Thursday, June 19, 2014

‹‹ይህ ሽልማት የእኔ ብቻ አይደለም፣ የእናንተም ነው›› እስክንድር ነጋ


June 18, 2014
በኤልያስ ገብሩ ጎዳና
‹‹ይህ ሽልማት የእኔ ብቻ አይደለም፡፡ የእናንተም ነው፡፡ …››
‹‹በእስር ላይ የምትገኙ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያኖች የእኔ ጀግኖች ናችሁ››
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ
‹‹አሁን ደስተኛ ነኝ››
‹‹እስክንድርን ምግብ ማብሰል እያለማመድኩት ነው››
አቶ አንዷለም አራጌ
ከትናንት በስትያ ሰኔ 03 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ላይ ከቅርብ ጓደኛዬ እና የሙያ ባልደረባዬ ጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ ጋር ወደቃሊቲ ማረሚያ ቤት [እስር ቤትም ነው] አምርተን ነበር- ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋንና የአንድነት ፓርቲ ጸሐፊ የሆኑትን አቶ አንዷለም አራጌን ለመጠየቅ፡፡ የተለመደውን የፖሊስ ፍተሻ አልፈን ወደ ውስጥ ስንዘልቅ የሰማያዊ ፓርቲ የድርጅት ጉዳይ ኃላፈ አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ ፣ አቶ ሳሙኤል የተባሉ አባልና የ‹‹ነገረ ኢትዮጵያ›› ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው እስክንድርን ሊጠይቁ ቀድመውን ደርሰው ነበር፡፡Ethiopian political prisoners Eskinder Nega and Andualem Arage
…እስክንድርን እና አንዷለምን አስጠራናቸው፡፡ ሁለቱም ሲያዩን ደስ አላቸው፡፡ በተለይ በተለይ የእስክንድር ፈገግታ በጣም ደማቅ ነበር፡፡ ተከፋፍለን ከሁለቱም ጋር ሃሳቦችን መለዋወጥ ጀመርን፡፡
እስክንድር በዓለም የጋዜጠኞች እና የዜና አታሚዎች ማኅበር የዓመቱ የወርቅ ብዕር የ “pen Golden of freedom 2014″ ተሸላሚ በመሆኑ ‹‹እንኳን ደስ ያለህ›› አልኩት፡፡ ‹‹አመሰግናለሁ፡፡ ትናንት አንድ ልጅ ሊጠይኝ መጥቶ ነግሮኛል›› ካለን በኋላ ደግመን ስለሽልማቱ በጋራ ሃሳብ መለዋወጥ ቀጠልን፡፡ እስክንድር ሽልማቱ አዲስ መሆኑን አላወቀም ነበር፡፡
በመሆኑም ስለሽልማቱ ሁኔታ፣ ማን እንደሸለመው፣ ሽልማቱ የት እንደተደረገ፣ ሽልማቱን ማን እንደተቀበለለት [ሽልማቱን የተቀበለው በኢትዮጵያ በሽብርተኝነት ክስ ወንጀለኛ ተብሎ ከባልደረባው ፎቶ አንሺ ጋር 11 ዓመታት ከተፈረደበት በኋላ በይቅርታ የተለቀቀው ስዊድናዊ ጋዜጠኛ ማርቲን ሽብዬ ነበር]፣ የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ምን እንደሚመሰል፣ በሽልማቱ እነማን እንደተገኙ …ያወቅነውን ሁሉ ነገርነው፡፡
‹‹ይህንን አላዋኩኝም፣ ሰርካለም (ባለቤቱ) ለምን በቦታው አልተገኘችም?›› በማለት ጠየቀንና በድጋሚ ደስ ብሎት ጣቶቹን በሽቦ ውስጥ አሾልኮ ጨበጠን፡፡ ወዲያው ይህቺን መልዕክት ተናገረ፡-
‹‹ይህ ሽልማት የእኔ ብቻ አይደለም፡፡ የእናንተም ነው፡፡ የኢትዮጵያዊ ጋዜጠኞች ነው፡፡ ሁላችንንም ይመለከተናል፡፡ ለሁላንችም ይገባናል፡፡ ይሄንን ሽልማት የምመለከተው ሐሳብን በነጻነት ከመግለጽ የመብት ጥሰት አኳያ ብቻ አይደለም፡፡ ለሌሎች የዜጎች መብቶች ሲሉ ለታገሉ እና እየታገሉ ላሉ ፖለቲከኞች፣ የሕሊና እስረኞችም ጭምር ነው፡፡ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከሌሎች ከተነፈጉ መብቶች ተለይቶ የሚታይ አይደለም፡፡ ሁሉንም መብቶች እናገኛቸዋለን፣ ወይም እናጣቸዋለን፡፡ ለዚህ ደግሞ ጸንተን እንታገል፣ ትግላችን ግን ሰላማዊ ብቻ መሆን አለበት፡፡ …››
እስክንድር ደስ ብሎት ሃሳቡን መናገሩን ቀጥሏል፡፡ እኔ ለተወሰኑ ቀናት በማዕከላዊ መታሰሬን ሰምቶ ስለነበረም ‹‹ማዕከላዊ እያለህ የታሰሩትን ጋዜጠኞች እና ጦማሪያኖች ለማግኘት ችለህ ነበር?›› ብሎ ጠየቀኝ፡፡ እነሱን በአካል ማግኘት አለመቻሌን ነገር ግን ከእነሱ ጋር ታሥረው የነበሩ ሌሎች ተጠርጣሪ ዜጎችን አግኝቼ በእስር ስላሉበት ሁኔታ መጠየቄን ነገርኩት፡፡
የታሰሩት ጋዜጠኞች እና ጦማሪያኖችን ቤተሰብ ማግኘት እችል እንደሆነና ከቻልኩም በእነሱ በኩል መልዕክቱ ይደርስለት ዘንድ በድጋሚ ጥያቄያዊ ሃሳቡን አቀረበልኝ፡፡ የተወሰኑ የእስረኛ ቤተሰቦችን ማግኘት እንደምችል አስረዳሁት፡፡
‹‹የታሰራችሁ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያኖች የእኔ ጀግኖች ናችሁ፡፡ አከብራችኋላሁ፡፡›› ብለህ ንገርልኝ አለኝ – ደጋግሞ፡፡ …
በዕለቱ ከሰዓታት በፊት ሰናይት ታከለ የምትባል ወዳጄም እስክንድርን ልጠይቀው ቃሊቲ እንደምሄድ በነገርኳት ጊዜ ‹‹እንደማከብረው እና እንደማደንቀው ንገርልኝ›› ያለችኝን መልዕክት ለእስክንድር አደረስኩላት፡፡
እሱ ግን ሳቅ እያለ ‹‹ተሳስተሻል! …ተሳስተሻል! …ተሳስተሻል›› ብለህ ንገራት አለኝ፡፡ ‹‹ለምን?›› አልኩት፡፡ ‹‹ገና ምን ሰርቼ?›› በማለት በዚያ ትሁት አንደበቱ መለሰልኝ፡፡ በእውነት መልሱ አስደመመን፡፡ ዋይ እስክንድር፣ ፍጹም የተለየ ታላቅ ሰው!!!
እስክንድርን እናናግረው የነበርን ጠያቂዎች ወደ አንዷለም አራጌ ዞርን፡፡ አንዷለም ጋር የነበሩት ደግሞ ወደ እስክንድር፡፡
አንዷለም የስፖርት ቲ-ሸርት ከቁምጣ ጋር ለብሷል፡፡ ጥቁር መነጽር አድርጓል፡፡ ረጋ ብሎ ፈገግ በማለት ‹‹ምን አዲስ ነገር አለ?›› በማለት ጨዋታ ጀመረ፡፡ አንዷለም የእስክንድርን ሽልማት ሰምቶ ኖሮ፣ ‹‹አሁን ከምሳ በኋላ ጣፋጭ የለውዝ ሻይ እሱን እና ጓደኞቻችንን በመጋበዝ ‹እንኳን ደስ ያልህ!› በማለት ሰርፕራይዝ አደርገዋለሁ፡፡ ምግብ ማብሰል እያለማመድኩት ነው፡፡ ብዙ ጊዜ እኔ ነኝ ሰርቼ የማበላው፡፡ በልጅነቱ በበርገር ያደገ ልጅ አሁን ሽንኩርት እና ቲማቲም መክተፍ ችሏል …›› በማለት በቀልድ ነገረን፡፡
‹እነማን ከእናንተ ጋር አሉ? በአንድ ክፍል ውስጥስ ስንት ናችሁ? ጊዜያችሁንስ እንዴት ነው የምትጠቀሙበት?›› የሚል ጥያቄ አቀረብንለት፡፡
‹‹ለረዥም ጊዜ፣ በጣም አስቸጋሪ ክፍል ውስጥ፣ መሬት ላይ ስንከባለል ነበር በእስር ያሳለፍሉት፡፡ አሁን አቶ ስዬ አብርሃ ታስሮ በነበረበት ጥሩ በሚባል ክፍል ውስጥ ለአምስት ታስረን እንገኛለን፡፡ አቶ መላኩ ተፈራ፣ አቶ መላኩ ፈንታ ና አንድ ባለሃብት አብረውን ናቸው፡፡ አሁን አልጋ ላይ መተኛት ጀምሬአለሁ፡፡ ይሄ ለእኔ እንደ አዲስ ሕይወት ነው፡፡ አሁን ደስተኛ ነኝ፡፡ …ጊዜያችንን በጥሩ ሁኔታ ከፋፍለን እየተጠቀምንበት ነው፡፡ እናነባለን፣ እንወያያለን፣ የምንፈልጋቸውን መጽሐፍት ግን በምንፈልገው ጊዜ አናገኝም፣ በዚህ በኩል መጠነኛ ችግር አለ፡፡ በተረፈ ደህና ነኝ፡፡ እኔ ተስፈኛ ነኝ፡፡ እናንተም በተሰማራችሁበት ዘርፍ የምትችሉትን ሁሉ ለሀገራችሁ ለውጥ መታገል አለባችሁ…››
ከሁለቱም ጋር የነበረንን የ30 ደቂቃ ቆይታ ሳንጠግብ ‹‹በቃችሁ›› የሚለው የፖሊስ ድምጽ ተሰማ፡፡ ‹‹እናመሰግናለን፣ በቃ ሂዱ›› ሲል አንዷለም በእርጋታ ተናግሮ በሽቦ ስር አሾልኮ እጆቻችንን ጨበጠን፡፡
እስክንድር ደግሞ ‹‹‹ሲመቻችሁ ብቻ መጥታችሁ ጠይቁን፣ ሥራ እንዳይበደል!፡፡ ሥራችሁን ሥሩ›› በማለት ለእኛም ያለውን አሳቢነት ከምክሩ ጋር ደጋግሞ ገለጸልን – ሁሉንም ሰላም በሉልኝ በማለት፡፡ እንግዲህ እስክንድርን የምትሉ ሁሉ ሰላምታውን በእኔ በኩል አድርሻለሁ፡፡

Tuesday, June 10, 2014

በሃረር በጅምላ የተቀበሩ ሰዎች መቃብር መገኘቱን ተከትሎ ግጭት ተነሳ June 10/2014

ሰኔ ፫(ሦስት)ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በቀበሌ 19 ልዩ ስሙ ሃመሬሳ ወይም መድፈኛ ጀርባ በሚባለው አካባቢ ሰኔ 2 ቀን 2006 ዓም በቁፋሮ ላይ የነበረ አንድ የግሪደር ሹፌር የተከማቹ አስከሬኖችን አግኝቷል።

የ2ቱ አስከሬን ምንም አይነት የመበስበስ ምልክት አለማሳየቱን የገለጸው ወኪላችን፣ ግለሰቦቹ በቅርቡ የተገደሉ መሆናቸውን ያሳያል ብሎአል። አንደኛው ሟች እጆጁን ወደ ሁዋላ ለፊጥኝ ታስሮ የተገኘ ሲሆን ሌላው ደግሞ አይኖቹ በጨርቅ ተሸፍነዋል።

የአራት አስከሬኖች አጽምም እንዲሁ አብሮ መገኘቱን የገለጸው ወኪላችን ፣ ቀደም ብለው የተገደሉ መሆናቸውን መረዳት እንደሚቻል ገልጿል።

ህዝቡ አስከሬኖቹ እንዳይነሱ እና ምርመራ እንዲካሄድባቸው ጥያቄ ቢያቀርብም፣ ፖሊስ ፈቃደኛ ባለመሆኑ አስከሬኖቹን በማንሳት ከዋናው ቦታ በቅርብ ርቀት በሚገኝ ቦታ ላይ እንዲቀበሩ አድርጓል። በቅርቡ የተገደሉትን የሁለቱን አስከሬኖች ማንነት ለማወቅ አልተቻለም።

የግሪደሩ ሾፌር አስከሬኖቹን እንዳየ ራሱን በመሳቱ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

ኢሳት  በሃረር ፖሊስ ጣቢያ ታስረው የነበሩ ሁለት ወጣቶች አድራሻቸው መጥፋቱን መዘገቡ ይታወሳል።

ስቱዲዮ ከመግባታችን በፊት ደግሞ የአወዳይ ህዝብ ዛሬ  ሰኔ 3 ወደ አካባቢው በመኪና ተጉዞ ከደረሰ በሁዋላ ተቃውሞ አሰምቷል። የፌደራል ፖሊስ እና የክልሉ ፖሊስ በጋራ በአስለቃሽ ጭስ እና በተኩስ ተቃውሞውን የተቆጣጠሩት ሲሆን፣ ህዝቡ በወሰደው እርምጃ በርካታ ፖሊሶች ቆስለዋል። የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የልዩ ሃይል ዋና አዛዥ የሆኑት ኮማንደር ሳላሃዲን ግራ አይኑ አካባቢ በድንጋይ ተመትቶ ከባድ ጉዳት ደርሶበት ወደ ሆስፒታል ተወስዷል።

አካባቢው በክልሉ የኢንዱስትሪ መንደር የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በአነስተኛ እና ጥቃቅን ስም ለተደራጁ የባለስልጣናት ዘመዶች መሰጠቱን የዘገበው ወኪላችን፣ ለግንባታ የሚውሉ እቃዎች የተጠራቀሙበት መጋዘን በህዝቡ እንዲቃጠል ተደርጓል።

የህዝቡ ጥያቄ “አስከሬን እንዴት የትም ይጣላል፣ ትክክለኛ ቦታ ተፈልጎ በክብር ሊያርፍ ይገባል” የሚል መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል።

የኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት ወደ አካባቢው ተጉዘው ለማረጋጋት ሙከራ አድርገው ባለመሳካቱ ፖሊሶች ህዝቡን በሃይል ለመበተን መገደዳቸውን ወኪላችን አክሎ ገልጿል።

ሀመሪሳ ከአወዳይ ወደ ሃረር መግቢያ ሲሆን አካባቢው ጫካ እና ሜዳ ነው።

በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን ፖሊስ ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።

Wednesday, June 4, 2014

አባ ዱላና ከንቲባ ድሪባ የቁም እስረኛ ሆኑ፣ ፓስፖርታቸው ተቀማ

“የኢህአዴግ በርዕዮተዓለም መበላላት ይፋ እየሆነ ነው”
abadulla and deriba
አባ ዱላ ገመዳና የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማ ፓስፖርታቸውን ተነጥቀው የቁም እስረኞች መሆናቸው ከተለያዩ ምንጮች እየወጡ ያሉ መረጃዎች አመልከተዋል። የጎልጉል ምንጮች ግን ኦህዴድ ውስጥ በከፍተኛ አመራሮች ደረጃ እየተካሄደ ያለው ግምገማ ሲጠናቀቅ በርካታ ባለስልጣኖች ክስ እንደሚመሰርትባቸው ተናግረዋል።
በቀድሞው የኦሮሚያ ፕሬዚዳንት አባ ዱላ ገመዳና በአቶ ድሪባ ላይ ይህ ውሳኔ የተላለፈው አገር ጥለው እንዳይወጡ በሚል ነው። ጎልጉል በቅርቡ ካገር መውጣት የማይችሉ ባለሥልጣኖች እንዳሉ ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል። ውሳኔው የተላለፈው ሰሞኑን የአዲስ አበባን አዲስ ማስተር ፕላን ለመተግበር የኦሮሚያ ክልል ከተሞች መካተታቸው ይፋ መሆኑን ተከትሎ ከተነሳው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ነው። ከሁለቱ ባለስልጣናት በተጨማሪ ከፍተኛ የክልልና የዞን የኦህዴድ አመራሮችም በደህንነት ቅርብ ክትትል እየተደረገባቸው መሆኑ ተሰምቷል። ካገር መውጣት የማይችሉም አሉ።
አባ ዱላ /ጃርሳው/
ሙክታር
አባ ዱላ ኦሮሚያን ሲረከቡ በማክረር አካሄድ የሚታወቁት አቶ ጁነዲን ያዋቀሩትን ካቢኔ በመበተን ሥራቸውን አንድ ብለው ጀመሩ። አዲስ ካቢኔ ሲገነቡ የመረጡት አዲስ የዩኒቨርስቲ ተመራቂዎችንና በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተቀናቃኝ (የተቃዋሚ) ፓርቲ አባላትን በማስኮብለል ነበር። ህወሃት ለሁለት በተበረገደበት ወቅት ለአቶ መለስ ቡድን ድጋፍ በመስጠት ቅድሚያ የያዙት አባ ዱላ ባስቀመጡት ውለታ መሰረት ኦሮሚያ ላይ ያሻቸውን እንዲያደርጉ የሟቹ መለስ ድጋፍ ነበራቸው። በዚህም ድጋፍ ሳቢያ ኦሮሚያ ላይ የሚፈልጉትን ሲያደርጉ ከተባረሩት መካከል የአሁኑ ፕሬዚዳንት ሙክታር ከዲር ይገኙበታል።
“አትደግፉን ነገር ግን የክልሉን ልማት አታደናቅፉ” በማለት አዲስ የመለመሏቸው የተለያየ አመለካከት ያላቸው አዳዲስ የኦህአዴድ አባላት ኦሮሚያን ከአባ ዱላ እጅ ተረከቡ። አባ ዱላ ፍጹም ነጻነት ይሰጡ ስለነበር ካድሬው ወደዳቸው። ስማቸው ተቀይሮ መለያ ተሰጣቸው፤ “ብራንድ” ሆኑ – “ጃርሳው” ተባሉ። በካቢኔያቸውና በሳቸው መካከል የነበረው ፍቅር በነደደበት ወቅት አባ ዱላ ክልሉን እንደሚለቁ ተሰማ። ባለፈው ምርጫ አባ ዱላ ለፌዴራል እንጂ ለክልል እንደማይወዳደሩ ይፋ ሲደረግ ካድሬው ገነፈለ። “የኢህአዴግ ምክር ቤትን ውሳኔ አንቀበልም” በማለት ተቃወመ። ከአንዴም ሁለት ጊዜ ስብሰባ ቢካሄድም ከስምምነት ላይ ሊደረስ ባለመቻሉ ተበተነ። በመጨረሻም ራሳቸው አባ ዱላ በመሩት ስብሳባ ካድሬውን ተማጽነው ነገሩ ረገበ። ይሁን እንጂ ቅርሾ ግን ነበር። ይህንኑ አስመልክቶ “ኦህዴድ/ኢህአዴግ በመደብ ትግል መተላለቅ ጀመረ” በማለት ዘግበን ነበር።
አባ ዱላ ኦሮሚያን ሲመሩ ቆይተው ሲመሻሸ “ይህንን ቤት ይዤ ለመታገል አይመቸኝም” በማለት ቦሌ ያስገነቡትን አስገራሚ ህንጻ ለኦህዴድ አስረከቡ። በከፍተኛ ሙስና ይታሙ ስለነበር ተናዘውና ገብረው ታለፉ። ለፌዴራል ተወዳድረው አፈ ጉባኤ ለመሆን በቁ። በወቅቱ የወ/ሮ አዜብ ድጋፍ ቢኖራቸውም የሼኽ መሐመድ ሁሴን አላሙዲን የቀኝ እጅ የሆኑ ባለስልጣኖች ግን ጠምደዋቸው ነበር። ሙክታር አህመድ አንዱና ዋናው ነበሩ። ከላይ በረከት ስምዖንና አዲሱ ለገሰ አባ ዱላን ከሚቃወሙ መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚቀመጡ ናቸው።
በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ አልፈው እዚህ የደረሱት አባ ዱላ ሰፊ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች ህይወት የቀጠፈውን የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን አስመልክቶ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ተገኝተው ተማሪዎችን ከወ/ሮ አስቴር ማሞ ጋር በመሆን አነጋግረው ነበር። በወቅቱ የተማሪዎቹ ጥያቄ ፍትሃዊ እንደሆነ ሲመሰክሩ፣ ይህንኑ ምስክርነታቸውን ለተለያዩ የአገር ውስጥና የውጪ አገር ሚዲያዎች አሳውቀውም ነበር። አያይዘውም ነፍስ ያለ አግባብ ያጠፉ እንደሚጠየቁ ቃል ገቡ።abadulla
የጎልጉል ምንጮች እንዳሉት አባ ዱላ ይህንን ከተናገሩ በኋላ ከፍተኛ ወቀሳ ተሰንዝሮባቸዋል። “ረብሻውን ያስነሱት ራሳቸው የኦህዴድ ካድሬዎች ናቸው” ከሚል ድምዳሜ የደረሰው ኢህአዴግ ችግሩ ከተፈጠረ በኋላ ሰፊ የስለላ ስራ አከናውኗል። “ጥፋተኞቹን ለህግ እናቀርባለን” በማለት መግለጫ ያወጣው ኢህአዴግ በቀጣይ የሚያስራቸውና የሚከሳቸው ባለስልጣኖች አሉ። ምንጮቹ በተለይ አባዱላና የአዲስ አበባ ከንቲባ የሆኑት አቶ ድሪባ ኩማ ላይ ስለሚወሰደው ርምጃ ያሉት ነገር ግን የለም። ክስ ከተመሰረተባቸውና ምርመራው በሰንሰለት ታች ድረስ ከዘለቀ የኦህአዴድ የታችኛው መዋቅር ሊናጋ እንደሚችል ግን ግምታቸውን አኑረዋል። ለምሳሌ ያነሱት ሽፈራው ሽጉጤን ነው። ሽፈራው ሽጉጤ በሙስና እንዲከሰሱ ከተወሰነ በኋላ የታለፉት “የሲዳማ ብሔረሰብ ይነሳል” በሚል እንደሆነ ያወሱት ምንጮች “ክስ ተመስርቶ ምርመራው ቢካሄድባቸው ወ/ሮ አዜብም አሉበት ሲሉ አስቀድመው በምክር ቤት ይፋ በማድረጋቸው ዝምታ ተመርጧል”።
ኦህዴድን ወደ ታች ማዘዝ እንደ ቀድሞው አይቀልም
አዲስ አበባንየሚያሰፋው አዲሱ ማስተር ፕላን ተግባራዊ እንዲሆን ሀሳብ ሲቀርብ ድፍን የኦህዴድ ምክር ቤትና ካቢኔ ተቃውሞ አሰምቷል። በክልሉ ምክር ቤት ደረጃም የተያዘው አቋም ተመሳሳይ ነው። ይህንን እውነት የሚያነሱ ክፍሎች ኢህአዴግ/ህወሃት ስንቱን አስሮና ለፍርድ አቅርቦ ይችለዋል ሲሉ ጥያቄ ይሰነዝራሉ” ቀደም ሲል በምርኮኞች ስብስብ የተቋቋመው ኦህዴድና አሁን ያለው ኦህዴድ የተለያዩ መሆናቸውን ኢህዴግ ችግር ሊገጥመው እንደሚችልም ግምታቸውን ያስቀድማሉ።
አሁን ያለው ኦህአዴድ ከምርኮ አስተሳሰብ የተላቀቀ። አዲስ ትውልድ የተካተተበት፣ በጎሳ አስተሳሰብ የተቃኙ፣ ህወሃት በሚፈልገው መጠን ከመታዘዝ በላይ ወደ ራሳቸው ደምና ጎሳ የተሳቡ፣ ይህንኑ አስተሳሰብ እስከ ቀበሌ መዋቅር ድረስ የተከሉ በመሆናቸው የተወሰኑ የበላይ አመራሮችን በማሰር ችገሩ ሊፈታ እንደማይችል ሰፊ አስተያየት እየተሰጠ ነው። ለዚህም ይመስላል ኢህአዴግ በመደብ መተላላቅ መጀመሩ ይፋ እየሆነ የመጣው።
የመጨረሻው መጀመሪያ
ለጊዜው ይፋ ሆኑ መረጃዎች እንደሚያመክቱት አባዱላና አቶ ድሪባ ኩማ ካገር መውጣት አይችሉም። የተጀመረው ግምገማ ተጠናቆ የሚሆነው ሳይታወቅ በቅርብ ክትትል ስር ናቸው። የጎልጉል ምንጮች እንደጠቆሙት የዞንና ወረዳ መዋቅሮች ላይ ርምጃ ለመውሰድ  ስጋት አለ። ካድሬው ዘንድም መደናገጥ ተፈጥሯል። ህወሃት ውስጥም የአቋም መለያየት ተከስቷል፡፡ በአንድ ወገን ካድሬው እንዳይሸፍትና በቀጣዩ ምርጫ ኢህአዴግን አሳልፎ እንዳይሰጠው ርምጃው የተለሳለሰ መሆን አለበት እየተባለ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ግለ ሂስ በማካሄድ ነገሩን የማርገብና ምርጫውን የማለፍ ስልታዊ አካሄድ አለ። ይሁን እንጂ ኦህዴድ እየተለማመደ ያለው አካሄድ ሌሎችን ትምህርት በሚሰጥ መልኩ ካልታረመ ወደ ፊት ችግሩን ያገዝፈዋል የሚል አቋም የሚያራምዱ መኖራቸው ታውቋል። ህወሃት በዚህ ደረጃ አቋም ለመያዝ አለመቻሉና በርዕዮተ ዓለም መከፋፈል መጀመሩ ለዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ የዘራው መርዝ መልሶ ራሱን ሊያጠፋው አፉን መክፈቱ የሚጠቁም ነው፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት “ኢህአዴግ በርዕዮተ ዓለም መበላላት መጀመሩ ይፋ እየሆነ ነው” የሚለው ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚነሳ ዓቢይ ጉዳይ ሆኗል፡፡