉት ሲናገሩ የሰላማዊ ትግል መንገዱ አያዋጣም የሚሉዋቸው እንዳሉ አመለከቱ። ሲያጠቃልሉት ማንም ይሁን ማን “ሰላማዊ ትግል አያዋጣችሁም ለሚሉን ከፈለጋችሁ ገንዘባችሁን አትርዱን እንላቸዋለን” በማለት የራሳቸውን መንገድ እንደሚከተሉ ገልጸው ጥያቄውን ቆለፉት።
አገር ውስጥ ያለውን ህዝብ አታከብሩትም ለሚለው ግን “በርግጥ በሚፈለገው ደረጃ ህዝብ ውስጥ ላንቀሳቀስ እንችላለን” በማለት ራሳቸውን ጥፋተኛ አስመስለው ቢሮ ይታሸግብናል፣ እኛን የሚደግፉ ከስራ ይባረራሉ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አይፈቀድልንም፣ ሰላማዊ ሰልፍ እንድናደርግ አይፈቀድም፣ መምህራን እኛን ስለደገፉ ይባረራሉ፣ … ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ኢህአዴግ እንደሆነ ተናገሩ።
ኢህአዴግን ተቀብለውና ደግፈው ከሚሰሩ ፓርቲዎች ጋር አብረው መስራት እንደማይችሉ ሲገልጹ “ኢህአዴግን ከሚደግፉት ጋር ተቀምጠን ምን አብረን ልንሰራ እንችላለን” ካሉ በኋላ “ኢህአዴግን እንደመንግስት እውቅና ሰጥተው ከሚንቀሳቀሱት መካከል ኢዴፓ በርካታ ልዩነቶች አሉት ግን ኢህአዴግን እንደ መንግስት እውቅና በመስጠት ይቀበላል። እናንተስ?” በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ኢህአዴግ በህዝብ፣ በምርጫ ገዢ ያልሆነ ፓርቲ ስለሆነ እውቅና አንሰጠውም” የሚል ግልጽ መልስ ሰንዝረዋል።
“ስለ አንቀጽ 39 ለምን አሁን ትጠይቀኛለህ?”
ነጋሶ ፓርቲያቸው አንቀጽ 39 እና የመሬት ጉዳይ ላይ ስላለው አቋም ግልጽ ያለ መልስ እንዲሰጡ በተደጋጋሚ ተጠይቀው ነበር። በግራም ሆነ በቀኝ፣ እሳቸው በጻፉት መጽሃፍ ላይ ካቀረቡት ሃሳብ ጋርና ቀደም ሲል ኢህአዴግ በነበሩበት ወቅት ሲያራምዱት ከነበረው ሃሳብ አንጻር የሃሳብ መንሸራተት እንዳጋጠማቸው በማስመሰል ጠያቂው ሊሞግታቸው ሞክሮ ነበር። በተደጋጋሚ ለማስረዳት ቢሞክሩም ሊቀበላቸው ባለመቻሉ “አንድ ሰው ድንጋይ አይደለም። የአቋም መቀያየር ወንጀል አይሆንም” በማለት አሳርገውታል።
በጥቅሉ ግን ካላይ የተነሱት ሁለት መሰረታዊ ሃሳቦች ህዝብ ውሳኔ ሊያሳልፋቸው እንደሚገባ አመልክተዋል። መገንጠል መብት ቢሆንም እርሳቸው እንደማይደግፉት በግልጽ አስቀምጠው ያለፉት ነጋሶ፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በመመስረት የሚመለሱ ጉዳዮች እንደሆኑ ግን አስምረውበታል። ምንም እንኳ ፓርቲያቸው የኒዎ ሊብራል ሃሳብ አራማጅ ቢሆንም በግላቸው በነጻ ኢኮኖሚ ስም መንግስት ከዋናና ህዝብን ከሚያገለግሉ ዋና ዋና የኢኮኖሚ አውታሮች መውጣት አለበት ብለው እንዳማያምኑ አስምረውበታል። በመድረክ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች ተመሳሳይ አቋም ባልያዙበት ሁኔታ ግንባር መመስረቱ ችግር እንዳለው ለቀረበላቸው ጥያቄ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነና ዋና የሚባሉት የልዩነት ቁልፍ ጉዳዮች ህዝብ ውሳኔ እንዲሰጥባቸው በመዘርዘር አልፈዋቸዋል።
ጠያቂው መሃል በመግባት አንቀጽ 39ን ትቀበላላችሁ? በሚል ላቀረበላቸው “አሁን ለምን ትጠይቀኛለህ” በማለት አስረግጠው መልስ ሰጥተዋል። በዚሁ የራዲዮ ፋናን ስቱዲዮ በስንብት ለቀው ወጥተዋል።
ነጋሶ እንደ ፖለቲከኛ ድርጅቱ ላይ ደረሱ የተባሉትን ችግሮች በየመካከሉ በማስገባት ጥያቄን በጥያቄ መመለስ ቢችሉ ኖሮ ይበልጥ አሸናፊ ሆነው መውጣት ይችሉ ነበር። ለምሳሌ ስለህጋዊነት ሲነሳ የራዲዮ ፋና አፈጣጠር ህጋዊ አለመሆኑንና ኤፈርት ስለተቆታጠረው የኢኮኖሚ የበላይነት፣ ስለ እስርና የሚዲአ አፈና … በየመልሶቻቸው መካከል በማስገባት ቢመልሱና ጥያቄ ቢሰነዝሩ ቢያንስ ሃሳባቸውን በአድማጭ ላይ አራግፈው መውጣት በቻሉ ነበር። እንዲህ ያለ ሰፊ የሚዲያ ሽፋን ሲገኝ መሰረታዊ ብቻ ሳይሆን ራሳቸው የኢህአዴግ አባላት የሚያጉረመርሙትን ጉዳዮች በማንሳት የራሳቸውን ልምድና ተሞክሮ ማካፈል ይችሉ ነበር። ጠያቂው ከኢህአዴግ ስለተለዩበት ምክንያት በሰሚ ሰሚ ላነሳላቸው ጥያቄ “ቆቅ” ፖለቲከኛ ሆነው መረጃ ማስተላለፍ ሳይችሉ መቅረታቸው የዕለቱ ድክመታቸው ቢሆንም ሊሞገቱ ተጋብዘው ሞግተው ስለመውጣታቸው የዚህ ሪፖርት አቅራቢ ምስክራቸው ነው፡፡
No comments:
Post a Comment